
12 መጋቢት 2025
ማክሰኞ መጋቢት 2/2017 ዓ.ም. ከመቀለ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው አዲጉዶም ከተማ፣ በደብረፅዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) በሚመራው የህወሓት ክንፍ ይደግፋሉ የተባሉ የትግራይ ኃይል አባላት በንፁኅን ዜጎች ላይ ተኩስ ከፍተው አራት ሰዎች ማቁሰላቸውን ነዋሪዎች እና ተጐጂዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
የትግራይ ሠራዊት አባላት ማክሰኞ ዕለት የአዲጉዶም ከተማ ጽህፈት ቤትን በኃይል ይዘው የከተማውን ከንቲባ በቁጥጥር ስር ያደረጉ ሲሆን፣ ከንቲባውን እና ምክትላቸውን ጨምሮ የካቢኔ አባላት ደግሞ ከቤታቸው መወሰዳቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ማክሰኞ ጀምሮ በርካታ የታጠቁ የሠራዊት አባላት በከተማው እና በሌሎችም አካባቢዎች ተሰማርተው ይገኛሉ።
ቢቢሲ ትግርኛ ተጎጂዎችን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ነዋሪዎችን እና የደቡብ ምሥራቅ ዞን አስተዳደርን አነጋግሮ ማረጋገጥ እንደቻለው የታጠቁ የህወሓት አባላት የአዲጉዶም ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤትን በመክበብ ከንቲባውን እና ካቢኔያቸውን ጨምሮ ሰባት አመራሮችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋዊ ኤክስ ገጻቸው ላይ በአዲጉዶም ከተማ እና በመቀለ አንዳንድ አካባቢዎች የትግራይ ኃይል አዛዦች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ በርካቶች መቁሰላቸውን አስፍረዋል።
የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደገለፁት ማክሰኞ ዕለት በአዲጉዶም ከተማ እና አካባቢው በሚገኘው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ነዋሪዎች ተሰብስበው የነበረ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ ሕዝቡን ለመበተን ተኩስ ከፍተዋል።
በአድጉዶም ከተማ የተሰማራው እና የከተማዋን አስተዳደር የተቆጣጠረው የትግራይ ታጣቂ ኃይል ሠራዊት 44 አባላት መሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
የከተማው ነዋሪ አቶ ገብረሕይወት ኃይለ በወቅቱ በጽህፈት ቤቱ አቅራቢያ በሚገኘው የወላጆቻቸው ቤት ውስጥ እንደነበሩ ስለነበሩ ሁኔታዎችን ተመልክተዋል።
“የወላጆቻችን ቤት በሚገኝበት አካባቢ ምሽግ ሠርተው [ታጣቂዎች] እዚያ ቆይተዋል፤ ልዩ ኃይሎቹ ከንቲባውን እና ካቢኔዎቻቸውን በወሰዱበት ጊዜ ነዋሪዎቹ ተሰብስበው ነበር። በወቅቱ ለምን በሚል ጥያቄ ሲያነሱም ታጣቂዎቹ ተኩስ ከፈቱ” ብለዋል።
“ተኩሱ የተከፈተው ቤታችን አካባቢ ነው። አንድ ወጣት በጥይት ተመትቶ ሲወድቅ አይቻለሁ። ወጣቱ ታፋው ላይ ነው በጥይት የተመታው። በአካባቢው ድሽቃ ተጠምዶ አይቻለሁ” ብሏል።
በመጀመሪያ በተተኮሰው ጥይት የተመታው የ30 ዓመቱ ወጣት ሞጎስ ኪዳነ ይባላል። አሁን በአዲጉዶም ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት ይገኛል።
ሞጎስ በዕለቱ በርካታ ወታደሮች በከተማዋ እንደተሰማሩ በመግለጽ “አምስት ሰዎች በጥይት ተመትተናል። እኔ ታፋየ ላይ ነው ተኩሰው የመቱኝ። ከዚያም ስወድቅ በዱላ ደጋግመው ደበደቡኝ፤ አሁን በከባድ ህመም ላይ ነኝ” በማለት ጥቃቱ ምንም ግጭት ወይም አለመግባባት ባልነበረበት ሁኔታ እንደተፈፀመ ብሏል።
የገብረሕይወት ኃይለ ታናሽ ወንድም ዓለም ኃይለም በተኩሱ ከተጎዱ አራት ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
“በመጀመሪያ ሕዝቡን ለመበተን ወደ ሰማይ ተኮሱ። ከዚያ ወጣቱ መሮጥ ሲጀምር በቀጥታ ሰላማዊ ሰው ላይ መተኮስ ጀመሩ። አራት ሰዎች ቆስለዋል። አራተኛው የእናቴ ልጅ ታናሽ ወንድሜ ነው” በማለት ወንድሙ አሁን በአዲጉዶም ሆስፒታል እንደሚገኝ ገልጿል።
የደቡብ ምሥራቅ ዞን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፀጋይ ገብረተኽለ ጥቃቱን መፈጸሙን አረጋግጠው፤ ሰዎች በጥይት ጭንቅላት፣ ደረት እና እግራቸውን መመታቸውን ጠቅሰዋል።
በጥይት ተመትተው ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው አራቱ ሰዎች መካከል ሁለቱ ለተጨማሪ ሕክምና ወደ መቀለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል መላካቸውንም ተናግረዋል።
- አቶ ጌታቸው የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጣልቃ ለመግባት በቂ ምክንያት እንዳለው ተናገሩ12 መጋቢት 2025
- ትግራይ ውስጥ እየሆነ ያለው ምንድን ነው?11 መጋቢት 2025
- “በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ11 መጋቢት 2025
በታጣቂዎች ተወስደዋል የተባሉት እነማን ናቸው?
የደቡብ ምሥራቅ ዞን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፀጋይ ገብረተኽለ ከአድጉዶም ከተማ በተጨማሪ ረቡዕ ዕለት በሃገረሰላም፣ በደጉዓ ተንቤን፣ በሳምረ እና በሰሓርቲ ወረዳዎች በደብረፅዮን የሚመራውን የህወሓት ክንፍን የሚደግፉ ታጣቂዎች “ቁልፍ በመስበር በኃይል የአስተዳደር ቢሮዎችን እንደተቆጣጠሩ” ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በአድጉዶም ከተማ የተሰማራው እና የከተማዋን አስተዳደር የተቆጣጠረው የትግራይ ታጣቂ ኃይል ሠራዊት 44 አባላት መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ በአድጉዶም ከንቲባውን እና ምክትላቸውን ጨምሮ ሰባት አመራሮችን አፍነው በጽህፈት ቤቱ ላይ ተኩስ እንደከፈቱ እና “እስከ አመሻሽ 11፡00 ሰዓት ድረስ ማህተም እና ቁልፋ እንዲያስረክቡ በመጠየቅ ግርግር ፈጥረው ነበር” ብለዋል።
የአዲጉዶም ከንቲባ ኢንጂነር አንዶም ወልዱ፣ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ዓወት ተወልደ፣ የፀጥታ ኃላፊው አቶ አባዲ፣ የከተማው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይርጋ፣ አቶ ሃደራ (ሊቀመንበር) እና አቶ ዕፃይ ከወጣቶች ማኅበር እና ሌላም ወጣት ታፍነው መወሰዳቸውንም ተናግረዋል።

ዛሬ (ረቡዕ) ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የታጠቁ ኃይሎች በመሰማራታቸው ሕዝቡ ከተለመደው ዕለታዊ እንቅስቃሴ ተገድቦ መዋሉን እና ረቡዕ ከመንጋቱ በፊት ታጣቂዎች ቤት ለቤት በመዞር ሰዎች ሲያድኑ እና ሲያስሩ እንደነበረ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ ሁኔታውን ለቢቢሲ ሲያስረዳ “ከጦርነቱ በኋላ እንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥመናል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር” ብሏል።
በተጨማሪም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በታጠቁ ሰዎች የተከበቡ ሲሆን፣ የሕዝብ አገልግሎት ሳይሰጡ ውለዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች ረቡዕ ማለዳ እንደተለመደው ወደ ቢሯቸው ለመግባት ሲሞክሩ በታጣቂዎቹ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በከተማው የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ሹሙዬ ገዛኢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቢሮው ረቡዕ ጠዋት በታጣቂዎች ተዘግቷል።
“ማክሰኞ ከባድ ተኩስ ነበረ፤ ረቡዕ ጠዋቱ 2፡00 ላይ ወደ ሥራ ለመግባት ወደ ቢሮ ሄድን ቢሮው በታጣቂዎች ተከብቧል። ወደ ቢሮ ለመግባት ቀርቶ በዚያ በኩል ለማለፍ የሚያስፈራ ሁኔታ ነው ያለው” ብለዋል።
የደቡብ ምሥራቅ ዞን ርዕሰ መስተዳድር ፀጋይ ገብረተኽለ እንደተናገሩት በከተማው በ50 ሜትር ርቀት ላይ ኬላዎች ተዘጋጅተዋል።
ረቡዕ (ረቡዕ) ከሰዓት በኋላ በከተማዋ የተፈፀመውን ጥቃት እና አፈና ለማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የሞከሩ ነዋሪዎች በታጣቂዎቹ መበተናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

ውጥረቱ እዚህ እንዴት ደረሰ?
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ማክሰኞ በይፋዊ ኤክስ ገጻቸው ላይ በአዲጉዶም ከተማ እና በመቀለ አንዳንድ አካባቢዎች የትግራይ ኃይል አዛዦች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ በርካቶች መቁሰላቸውን ጽፈዋል።
ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድንን የሚደግፉ የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ አዛዦች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እየተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በእነርሱ የተሾሙ ግለሰቦችም በኃይል ቢሮዎችን መቆጣጠር ጀምረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥት በክልሉ ጣልቃ መግባትን ጨምሮ “የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ” በቂ ምክንያት እንዳለው ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የመንግሥትን መዋቅር አፍርሰዋል በሚል አራት የሠራዊት አዛዦችን ማገዳቸው ይታወቃል።
በሌ/ጄኔራል ፍስሃ ኪዳኑ (ፍስሃ ማንጁስ) የሚመራው የትግራይ ሰላምና ደኅንነት ቢሮ የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ እንደማይቀበል ያሳወቀ ሲሆን የቢቶ ኃላፊውም በተመሳሳይ ዕግድ ተጥሎባቸዋል።
በትግራይ ለወራት የቆየው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ያለው ውጥረት እና ፍጥጫ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።