
ከ 1 ሰአት በፊት
በትግራይ በህወሓት አመራሮች መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባት ተባብሶ አንደኛው ወገን በታጣቁ ኃይሎች በመታገዝ የአስተዳደር ተቋማትን እየተቆጣጠረ ይገኛል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረ ፂዮን ገብረ ሚካኤል የሚመሩት ቡድን እየወሰደ ያለው እርምጃን “እብደት” በማለት ድርጊቱ ክልሉን ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊወስደው ይችላል ሲሉ እያስጠነቀቁ ነው።
ባለፉት ቀናት የተባባሰውን ሁኔታ ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ በአሁኑ ጊዜ የት እንዳሉ፣ ወደ መቀለስ መቼ እንደሚመለሱ፣ የፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ ስለመጠየቃቸው፣ አስተዳደራቸው በክልሉ ውስጥ ስላለው የመቆጣጠር አቅም የቢቢሲ ኒውስ ባልደራባ ካትሪን ባይሩሃንጋ ጠይቃቸዋለች።
አቶ ጌታቸው በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ስለተከሰተው ቀውስ መልስ በመስጠት ይጀምራሉ።
አቶ ጌታቸው፡ የመንግሥት ማህተም መንጠቅ ማለት ሥልጣን መያዝ ማለት አይደለም። ነገር ግን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በማዘባረቅ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት መጠምዘዝ ነው ዓላማው። አንድ የህወሓት አንጃ ከፌዴራል መንግሥት ጋር መደራደር ከጀመረ የፕሬዝደንትነት ቦታውን ይይዛል የሚል አስተሳሰብ አለ።
አብዛኛው የወታደሩ ክፍል የትግራይ የግዛት አንድነት መጠበቅ አለበት ብሎ ነው የሚያምነው፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈፀም ይሻል። አንዳንድ ቦታዎች ሰው በተሰበሰበት ጥይት ተተኩሷል።
ይህ የሆነው አንዳንድ ‘እብድ’ ሰዎች የመንግሥት ማህተም ለመንጠቅ እና ሥልጣን ለመያዝ ካላቸው ጥም የተነሳ ነው። ዓላማው ከተማ መቆጣጠር ሳይሆን በአንዳንድ ከተሞች ግርግር መፍጠር ነው።
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ቢቢሲ፡ አሁን ትግራይ ነው ያሉት?
አቶ ጌታቸው፡አሁን አዲስ አበባ ነው ያለሁት።
ቢቢሲ፡ ትግራይን ጥለው ለምን ወጡ?
አቶ ጌታቸው፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ [ዐቢይ አሕመድ] ስልክ ተደውሎልኝ ነው የመጣሁት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሬት ላይ ያለውን ነገር እንዳብራራላቸው ነው የጠሩኝ። ይህን ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶች ጋር እየተወያየሁበት ነው ያለሁት። ከአውሮፓና እና ከዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደሮችም ጋር አውርቻለሁ። እነዚህ ሰዎች ሁኔታውን እየተከታተሉት ይገኛሉ። የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈፃሚነ እንዲሆንም እያገዙን ያሉ ዲፕሎማቶች ናቸው።
ቢቢሲ፡ በቅርቡ [ወደ ትግራይ] ይመለሳሉ?
አቶ ጌታቸው፡ አዎ እመለሳለሁ።
ቢቢሲ፡ መቼ?
አቶ ጌታቸው፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያለኝን ስበሰባ ማጠናቀቅ አለብኝ። በሚቀጥሉት ቀናት ሌሎች ስብሰባዎችም አሉኝ። በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ [ወደ ትግራይ] እመለሳለሁ። ዕቅዴ እሱ ነው።
ቢቢሲ፡ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የምንመለከተው ነገር ከትግራይ ሸሽተው እንደወጡ ነው።
አቶ ጌታቸው፡ ለምንድን ነው ከትግራይ የምሸሸው?
ቢቢሲ፡ ትግራይ ክልል ባለው የደኅንነት ጉዳይ እና ሁኔታውን መቆጣጠር ባለመቻልዎ?
አቶ ጌታቸው፡ አንድ ነገር ልንገርሽ። ትላንት [ማክሰኞ] ከሰዓት ከሕዝብ ጋር ውይይት እያደረግኩ ነበር። የጊዜያዊ አስተዳደሩ አጋር የሆነው የፌዴራል መንግሥቱ ስልክ ደወለልኝ። እርግጥ ነው ሁኔታው የሚያሳስብ ነው። ፌዴራል መንግሥቱ ትግራይን የሚያስተዳድሩ ሰዎችን ስብሰባ ጠርቶ የማናገር መብት አለው።
ነገር ግን ይህ የሚባለው ነገር እንደኛው የህወሓት ክፍል ብዥታ መፍጠር ካለው ዓላማ ነው። ለውጥ ማምጣት የሚሹ ሰዎችን እኔን ጨምሮ ከትግራይ እየወጡ ነው ይላሉ። ነገር ግን ትግራይን ሸሽቶ ወጥቷል የሚባለው ሐሰት ነው። ሕዝቡን ግራ ለማጋባት ያሰራጩት ወሬ ነው።
- መቀለ አቅራቢያ በምትገኘው አዲጉዶም ከተማ የተከሰተው ምንድን ነው?12 መጋቢት 2025
- አቶ ጌታቸው የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጣልቃ ለመግባት በቂ ምክንያት እንዳለው ተናገሩ12 መጋቢት 2025
- ትግራይ ውስጥ እየሆነ ያለው ምንድን ነው?11 መጋቢት 2025

ቢቢሲ፡ ከፌዴራል መንግሥቱ እርዳታ ጠይቀዋል። ምን ማለት ነው ይሄ? የፌዴራል ኃይሎች ጣልቃ እንዲገቡ ይፈልጋሉ ማለት ነው?
አቶ ጌታቸው፡ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ ኃይሉን ማሰማራት ቢችልም አሁን ባለው ሁኔታ የፌዴራል መንግሥቱ ኃይሎች ጣልቃ መግባታቸው ትክክለኛው እርምጃ ነው ብዬ አላስብም።
ፌዴራል መንግሥት ከኤርትራ ጋር የምንጋራውን ድንበር የመጠበቅም ኃላፊነት አለበት። ነገር ግን እኛ የምንፈልገው ድጋፍ አሁን ግርግር እየፈጠሩ ያሉ ኃይሎች ወደ ልቡናቸው እንዲመለሱ ዕድል እንዲሰጣቸው ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ካደረግኩ በኋላ የሚፈጠረውን የምናየው ይሆናል።
ቢቢሲ፡ በርካታ የትግራእ ተወላጆች ህወሓት አሁንም ወደ ግጭት ሊወስደን ይችላል ብለው ያምናሉ። ከዚህ ቀደም ከነበረው ጦርነት አልፎ አሁን ደግሞ እርስ በራሱ ተከፋፍሏል ይላሉ።
አቶ ጌታቸው፡ በዚህ በጣም ነው የምስማማው። ያፈነገጠው ህወሓት ባለሥልጣናትም ሆኑ በቅርቡ ከሕግ በላይ የሆነ ድርጊት ለመፈፀም የሞከሩ ወታደሮች ጉዳይ የሚጠቀስ ነው። የትግራይ ሕዝብ ሰላም ይገባዋል. . .
ቢቢሲ፡ ነገር ግን እርስዎም የህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበር ነዎት። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ነዎት። እርስዎም የውድቀቱ አካል ነዎት ማለት ነው።
አቶ ጌታቸው፡ አዎ የውድቀቱ አካል ነኝ። ይህንን ክጄ አላውቅም። የዚህ ችግር አካል በመሆኑ ኃላፊነቱ ከመውሰድ ወደኋላ አላልም። እያልኩ ያለሁት ሌላኛው የህወሓት ክፍል በወታደሩ ታግዞ እየፈፀመ ያለው ድርጊት ሊያሳስበን ይገባል ነው።
ይህ ጉዳይ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ድጋሚ ጦርነት ውስጥ እንድንገባ ከማድረጉም በላይ ሌሎች የውጭ ኃይሎች እንዲሳተፉ ሊያደርግ ይችላል። ይህ እንዲሆን በፍፁም አልፈልግም። ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ ይህ አይገባውም።
ቢቢሲ፡ አሁን ያለው ስጋት የጎረቤት ሀገር፣ ኤርትራ ኃይሎች አንዱን አንጃ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ሌላኛውን ደግፈው በትግራይ ጦርነት ያደርጋሉ የሚል ነው።
አቶ ጌታቸው፡ይህ ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱ የትኛውን ወገን ይደግፋል የሚል አይደለም። የፌዴራል መንግሥቱ መሳተፍ ቢፈልግም ኃይሎችን ማሰመራት ይፈልጋል ማለት አይደለም።
ኤርትራ ይህን አጋጣሚ ተጠቅማ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ ብትገባ የጦርነት አውድማ የምትሆነው ትግራይ ናት። ይህን ለማስወገድ ነው የምፈልገው። አለመታደል ሆኖ አንዳንድ የህወሓት ባለሥልጣናት ፈቃደኛ እየሆኑ አይደለም። ቢሆንም ይህን ለማስወገድ ባለን አቅም የተቻለንን ማድረግ አለብን።
ቢቢሲ፡ አሁን የእርስዎ የጊዜያዊ አስተዳደር ምን ያህል ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው? ትግራይን ማስተዳደር ይችላል?
አቶ ጌታቸው፡ አንዳንድ የወታደሩ አካላት ማህተም በመንጠቁ ተግባር ተሳትፈዋል ማለት መላው የትግራይ መከላከያ ኃይል አንደኛውን የህወሓት ኃይል ይደግፋል ማለት አይደለም። እኔ የማውቀው ብዛት ያለው የህወሓት ክፍል እና ብዛት ያለው የወታደሩ ክፍል ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን ነው። አሁን ያለውን መንገጫገጭ መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ግልፅ ነው።
ቢቢሲ፡ ጥያቄዬን አልመለሱልኝም። አስተዳደርዎ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው ወይ? ትግራይን መቆጣጠር ይችላል ወይ?
አቶ ጌታቸው፡ አሁን ባለው ሁኔታ በአንደኛው የህወሓት ክፍል ምክንያት የሰሜን ምሥራቅ እና ማዕከላዊ ቦታዎችን ቁጥጥር አጥቷል። ይህንን መልሰን መቆጣጠር አለብን ነው የምንለው። ምክንያቱም ሕዝቡ መንግሥት የሚያቀርበውን አገልግሎት ማግኘት አለበት።