ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ወታደራዊ አዛዣቸው ወታደራዊ ልብስ ለብሰው

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ በዩክሬን እና ሩስያ መካከል ሊደረግ ስለሚችል የተኩስ አቁም ስምምነት ንግግር ለማድረግ ወደ ሞስኮ ማቅናታቸውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

የቡድኑ ወደ ሩስያ የመጓዝ ዜና የተሰማው፤ በሳውዲ አረቢያ በተደረገው የአሜሪካ እና ዩክሬን ባለስልጣናት ስብሰባ ላይ የኪዬቭ ባለስልጣናት ለ30 ቀናት ተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸው ከተነገረ በኋላ ነው።

ከዚህ ጉዞ አስቀድሞ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሮቢዮ “በእውነቱ ኳሱ እጃቸው [በሩስያ ሜዳ] ነው” ብለው ነበር። አሜሪካ፤ ይህንን ጦርነት ለመቋጨት ብቸኛው መንገድ የሰላም ስምምነት እንደሆነ እንደምታምንም ተናግረዋል።

የአሜሪካው ቡድን የተጓዘው፤ የሩስያውን ሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ኩርስክ የተባለውን ግዛት እየጎበኙ መሆኑን ክሬምሊን ባስታወቀበት ጊዜ ነው።

ማክሰኞ ዕለት በጅዳ ከተደረገው ንግግር በኋላ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ስምምነት የተደረሰበትን “አዎንታዊ” እቅድ ሩስያ እንድትቀበለው የማድረግ ኃላፊነት አሜሪካ እንደሆነ ተናግረዋል።

ክሬምሊን በበኩሉ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እየተመለከተው መሆኑን የገለጸ ሲሆን በትራምፕ እና በፑቲን መካከል በስልክ ንግግር ሊደረግ እንደሚችልም ጠቁሟል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ የአየር ላንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ማይክል ማርቲንን በቤተ መንግስታቸው በተቀበሉበት ወቅት፤ የተኩስ አቁሙን በተመለከተ “በጎ መልዕክት” መቀበላቸውን ገልጸዋል።

“በጎ መልዕክት ግን ምንም ነው” ያሉት ትራምፕ፤ “ይህ በጣም ከባድ ሁኔታ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የትኛዎቹ የአሜሪካ ባለስልጣናት ወደ ሞስኮ እንደተጓዙ አልገለጹም።

ይሁንና የነጩ ቤተ መንግስት ፕሬስ ሰክሬቴሪያት ካሮላይን ሌቪት፤ የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ማይክ ዋልትዝ የሩስያ አቻቸውን ማነጋገራቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የጅዳውን ንግግር ተከትሎ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ ወደ ሞስኮ እንደሚጓዙ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ዋይት ሃውስ ረቡዕ ዕለት ይህንኑ አረጋግጧል።

ፕሬስ ሰክሬቴሪያት ካሮላይን ሌቪት፤ “ሩስያዎቹ ይህንን እቅድ እንዲፈርሙ እናሳስባለን። በዚህ ጦርነት ወደ ሰላም መጠጋት የቻልነው በዚህ ልክ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ክሬምሊን፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እየተመለከተ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ቃል አቀባዩ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው ዝርዝር ጉዳዮች በቀጣዮቹ ቀናት “በተለያዩ መንገዶች” እንደሚገለጽ ጠቅሰዋል።

ትራምፕ በቤተ መንግስታቸው ባደረጉት ንግግር የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለሩስያ ትርጉም የሚሰጥ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። ዝርዝር ጉዳዮችን ባይናገሩም የተኩስ አቁሙ “ለሩስያ አሉታዊ ጎኖች” እንዳለውም ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

“በአንድ በኩል፤ በጣም ውስብስብ የሆነውን ሁኔታ ፈትተነዋል። ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተፈትቷል። ስለ መሬት እና ከእርሱ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮችም ተነጋግረናል” በማለት ተናግረዋል። ትራምፕ አክለውም፤ “ስለ መሬት የተነጋገርንባቸውን አካባቢዎች እናውቃቸዋለን። ጉዳዩ ከዚያ የመውጣት ወይም ያለመውጣት ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ፤ ሩስያ ላይ ጫና ለመፍጠር ሲባል “ፋይናንስ ነክ ጉዳዮችን እንደሚያከናውኑም” ገልጸዋል። “ያ ለሩስያ በጣም መጥፎ ሊሆን ይችላል” ያሉት ትራምፕ፤ “ሰላም ማግኘት ስለምፈልግ ያንን ማድረግ አልፈልግም” ሲሉ ተደምጠዋል።

የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለስልጣናት በጅዳ ያደረጉት ስብሰባ፣ ወደ ንትርክ ከተቀየረው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እንዲሁም የፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ጄዲ ቫንስን ስብሰባ በኋላ የመጀመሪያው ነው። ከዚያ በጩኸት የተሞላ ስብሰባ በኋላ አሜሪካ ለዩክሬን ትሰጥ የነበረውን ድጋፍ እና የደህንነት መረጃ አቁማለች።

ከጅዳው ስምምነት በኋላ የተቋረጠው ድጋፍ እና የደህንነት መረጃ ማጋራት የቀጠለ ሲሆን ትራምፕ “አስቸጋሪው” የዩክሬን ወገን እና ዜሌንስኪ አሁን ሰላም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚደረገው ድርድር እየተካሄደ ባለበት ጊዜ እንኳ በዩክሬን ጦርነቱ ተባብሷል።

የሩስያ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች የፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የትውልክ ከተማ የሆነችውን ክሪቪ ሪህን ዒላማ እንዳደረጉ ተዘግቧል። የወደብ ከተማዋ ኦዴሳ እንዲሁም ኒፕሮፔትሮቭስክ እና ካኪቭ ተባሉት ከተሞች የጥቃት ዒላማ እንደተደረጉ ተሰምቷል።

በሩስያዋ ክሩስክ ግዛትም የሚደረገው ግጭትም የቀጠለ ሲሆን የሩስያው ቃል አቀባይ ፔስኮቭ የሀገሪቱ ወታደሮች “ውጤታማ በሆነ መልኩ ወደፊት እየገፉ” እና በዩክሬን ኃይሎች የተያዙ አካባቢዎችን መልሰው እየተቆጣጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት ደግሞ በግዛቱ የሚገኝት ወታደራዊ ዕዝ ለመጎብኘት መጓዛቸውን ክሬምሊን አስታውቋል። ከክሬምሊን የወጡ የቪድዮ ምስሎች ፑቲን እና ወታደራዊ አዛዣቸው ቫሌሪ ገራሲሞቭ የውጊያ ጊዜ አልባሳትን ታጥቀው ሲራመዱ አሳይተዋል።

ፑቲን፤ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ዩክሬን ድንበር ተሻግራ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ በግዛቱ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

በጉብኝቱ ወቅትም የሩስያ ወታደሮች አካባቢውን “ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲያወጠዑ” ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የሩስያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ይሁንና ፑቲን እስካሁን ድረስ ማክሰኞ ዕለት ዩክሬን እና አሜሪካ የተስማሙበትን የተኩስ አቁም እቅድ በተመለከተ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ዩክሬን ሠራዊት ኃላፊ ኦሌክሳንደር ስርስኪ የተወሰኑ ወታደሮች ከክረስክ ለቅቀው እየወጡ መሆኑን ጠቁመዋል። ኃላፊው፤ የመልዕክት መለዋወጫ መተግባሪያ በሆነው ቴሌግራም ባሰፈቱት ፅሁፍ “በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ቅድሚያ ስሰጠው የነበረ እና እየሰጠሁ የምቀጥለው ጉዳይ የዩክሬናውያን ወታደሮችን ህይወት ማዳን ነው” ብለዋል።