ዶናልድ ትራምፕ

ከ 4 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ የዓለም ሀገራት ላይ ተጨማሪ ታሪፍ ለመጣል ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝደንቱ የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ ካናዳ እና የአውሮፓ ኅብረት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።

ትራምፕ እኒህ እርምጃ የወሰዱ እና ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ላይ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ታሪፍ እንደሚጥሉ ተናግረዋል።

“እኛ ላይ የሚጥሉትን ክፍያ ሁሉ እኛም እነሱ ላይ እንጥላለን” ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ያሰሙት ማስጠንቀቂያ የንግድ ጦርነቱ እንዳይባባስ እንዲሁም በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገራት ምጣኔ ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያመጣ ተሰግቷል።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በብረታ ብረት እና አሉሚኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ የጣሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም በነፃ ይልኩ የነበሩ ሀገራትም የታሪፍ ጫናው እንደሚመለከታቸው አስታውቀዋል።

በያዝነው ወር መባቻ ትራምፕ ከቻይና የሚመጡ ምርቶች ላይ የ20 በመቶ ታሪፍ መጣላቸው አይዘነጋም።

ቁሳቁስ ወደ ሀገራት ሲገቡ የሚጣል ግብር የሆነው ታሪፍ እንደ ኮፐር፣ የእንጨት ምርቶች እና ተሽከርካሪዎች ላይ እንደሚጥሉም አስጠንቅቀዋል።

የአውሮፓ ሀገራት እና የካናዳ መሪዎች የፕሬዝደንቱን እርምጃ ምክንያታዊ ያልሆነ ሲሉ የወቀሱት ሲሆን የራሳቸውን ታሪፍ አሜሪካ ላይ ጥለዋል።

ሌሎች ለአሜሪካ ገበያ በርካታ ምርቶችን በመላክ የሚታወቁት ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ሜክሲኮ እና ብራዚል ለጊዜው እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበዋል።

“ልክ እንደማንኛውም ሰው የብረታ ብረት እና አሉሚኒየም ምርቶች ላይ ዓለም አቀፍ ታሪፍ መጣሉ አበሳጭቶኛል። ነገር ግን በተረጋጋ መልኩ ሁኔታዎች ማጤን እንሻለን” ሲሉ የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ተናግረዋል።

ካናዳ ከሐሙስ ጀምሮ ከአሜሪካ የሚመጡ 30 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥል አስታውቃለች።

ትሩዶን ተክተው ሥልጣን የሚረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ከትራምፕ ጋር አዲስ የንግድ ስምምነት ለመድረስ ዝግጁ መሆናቸውን ገለፀዋል። ነገር ግን ስምምነቱ የካናዳ “ሉዓላዊነትን ያከበረ” ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት 26 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጡ የአሜሪካ ምርቶች ላይ ከሚመጣው የፈረንጆቹ ወር መባቻ ጀምሮ ታሪፍ እንደሚጥል አስታውቋል።

ምንም እንኳ ትራምፕ በሒደት የአሜሪካ ብረታ ብረት እና አሉሚኒየም ኢንዱስትሪ እንዲበለፅግ እፈልጋለሁ ቢሉም የሚጥሉት ታሪፍ ሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ ተፅዕኖ ያመጣል ሲሉ ተንታኞች ይሞግታሉ።

ኩባንያዎች ከውጭ የሚያስመጧቸው ምርቶች ላይ የተጣለው ታሪፍ እንዲነሳላቸው ለትራምፕ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት የአየርላንዱን ፕሬዝደንት በቢሯቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ “በደንብ እንጂ” ሲሉ ታሪፍ መጣላቸውን እንደሚቀጥሉበት ተናግረዋል።