ህጻን ልጅ አፍንጫው ውስጥ መመርመሪያ ተከተቶ ሲመረመር

ከ 5 ሰአት በፊት

የዓለም የጤና ድርጅት በመጋቢት 2/2012 ዓ.ም. ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን ካወጀ አምስት ዓመት ሆነው።

በወቅቱ የዓለም መንግሥታት 2.6 ቢሊዮን ሰዎች ተከርቸም ያስገባውን የእንቅስቃሴ ገደብ፣ እንዲሁም ሰዎችን ለወራት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረገው ኳረንቲን ያሉ ከዚህ ቀደም ታይተው የማያውቁ እርምጃዎችን ተግብረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ቫይረሱ 777 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ ለሰባት ሚሊዮን ሰዎች ሞትም ምክንያት ሆኗል። እንደ ተቋሙ ግምት ከሆነ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ብዛት 15 ሚሊዮን ደርሷል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያመጣቸው አስከፊ መዘዞች አሁንም ድረስ ተፅዕኗቸው በተለያዩ መንገዶች እንደቀጠለ ነው። ከወረርሽኙ የተገኙ ትምህርቶችም ግን አልታጡም። ባለሙያዎች ከአስከፊው ጊዜ የተገኙ የተወሰኑ ጥሩ ትምህርቶችን ለይተው አውጥተዋል።

በቤልጂየም ብራሰልስ ከተማ በሚገኘው ቭራጅ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ የጤና ሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት እንዲሁም የጭንቀት እና የአእምሮ ቁስለት (trauma) ባለሙያ የሆኑት ኤልክ ቫን ሆፍ፤ በወረርሹ ወቅት የነበሩትን የእንቅስቃሴ ገደቦች የሚገልጿቸው “በታሪክ ትልቁ የጅነ ልቦና ሙከራ (experiment)” ብለው ነው።

ከወረርሽኙ የተገኙ አራት ትምህርቶችን እነሆ፡

90 ዓመቷ ማርጋሬት ኬናን ከህክምና ባለሞያ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ማርጋሬት ኬናን ፈቃድ ያገኘ የኮቪድ 19 ክትባት በመውሰድ በምዕራቡ ዓለም የመጀመሪያዋ ሰው ናቸው

በክትባት ቴክኖሎጂ ላይ የተገኙ እምርታዎች

ተመራማሪዎች ለኮቪድ 19 መከሰት ምክንያት የሆነው ሳርስ-ኮቭ-2 የተሰኘው ቫይረስ በተከሰተበት ወቅት ቫይረሱን ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚዋጋ ክትባት ለማዘጋጀት የወሰደባቸው ጊዜ ዘጠኝ ወራት ብቻ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ይህንንም ማሳካት የቻሉት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በክትባት ዕድገት ላይ አብዮት ያመጣውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው።

“ሴንተቲክ ሜሲንጀር አርኤንኤ” (synthetic messenger RNA) የተባለው የህክምና ቴክኖሎጂ ለብዙ ሰዎች የሚውል የክትባት ፕሮግራምን ለማበልጸግ የሚያስችል ውጤታማ ዘዴ እንዲሆን ለብዙ ዓመታት ምርምር ሲደረግበት ቆይቷል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ግን ይህ ሂደት በፍጥነት እንዲከናወን አድርጓል።

የአሜሪካዎቹ ፋይዘር እና ሞደርና እንዲሁም የጀርመኑ ባዮኤንቴክ የተባሉት የኩባንያዎች “ሴንተቲክ ሜሲንጀር አርኤንኤ”ን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ክትባቶቻቸውን መፍጠር ችለዋል። ይህም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ክትባት በመስጠት በቫይረሱ ሊከሰትባቸው ይችል ከነበረ የከፋ ጉዳት እንዲጠበቁ አድርጓል።

የዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑት የ90 ዓመቷ ማርጋሬት ኬናን፤ ኅዳር 29/2013 ዓ.ም. ፈቃድ ያገኘ ክትባት በመውሰድ በምዕራቡ ዓለም የመጀመሪያዋ ሰው ሆነው ነበር።

ይህንን የክትባት ቴክኖሎጂ ያገኙት ተመራማሪዎቹ ካታሊን ካሪኮ እና ድሪው ዋይዝማን በአውሮፓውያኑ 2023 በመድኃኒት ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።

በዓለም የጤና ድርጅት የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ማርጋሬት ሃሪስ፤ ክትባት ለማግኘት የተደረገውን ሽቅድድም የወረርሽኙ ትልቁ ጥሩ ትሩፋት ነው ሲሉ ይገልጹታል። ዶ/ር ማርጋሬት፤ “በማይታመን ፍጥነት የቴክኖሎጂ ዕድገቶች ሲከናወኑ ተመልክተናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሚሴንጀር አርኤንኤ ቴክኖሎጂ አስቀድሞም የሚታወቅ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ እንደ ካንሰር ክትባት ላሉ ሌሎች ምርምሮች ጥቅም ላይ ሲውል እያየን ነው” በማለት አክለዋል።

የኤድንብራ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪ ስሪድሃር፤ “Preventable: how a pandemic changed the world and how to stop the next one” የተሰኘ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ አሳትመዋል። እሳቸው እንደሚናገሩት ከወርሽኙ የተገኙ ትምህርቶች አዲስ ቫይረስ በሚከሰትበት ወቅት በቶሎ እንዲታወቅ እና እንዲለይ አስችሏል።

“ሳይንሳዊ አቅማችን ተሻሽሏል፤ ዘዴዎቻችንም አድገዋል” ይላሉ። “ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት የነበረን ጥያቄ ‘ክትባት እናገኛለን ወይ?’ የሚል ከነበረ፤ አሁን ጥያቄው ‘በምን ያህል ፍጥነት ክትባት ማምረት እንችላለን?’ የሚል ነው” ሲሉ የተገኘውን ዕድገት ያስረዳሉ።

በተጨማሪም፤ ለቀጣዩ ወረርሽኝ እንዴት መዘጋጀት እንደሚቻል ትምህርት መገኘቱን ፕሮፌሰሯ ይናገራሉ። ለምሳሌ፤ “የወረርሽኙን ወቅት በተሻለ ሁኔታ ያሳለፉ ሀገራት ከወረርሽኙም አስቀድሞ ጤናማ ሕዝብ የነበራቸው” መሆናቸውን ያነሳሉ።

ጭንብል ያደረጉ እና ቦር ሳያዙ ህጻናት በሰልፍ ደረጃ ሲወጡ

አዲስ ዘመን ለትምህርት

የትምህርት ቤቶች መዘጋት በመላው ዓመት በሚገኙ ህጻናት ላይ አስከፊ መዘዝ አስከትሏል። በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ የተከሰቱት ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ብዛት መጨመር እና የትምህርት መዘጋት ወረርሽኙ ካስከተላቸው ጠባሳዎች መካከል እንደሆኑ በኢንተር አሜሪካ ዲቨሎፕመንት ባንክ የትምህርት ኃላፊ የሆኑት መርሴዲስ ማቴኦ ይናገራሉ።

ማቴኦ፤ እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም ስለ ትምህርት በነበረው ምልከታ ላይ አዎንታዊ ለውጥ መኖሩን ታምናለች። “በትምህርት ላይ የሚደረገውን ክርክር ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን በማሸጋገር፣. . . የትምህርት ሥርዓትን መልሶ በማጤን ረገድ በጣም አዎንታዊ ተፅዕኖ ነበረው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የትምህርት ዘርፉ ዲጂታላይዝ በመደረግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደነበር በወረርሽኙ ወቅት ግልጽ ሆኗል” የሚሉት ማቴኦ፤ ትምህርትን በየትኛውም መንገድ ለመቀየር በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደነበር ያስረዳሉ። የኮቪድ 19 መከሰት ግን ትምህርት ቅልቅል እና ተለዋዋጭ በሆነ መንገድ እንዲሰጥ እንዳስገደደ ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት የመማሪያ ክፍሎችን በአካል መገኘት የሚጠይቁ እንዲሁም ቋሚ ቦታ አድርጎ የመውሰድ እሳቤ መቅረቱንም ገልጸዋል። የመማሪያ ክፍሎች መዘጋት የትምህርት ዘርፍን ፖለቲካዊ አጀንዳነት እንዲያድግ አድርጓል።

እንደ ማቴኦ ገለጻ፤ ከዚህም ባሻገር ወረርሽኙ ትምህርት ቤቶች በዘመናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸው ሚናን በተመለከተ ጥሩ ግንዛቤ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

በቪድዮ ጥሪ ትምህተት የምትከታተል ሴት

በሥራ ላይ የአመለካከት ለውጥ

ወረርሽኙን ተከትሎ ብዙ ሰዎች ከሥራ ገበታቸው መፈናቀላቸው እና በዚህም ምክንያት የተከሰተው ድህነት ከኮቪድ-19 አስከፊ መዘዞች አንዱ ነው።

ወረርሽኙ ጥቂት ወጣቶች እና ሴቶች ብቻ የሥራውን ዓለም እንዲቀላቀሉ አድርጓል። ይህም ወደፊት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ተግዳሮት እንደሚሆን ያሰጋል።

በወረርሽኙ ወቅት ከተገኙ ትምህርቶች አንዱ የሥራ ቅጥር እና የሰዎች ገቢ ጥበቃ ፖሊሲዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝን ለመቅረፍ ምን ያህል እገዛ እንደሚያደርጉ መረዳት መፈጠሩ እንደሆነ በዓለምአቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የላቲን አሜሪካ እና ካረቢያን የሠራተኞች ኢኮኖሚ ባለሙያ ጌርሰን ማርቲኔዝ ይናገራሉ።

ከእነዚህ ፖሊሲዎች አንዱ በአንድ ወቅት ላይ በተፈጠረ ችግር ምክንያት የተቀነሱ ሠራተኞች ሁኔታው ሲስተካከል ሥራቸውን መልሰው እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። እንደ ጌርሰን ገለጻ እነዚህ ስትራቴጂዎች ኢኮኖሚው በፍጥነት መልሶ እንዲያገግም ማድረጋቸው ጥርጥር የለውም።

የሥራ ገበያው በአንጻራዊነት በፍጥነት ቢያገግምም፤ እንደ ጂኦፖለቲካል ውጥረቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የሀገራት ዕዳ መጨመር ያሉ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ይህ መሻሻል እንዳይቀጥል ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተቋሙ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አስጠንቅቋል።

ምናልባት ግን እጅጉን የተለመደው የሥራ ቦታ ለውጥ ሥራዎች ከርቀት እና በቅይጥ መንገድ መሠራት መቻላቸው ነው። ምንም እንኳ አሁን ላይ ብዛት ያላቸው የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞች ወደ የሙሉ ጊዜ የፊት ለፊት የሥራ ሁኔታ እንዲመለሱ ግፊት እያደረጉ ቢሆንም፣ በቅይጥ መንገድ መሥራት ለምርታማነት የሚያስገኘውን ጥቅም በተመለከተ ያሉት ማስረጃዎች የተደበላለቁ ናቸው።

ብዙ መንግሥታት ከርቀት መሥራትን በተመለከተ ሕጎችን አሻሽለዋል። ለምሳሌ እንደ አየርላንድ እና ፈረንሳይ ያሉ ሀገራት፤ አለቆች ከሥራ ሰዓት ውጪ ከሠራተኞች ጋር ግንኙነት እንዳይፈጥሩ ሚያደርጉ ሕጎችን አዘጋጅተዋል።

በተጨማሪም በወረርሽኙ ምክንያት የመጣው የቴክኖሎጂ አብዮት ውጤታማነትን በፍጥነት ለማግኘት የሚያስችል “ወርቃማ ዕድል” መፍጠሩን ማርቲኔዝ ይናገራሉ። ለምሳሌ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የሥራ ሂደታቸውን እንዲመሩ አስችሏል።

ግድግዳ ላይ የተሳለ ጭንብል አድርገው የሚሳሳሙ ሰዎች ስዕል

ለአእምሮ ጤና ቅድሚያ መስጠት

በወረርሽኙ ወቅት በመላው ዓለም የተሠራጨው የመታሰር ስሜት፣ እርግጠኝነት ማጣት፣ ብቸኝነት እንዲሁም ፍርሃት እና ጭንቀት በወረርሽኝ ወቅት መኖር ብቻውን ህመም የሚፈጠር ስሜት እንዲሆን አድርጓል።

እንደ የዓለም እና የፓን አሜሪካ የጤና ድርጅቶች ያሉ ተቋማት ወረርሽኙን ተከትለው በመጡት የድብርት እና ጭንቀት በሽታዎች መጨመር እንዲሁም ራስን የማጥፋት ባህሪ እና ሃሳቦች መስፋፋትን በተመለከተ ያደረጓቸው ጥልቅ ጥናቶች ብዛት ጨምሯል።

ወረርሽኙ “በሰዎች ስሜታዊ ትውስታ እና ስሜት የመጋራት መንገድ ላይ” ተፅእኖ እንዳሳደረ በጭንቀት፣ በውጥረት እና በድብርት በሽታዎች ላይ ባለሙያ የሆኑት የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ላውራ ሮጃስ ማርኮስ ያስረዳሉ። ነገር ግን ወረርሽኙ “ስቃይን ብቻ ሳይሆን ትምህርትንም በተመለከተ ለውጥ የተፈጠረበት” እንደሆነ ባለሙያዋ ይናገራሉ።

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ በአሁኑ ወቅት የአእምሮ ጤንነት “ከሰውነታችን የተነጠለ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የተገናኘ” መሆኑን በመረዳት፤ የአእምሮ ጤንነታችንን መቀጠበቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድንረዳ አድርጓል።

“ሰዎች ይህንን ዕድል ሕይወታቸውን ለመገምገም ተጠቅመውበታል፤ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን፣ አካባቢያቸውን እና ኅልውናቸውን ጭምር እንደ ቀላል ነገር አለመውሰድን ተምረውበታል” ሲሉ ባለሙያዋ ያክላሉ።

ቢቢቢ ወርልድ ሰርቪስ ‘ግሎብስካን’ በተባለ ኩባንያ በ2022 ያስጠናው ጥናት፤ በ30 ሀገራት ከሚገኙ የጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል አንድ ሦስተኛው ከወርሽኙ በፊት ከነበረው የተሻለ ስሜት እንደሚሰማቸው አመልክቷል።

ብዙዎቹ ከቤተሰባቸው ጋር የበለጠ ጊዜ እንደሚያሳልፉ፣ ከማኅበረተሰባቸው እና ከተፈጥሮ ጋር የተሻለ ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው እንዲሁም በአጠቃላይ ቅድሚያ ስለሚሰጧቸው ጉዳዮች ይበልጥ ግልፅ ስሜት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።እነዚህ ለውጦች አዎንታዊ ውጤቶች እንደሆኑ ጥናቱ ጠቅሷል።

ወረርሽኑ የቪድዮ ጥሪን በሰፊው ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረጉ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ሕክምና የሚሰጡበት መንገድ ላይም ዘላቂ እና ስር ነቀል ለውጥ አስከትሏል።

በሥነ ልቦና ህክምና ላይ የተፈጠረው ይህ ለውጥ ባለሙያዎች ለምሳሌ በጦርነት ውስጥ ላሉ የዩክሬን ወታደሮች ወይም ርቀት ቦታ ለሚገኙ ደንበኞቻቸው እርዳታ እንዲያቀርቡ አስችሏል።

እንደ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ላውራ ሮጃስ ማርኮስ ገለጻ ወረርሽኙ፤ የተፈጥሯችን ሁለት ዋነኛ ጉዳዮች ስለሆኑት ችግሮችን የመቋቋም ጥንካሬ እና ሰብአዊ ርህራሄ ቆም ብለን እንድናስብ አድርጓል።

ባለሙያዋ፤ እነዚህ የአብሮነት ምልክት የሆኑ ጉዳዮች የጨለማው ወቅት ብሩህ ጊዜያት ነበሩ ይላሉ።