
13 መጋቢት 2025, 12:56 EAT
ላለፉት ጥቂት ወራት በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች መካካል የነበረው ውጥረት ከቃላት መወራወር አልፎ በመሳሪያ ወደታገዘ ሁኔታ የአስተዳደር ተቋማትን መቆጣጠር ደረጃ ላይ ደርሷል።
በዶ/ር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ተሿሚዎች በመሻር የራሱን ኃላፊዎች መሾም ጀምሯል።
ይኸው ቡድን የአዲግራት ከንቲባ ቢሮን መያዙን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
አክለውም “ይህን ለማድረግ ያቀዱት አዲግራት ላይ ብቻ አይደለም መቀሌም ማድረግ ይፈልጋሉ ሌላ ቦታም ማድረግ ይፈልጋሉ” ብለዋል።
ከመንፈቅ በፊት ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች እና በአስተዳደሩ የተሾሙ ኃላፊዎች እንደማይወክሉት ገልጾ ነበር።
የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ባለፈው ዓመት መጨረሻ በተካሄደው 14ኛው የህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ሥራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ አስታውቀው ነበር።
ከዚሁ ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በቋጨው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ህወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የራሱ ያልሆኑ ሰዎችን አንስቶ የሚወክሉትን መመደብ እንደሚችል ተናግረዋል።
ከሁለት ወራት ገደማ በፊት ደግሞ በትግራይ ክልል ያሉ የወታደራዊ ኃይል አመራሮች በህወሓት ውሳኔ መሠረት “የተዳከመው” የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተነስቶ በሌላ እንዲዋቀር መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ወታደራዊ አመራሮቹ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የጊዜያዊ አስተዳደሩ “ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም፣ የሌሎች መጠቀሚያም ሆኗል” የሚል ክስ አቅርበዋል።
ከዚህ ውሳኔ ሁለት ወራት በኋላ አቶ ጌታቸው አራት የትግራይ ሠራዊት ወታደራዊ አዛዦችን በጊዘያዊነት አግደዋል።
የሠራዊት አመራሮችን ባገዱ ማግስት በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ “ውሳኔ” ያሉትን ተግባራዊ ለማድረግ “ሁሉንም እርምጃዎች” መውሰድ በመጀመራቸው እንደታገዱ ገልጸዋል።
“የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ሰብረው እየገቡ ነው፣ ጊዜያዊ የአስተዳደር ኃላፊዎችን እያነሱ ነው፣ ይህ ደግሞ በሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በይበልጥም በራሱ በሠራዊቱ ውስጥ ውዥንብር ፈጥሯል” ብለዋል።
“ጥያቄው ፕሬዝዳንቱን ወይም የካቢኔ አባላትን [ከሥልጣን] የማንሳት እና አለማንሳት አይደለም፤ ከሁሉም በላይ በፕሪቶሪያ ስምምነት የተገኘውን ትንሽ ሰላም የማስጠበቅ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ህወሓት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ “ህወሓት እና የትግራይ ሠራዊት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ባለቤቶች ናቸው” ብሏል።
መግለጫው አክሎም “በእግድ ስም የተጻፉት ደብዳቤዎች ከሥልጣን ውጪ የተደረጉ፣ ተቀባይነት እና ተፈጻሚነት የሌላቸው” መሆናቸውን ገልጿል።
- “ለምንድን ነው ከትግራይ የምሸሸው? . . . እመለሳለሁ” አቶ ጌታቸው ረዳ13 መጋቢት 2025
- መቀለ አቅራቢያ በምትገኘው አዲጉዶም ከተማ የተከሰተው ምንድን ነው?12 መጋቢት 2025
- አቶ ጌታቸው የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጣልቃ ለመግባት በቂ ምክንያት እንዳለው ተናገሩ12 መጋቢት 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ከሁለት ዓመት በፊት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካካል የተፈረመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት፤ “የጊዜያዊ አስተዳደሩ በሁለትም ወገኖች ፖለቲካዊ ምክክር” እንደሚቋቋም ያትታል።
ከስምምነቱ መፈረም ጥቂት ወራት በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ማቋቋሚያ ደንብ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
በደንቡ መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳደር የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ቢሮዎች፣ ተቋማት እና የሥራ ክፍሎችን የማደራጀት ሥልጣን እንዲሁም ተግባራቸውን የመወሰን ሥልጣን አለው።
ከዚህ በተጨማሪም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ለሚዋቀሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን “በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ውክልና በሚያረጋገጥ እና አካታች በሆነ መንገድ” መመልመል እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመመካከር ይሾማሉ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በበላይነት የማስተባበር እና የመምራት ኃላፊነትም በደንቡ ተሰጥቷቸዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳደር “አግባብነት ባላቸው ሕጎች” ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የተሰጡት ሥልጣን እና ተግባራት ይኖሩታል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳደር [በፕሪቶሪያ] የሰላም ስምምነት መሠረት በሚደረግ የፖለቲካ ምክክር ተለይቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሾም ደንቡ ላይ ሰፍሯል።
ከዚህ በተጨማሪም ርዕሰ መስተዳደሩ የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች በጊዜያዊነት በመመድን መደበኛ ሥራው እንዲቀጥል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ደንቡ ያትታል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል የተሰጡት ሥልጣን እና ተግባሮች ይኖሩታል። በተጨማሪም አስፈጻሚ አካሉን የመምራት የማስተባበር እና የክልሉን ዕቅድ እና በጀት የማጽደቅ ኃላፊነት አለው።
ከዚህ በተጨማሪ ከ22 ዓመታት በፊት የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገገድ በወጣው አዋጅ ለጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጡት ሥልጣኖች አሉት።
ከእነዚህ ሥልጣኖች መካከል “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን” መውሰድ አንደኛው ነው።
አሁን በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ቀውስጥ ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጥ አቶ ጌታቸው የጠየቁ ሲሆን፣ ነገር ግን ከቢቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህ ፍላጎት የፌደራሉን ኃይል ማሰማራት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በትግራይ በሕዝብ የተመረጠ ምክር ቤት ባለመኖሩ እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱም በክልሉ ጊዜያዊ መንግሥት አወቃቀር ሂደት ውስጥ ሚና ስላለው የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ለመጠየቅ የሚያስችል ሁኔታ የለም ብለዋል።