አቶ ጌታቸው ረዳ

13 መጋቢት 2025, 14:33 EAT

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ “ለራሱ የግል እና የቡድን ጥቅም ሲባል የሕዝብን ሠላም፣ የፕሪቶሪያን ስምምነት፣ የአገሪቱን መረጋጋት እንደ መያዣ ከተጠቀመ አካል” ጋር እንዳይደራደሩ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ጠየቁ።

በአሁኑ ወቅት “በትግራይ ውስጥ ከሚፈጠር ትርምስ እናተርፋለን” የሚሉ አካላት እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፤ “ከዚህም መካከል አንዱ የኤርትራ መንግሥት እንደሆነ አውቃለሁ” ብለዋል።

ክፍፍል ውስጥ በገቡት የህወሓት ክንፎች ምክንያት ቀውስ ውስጥ የገባውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚመሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ይህንን ያሉት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 4፤ 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

አቶ ጌታቸው፤ በሸራተን አዲስ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ እና ስላስከተለው ችግር ሰፊ ጊዜ ወስደው አስረድተዋል።

በአሁን ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋት “የሕግ ተቀባይነት ያጣ አንድ የህወሓት አንጃ ‘ጉባዔ አድርጌያለሁ’ ስላለ ‘ደጋፊ ናቸው’ የሚላቸውን የተወሰኑ ከፍተኛ መኮንኖች በመያዝ እየሰራቸው ያላቸው ስራዎች” ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ስርዓት ለማስያዝ በሚደረግ አንቅስቃሴ ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያለውን አቅም መጠቀም የሚያስችል ዕድል እየተነፈገ መምጣቱንም አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ይህ ቡድን የወረዳ፣ የቀበሌ እና የከተማ ከንቲባዎችን “ማህተም እየቀማ” መሆኑንም በመግለጽ ከስሰዋል።

በክልሉ “መፈንቅለ መንግሥት” እየተፈጸመ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ ይህንን ድርጊት የሚያከናውኑ አካላት የርዕሰ መስተዳደርነት ስልጣንንን ለመቀበል ከፌደራል መንግሥት ጋር “ድርድር ለማድረግ” ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ይችላሉ የሚል ግምታቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው፤ “ምርጫ ቦርድ ‘አላውቅህም፤ ያደረከውን ጉባኤ አልቀበልም’ ብሎት ግን ምርጫ ቦርድ ‘ያልከኝን አልቀበልም፤ ስለዚህ ምርጫ አድርጌያለሁ’ ብሎ፤ የወረዳ ማህተም፣ የቀበሌ ማህተም አሁን የከተሞች ከንቲባዎችን ማህተም እየለቀመ የሚውል ኃይል፤ ኮስተር ብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ‘ልደራደር ነው’ ብሎ ይመጣል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ ዓይነቱ አካሄድ “ግራ እንደሚያጋባቸው” የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ “ትንሽ ማፈር የሚቻልበት ሁኔታ ቢፈጠር፤ ይህንን የማፈር ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደንብ ፈር ቢያስይዙት ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል። አቶ ጌታቸው፤ ይህንን አጋጣሚም “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመገሰፅ” መጠቀም እንደሚፈልጉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ሰላም ለመፍጠር ሲባል ከሁሉም ጋር መደራደር እንዳለባቸው ይገባኛል። ጊዜያዊ አስተዳደሩን በአደባባይ አላውቅም ብሎ፤ በስርዓት የተሾመን ፕሬዝዳንት ‘የቀድሞ ፕሬዝዳንት’ እያለ፤ ከተማ ውስጥ የመንግሥትን በጀት እየተጠቀመ የሚያምስን ኃይል በምን አይነት መልኩ ነው እንደ ተደራዳሪ ተቀብለህ ልታየው የምትችለው?” ሲሉም ጠይቀዋል።

“ለራሱ የግል ጥቅም፣ የቡድን ጥቅም ሲባል የሕዝብን ሠላም፣ የፕሪቶሪያን ስምምነት፣ የአገሪቱን መረጋጋት እንደ መያዣ ይዞ ከረባት አስሮ እንደገና ለመደራደር” የሚመጣ አካል እንደሚኖር አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ “ምናልባት ዛሬ ከሰዓት በኋላ መጥተው ‘ማህተም ስለነጠቅን መንግሥት እንድንሆን ፍቀድልን’ እንደሚሉ ፍጹም እንዳትጠራጠሩ” ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“እንደዚህ ዓይነቱን ነውራም ተግባር አለማስተናገድ መጀመርም የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት አንዱ መገለጫ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ” ሲሉም መንግሥት ይህንን ጥያቄ እንደማይቀበል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው በዛሬው መግለጫቸው፤ የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባ በይፋ አለመጠየቃቸውን ተናግረዋል። “በካቢኔ ደረጃ ተሰብስብን የፌደራል መንግሥቱ ወደ ትግራይ ይግባ ብለን አልጠየቅንም፤ መጠየቅም አያስፈልገንም” ብለዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ይህ ጥያቄ ያልቀረበበት አንዱ ምክንያት “ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፌደራል መንግሥቱ አካል” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።

“የፌደራል መንግሥቱ በጋራ ከሌላ ፓርቲ ጋር በመሆን የመሰረተው አስተዳደር አደጋ ላይ ሲወድቅ መከላከል አለበት” ሲሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተመሰረተው የፌደራል መንግሥት ተሳታፊ በሆነበት የፕሪቶሪያ ስምምነት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ያለው የመንግሥት አወቃቀር ከሌሎች ክልሎች የተለየ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በመደበኛው አሰራር ክልሎች ፌደራል መንግሥትን ጣልቃ ገብነት የሚጠይቁት በምክር ቤት ወስነው መሆኑን ጠቅሰዋል።

“[በትግራይ ክልል] የፌደራል መንግሥትን ጣልቃ እንዲገባ የሚጠይቅ ምክር ቤትም የለም፤ የሚያስችልም ቁመና የለም” ያሉት አቶ ጌታቸው “ፌደራል መንግሥቱ ክልሉ ስጋት ላይ ነው ብሎ ካመነ ግን የእኛን ጥያቄ መጠበቅ አያስፈልገውም” ብለዋል።

እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር፤ ዋነኛ ኃላፊነታቸው በክልሉ ጦርነትን ማስቀረት መሆኑን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ “ኑ እንግጠም እያለ የሚፎክረውን አካል አደብ ለማስገዛት የፌደራል መንግሥቱ መግለጫ መስጠትም ሌሎች ከዚያ በላይ መሄድ ያለባቸው እንቅስቃሴዎች ካሉ የእኔ ግብዣ ያስፈልገዋል የሚል እምነት የለኝም” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው፤ በዚህ ወቅት የፌደራል መንግሥቱ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያነሱት ሀሳብ “ጦር ያዝምት” ማለታቸው እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ “ወደ ጦርነት ለማምራት እያንዣበቡ ያሉትን ሂደቶች ለማስቀረት ሁሉንም ዓይነት እርምጃዎች መውሰድ አለበት ብለን እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል የሚከሰት አለመረጋጋት ክልሉን ብቻ ሳይሆን “የአገሪቱን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ የመጣል አቅም” እንዳለውም አስጠንቅቀዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ እና ዶ/ር ደብረፀዮን ገብረሚካኤል

የትግራይ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ማሳለፉን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው ከማንም በላይ ሠላም የሚያስፈልገው ክልል ነው ብለዋል።

“በጦርነት ትርፍ እናገኛለን የሚል የተወሰነ በጥቅም የተሳሰረ ኃይል” የትግራይ ሕዝብን ሰላም “አደፍርሷል” በማለት ከስሰዋል።

“በኢትዮጵያ መንግሥትም ላይ ይሁን በትግራይ ሕዝብ ላይ የቆየ ቂም ያለው ሁሉ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ የትግራይን ሕዝብ ወደ ባሰ መከራ ሊያስገባ የሚችልበት ርብርብ እያደረገ ይገኛል፤ በተግባር የሚታይ እንቅስቃሴ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

“በትግራይ ውስጥ ከሚፈጠር ትርምስ እናተርፋለን” የሚሉ አካላት እንዳሉ በመግለጫው የጠቀሱ ሲሆን “ከዚህም መካከል አንዱ የኤርትራ መንግሥት እንደሆነ አውቃለሁ” ሲሉ ከስሰዋል።

“በተወሰነ ደረጃ እዚህ ትርምስ ውስጥ እንድንገባ በማድረግ ረገድ ይህንን ቡድን [የኤርትራ መንግሥት] ለመጠቀም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉ አውቃለሁ” ብለዋል።

የኤርትራ መንግሥት “ፖለቲካችንን ከማመስ አንጻር አስተዋጽኦ ብቻ ሳይሆን በተግባር ክልላችንን የጦርነት ቀጠና ለማድረግ ያለው እድል እየሰፋ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው” ብለዋል።

ክልሉ በፍፁም ጦርነት ማስተናገድ እንደማይችል የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የክልሉ ወጣት “ለእንደዚህ ዓይነቱ ርካሽ ተግባር ዝግጁ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

“በርግጠኝነት መናገር የምችለው የትግራይ ወጣት ሊዋጋ የሚችለው በሌላ አካል ጦርነት ከታወጀ ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ የእገሌን ወንበር ለማዳን ብሎ መስዋዕት የሚሆን ወጣት የለም ብለዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የክልሉ “ሕዝብ ሰላምን ስለሚፈልግ” እርሳቸውን እንደሚደግፍ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “ወጣቱ ሠላምን ስለሚፈልግ 90 በመቶ ሕዝብ እኔን እና መስተዳድሩን ይደግፋል” ሲሉ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።