ፍራፍሬ፣ ጫማ፣ ሜትር እና ውሃ

ከ 5 ሰአት በፊት

ኢንሱሊን በሰውነት ውስጥ ጠቃሚ ከሆኑ ሆርሞኖች አንዱ ነው።

የሰውነትን የስኳር (ጉሉኮስ) መጠን በማስተካከል፣ ሰውነታችን ስኳርን የሚያከማችበትን እና ኃይል የሚያመነጭበትን መንገድ ይወስናል።

ጣፊያ የሚያመነጨው የኢንሱሊን መጠን በጣም ያነሰ ከሆነ አልያም ሰውነት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ካልቻለ የጤና እክል ይከሰታል።

‘ኢንሱሊን ሬዚስታንስ’ ሲባል በተደጋጋሚ ሰምተው ይሆናል። በአማርኛ ኢንሱሊን መላመድ ብለው የሚተረጉሙት ባለሙያዎች አሉ።

እንዴት ማስወገድ ይቻላል? የሚለውን በተመለከተም የአመጋገብ ለውጥና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚመክሩ ተበራክተዋል።

ለመሆኑ ኢንሱሊን መላመድ ምንድን ነው? እንዴትስ መከላከል ይቻላል? የሚለውን እንመልከት።

ኢንሱሊን ሰውነት ውስጥ እንዴት ይሠራል?

ሰውነት ምግብን ወደ ጉሉኮስ ይለውጣል። ይህም አቅም የምናገኝበት ዋነኛው መንገድ ነው።

ጉሉኮስ በደም ሕዋሳት ውስጥ ይገባና ጣፊያ ኢንሱሊን እንዲለቅ መልዕክት ያስተላልፋል። ከዚያም ኢንሱሊን በደም ውስጥ ያለው ጉሉኮስ በጡንቻ፣ በስብ እና በጉበት ውስጥ እንዲገባ ይረዳል። ይህም ኃይል ለማመንጨትና ኋላ ላይ ጥቅም ላይ የሚውል አቅም ለማከማቸት ይረዳል።

ጉሉኮስ የደም ሕዋስ ውስጥ ገብቶ በደም ውስጥ ያለው መጠን ሲቀንስ ጣፊያ ኢንሱሊን ማምረት እንዲያቆም መልዕክት ይተላለፋል።

ኢንሱሊን በደማችን ውስጥ ያለውን የግሉኮስ መጠን ይቆጣጠራል
የምስሉ መግለጫ,ኢንሱሊን በደማችን ውስጥ ያለውን የግሉኮስ መጠን ይቆጣጠራል

ኢንሱሊን መላመድ ምንድን ነው?

በጡንቻ፣ በስብ እና በጉበት ውስጥ ያሉ ሕዋሳት ለኢንሱሊን መስጠት ያለባቸውን ምላሽ ሲያስተጓጉሉ ኢንሱሊን መላመድ ተፈጥሯል ማለት ነው።

ከደም ውስጥ ጉሉኮስ ወስዶ ማከማቸት እንዲሳናቸው ያደርጋል።

በዚህ ወቅት በደም ውስጥ ካለው የተበራከተ የጉሉኮስ መጠን ጋር የሚመጣጠን ኢንሱሊን ጣፊያ ማምረት ይጀምራል። ይህም hyperinsulinemia በመባል ይታወቃል።

በቂ ኢንሱሊን ከተመረተ የደም ስኳር መጠን ጤናማ ሆኖ ይቀጥላል። ለኢንሱሊን የሚሰጠው ምላሽ ደካማ ሲሆን ግን በደም ውስጥ ያለው የጉልኮስ መጠን ይጨምራል።

ይህም ዓይነት 2 የሚባለውን የስኳር ሕመም ጨምሮ ሌሎችም ሕመሞች ያስከትላል።

የጤና ባለሙያው ፍራንክሊን ጆሴፍ እንደሚሉት፣ ኢንሱሊን ሬዚስታንስ በዘረ መል፣ በአኗኗር እና በአካባቢያዊ ሁኔታ የሚወሰን ውስብስብ ሁኔታ ነው።

ዋና ዋና ምክንያቶቹን እንዲህ ዘርዝረዋል፦

ፆም እና ኢንሱሊን መላመድ

ፕ/ር ዋሲም ሀኒፍ እንደሚሉት ስኳር ታማሚዎች ለመፆም ከመወሰናቸው አስቀድሞ ባለሙያ ማማከር አለባቸው።

“ስኳር ላለባቸው ሰዎች ፆም አደገኛ ሊሆን ይችላል” ይላሉ ባለሙያው።

ፕ/ር ፍራንክሊን እንደሚሉት፣ ዓይነት 2 የስኳር ሕመምና የኢንሱሊን መላመድ ላለባቸው ሰዎች የበለጠ ከባድ ይሆናል።

በፆም ወቅት አንዳንዶች የሰውነት ክብደት ወይም የሰውነት ስብ መቀነስ ሊገጥማቸው ይችላል።

የረመዳን ፆምን እንደ ምላሴ የሚጠቅሱት ባለሙያው፣ የኢንሱሊን መላመድ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በጤና ሁኔታ፣ በአመጋገብና እንቅስቃሴ ይወሰናል ይላሉ።

“ረመዳን እየፆሙ ያሉ ሰዎች የስኳርና የሰውነት ምግብ ማብላላት አቅምን መከታተል አለባቸው” ይላሉ ባለሙያው።

የሥነ ምግብ ባለሙያው ሪም አል-አብደላት ጤናማ አመጋገብ ማዳበር በፆም ወቅት ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ።

ዘለግ ላለ ሰዓት ከምግብ መታቀብ (Intermittent fasting) ለጤና ጠቀሜታ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ዶ/ር ኒቲን ካፑር እንደሚሉት ከምግብ ታቅቦ መቆየት ሰውነት ምግብ የሚፈጭበትን መንገድ በማስተካከል ረገድ ሚና ቢኖረውም በባለሙያ ምክር የተደገፈ መሆን አለበት።

አመጋገብን መለወጥ ወይም ከምግብ መታቀብ ምን ያህል ዘላቂነት አለው? የሚለውን መጠየቅ እንደሚያስፈልግም ባለሙያው ይመክራሉ።

“ዕድሜ ልካችሁን ልታደርጉት ትችላላችሁ? ካልሆነ ስታቋርጡት ወደቀደመው ሁኔታ ትመለሳላችሁ ማለት ነው” ይላሉ።

እአአ በ2015 የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው አንድ ቀን ተመግቦ በቀጣዩ ቀን ከምግብ መታቀብ ከመጠን በላይ ውፍረት በሌላቸው ሰዎች ላይ የኢንሱሊን መላመድ ላይ ለውጥ አሳይቷል።

የኢንሱሊን መላመድ ለስኳር ሕመም ሊያጋልጥ ይችላል

የኢንሱሊን መላመድ ምልክቶች

መጀመሪያ ላይ ጉልህ ምልክት ላያሳይ ይችላል።

ከዚያም፤ ከፍተኛ ረሃብ፣ ድካም፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ አለመቻል፣ የቆዳ መጥቆር እና አንገት፣ ብብትና ብሽሽት አካባቢ ነጠብጣብ ማውጣት፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን እና ሌሎችም ምልክቶች ያሳያል።

ዓይነት 2 የስኳር ሕመም የሚያስከትለው የኢንሱሊን ሬዚስታንስ ቶሎ ቶሎ መሽናት፣ ውሃ መጠማትና የዕይታ መዛባትም ምልክቶቹ ናቸው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ምልክቶቹ ከሰው ሰው ይለያያሉ። አንዳንዶቹ ምልክቶች የሌላ ሕመም ስለሚሆኑም ሐኪም ማማከር ያሻል።

የኢንሱሊን መላመድን መቀልበስ ይቻላል?

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኢንሱሊን መላመድ ካለባቸው ሰዎች ከ70 እስከ 80 በመቶው ዓይነት 2 ስኳር ይይዛቸዋል። ይህም የሚከሰተው ሕመሙ ካልታከመ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ሆኖም ግን የዓይነት 2 የስኳር ሕመም ተጋላጭነት በአመጋገብ፣ በዕድሜና በዘር ይወሰናል።

“በደቡብ ምሥራቅ እስያ ያሉ ሰዎች የዓይነት 2 የስኳር ሕመም ተጋላጭነታቸው ከፍ ይላል” ሲሉ ፕ/ር ፍራንክሊን ይናገራሉ።

glycaemic index የተባለ መንገድ በመከተል የትኞቹ ምግቦች፣ በምን ያህል ፍጥነት የጉሉኮስ መጠን እንደሚጨምሩ ማወቅ ይቻላል።

በዝግታ የሚሰበሩ የካርቦሃይድሬት ዓይነቶች አነስተኛ ግላይሰሚክ ኢንዴክስ አላቸው።

እነዚህም አትክልትና ፍራፍሬ፣ ያልተብላላ ወተት እና ጥራጥሬን ይጨምራሉ።

ስኳርና ስኳር ነክ ምግቦችና መጠጦች፣ ድንችና ነጭ ሩዝ ከፍተኛ ግላይሰሚክ ኢንዴክስ አላቸው።

ፕ/ር ፍራንክሊን እንደሚሉት “ኢንሱሊን ሬዚስታንስ በአብዛኛው ሊቀለበስ ወይም በከፍተኛ ሁኔታ ሊሻሻል ይችላል”።

ይህን ማድረግ የሚቻለው አኗኗር በመለወጥና በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ መድኃኒት በመውሰድም ነው።

ጣፋጭና ስታርች መቀነስ በባለሙያዎች ይመከራል።

በተለይም ሆድ ላይ ያለን ስብና አጠቃላይ የሰውነት ስብን መቀነስ እንዲሁም አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም አስፈላጊ ነው።

ጭንቀትን ለማስወገድ እንደ ዮጋ እና ሜዲቴሽን ያሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግና አተነፋፈስን በማስተካከል የተሻለ ሕይወት መግፋትም ጠቃሚ ናቸው።

እንደ ሜትፎርሚን (Metformin) ያሉ መድኃኒቶች ከዓይነት 2 የስኳር ሕመም ጋር በተያያዘ ሁኔታ ውስጥ ለኢንሱሊን መላመድ ይወሰዳሉ። ሆኖም ግን ሐኪም አስቀድሞ ማማከር የግድ ነው።