
ከ 5 ሰአት በፊት
ከእስራኤል መጠነ ሰፊ ጥቃት በኋላ የሔዝቦላህ የድሮ ጥንካሬ ዛሬ የለም። ቡድኑ በብዙ መልኩ ተሽመድምዷል።
በሊባኖስ የነበረው ተሰሚነት ቀንሷል። አሁን የሊባኖስን ፖለቲካ እንዳሻው አይዘውርም።
ይሁንና ሔዝቦላህ አሁንም የሚናቅ ኃይል አይደለም።
በሊባኖስ ፓርላማ እና መንግሥት ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ የሺዓ ሙስሊም ፓርቲ ነው።
ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አለው።
የገንዘብ ምንጩ ግን ለብዙዎች ምሥጢር ነው። ቢቢሲ አረብኛ የሚጠረጠሩትን አንዳንዶቹን እንዲህ ዳስሷቸዋል።
700 ሚሊዮን ዶላር ከኢራን?
ሔዝቦላህ ስሙ እየገነነ የመጣው በአውሮፓውያኑ በ80ዎቹ ነው ።
በተለይ የሊባኖስን የእርስ በርስ ጦርነትን (1975-1990) ተከትሎ ወታደሮቹ ደቡባዊ ሊባኖስን መቆጣጠራቸው ሰፊ ድጋፍ አስገኝቶለታል።
ባለፈው ጥቅምት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ‘አልቀርድ አልሐሰን” (AQAH) የተሰኘውን የብድር እና የቁጠባ ባንክን በቦንብ ሲደበድብ ለብዙዎች ግራ መጋባትን ፈጥሮ ነበር።
ይህ የሊባኖስ የብድር እና የቁጠባ ባንክ ውስጥ ውስጡን የሔዝቦላህ ምሥጢራዊ የገንዘብ ዝውውር መሣሪያ መሆኑ በስፋት ይነገራል።
ቡድኑ በዚህ ባንክ ስም ገንዘብ ያስተላልፋል፣ ዶላር ይመነዝራል፣ የገንዘብ ዝውውርን ያሳልጣል በሚል ነው እስራኤል ዒላማ ያደረገችው።
‘አልቀርድ አልሐሰን’ የቁጠባ ባንክ ግን ይህን ያስተባብላል።
‘እኛ ለሊባኖሳውያን የፋይናንስ አቅርቦት ከመስጠት ውጪ የማንም አይደለንም’ ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለሁለት ወራት በዘለቀው የሔዝቦላህ እና የእስራኤል ፍጥጫ ከባድ ጥፋት ደርሷል።
በተለይ የሔዝቦላህ ይዞታ በሚባለው ደቡባዊ ሊባኖስ ከባድ የመሠረተ ልማት ውድመት ነው ያጋጠመው።
ይህ ጦርነት በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ በተኩስ አቁም ስምምነት ከተቋጨ በኋላም ሙሉ ሰላም አልመጣም።
ከዚህ የሰላም ስምምነት በኋላ ደግሞ የአሳድ አምባገነናዊ ሥርዓት ፍጻሜውን አገኘ።
ይህ ለሔዝቦላህ ሌላ ትልቅ ስብራትን የፈጠረ ሆነ።
በተለይ የጦር መሣሪያ አቅርቦቱ ከዚህ ወዲያ ትልቅ ፈተና ተደቅኖበታል። በሶሪያ የመሣሪያ ማከማቻ እና የሥልጠና ማዕከላት እንደነበሩት ነው የሚነገረው።
የገንዘብ እና የመሣሪያ ሽግግሩ በዚያ ድንበር ይበልጥ ቀላል እና ምቹ ነበር።
- ሊባኖስ የሚገኘው የእስራኤል ጠላት ሄዝቦላህ ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ?26 መስከረም 2024
- ሊባኖስን የሚመራው ማን ነው? ሄዝቦላህስ በአገሪቱ ውስጥ ምን ሥልጣን አለው?5 ጥቅምት 2024
- ሄዝቦላህ ሊባኖስ ውስጥ ምን ያህል ድጋፍ አለው? የሚቃወሙትስ አሉ?29 መስከረም 2024
ሆኖም ግን ሔዝቦላህ ኪሱን የሚያደልቡ በርካታ ቀዳዳዎች አሉት። የሶሪያ ድንበር ቢዘጋም ሌሎች መስመሮች ጨርሰው አልተዘጉበትም።
ከሁሉም የምትልቀው አጋሩ ግን ኢራን ናት።
እንደ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከሆነ ኢራን በየዓመቱ 700 ሚሊዮን ዶላር ለሔዝቦላህ ትበጅታለች።
ይህን ሔዝቦላህም ቢሆን የሚክደው አይደለም።
በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ሐሰን ናስራላህ በአንድ ወቅት በቴሌቪዥን በተሠራጨ ንግግራቸው ኢራን ዋና ለጋሻቸው እንደሆነች በኩራት ተናግረው ነበር፤ መጠኑን ባይጠቅሱም።
“በጀታችን፣ ደመወዛችን፣ ወጪያችን፣ ምግባችን፣ መሣሪያችን፣ ሚሳኤሎቻችን ከኢራን ናቸው” ብለዋል በዚያ ንግግራቸው።
ኢራን ይህን ሁሉ የምታቀርበው በብዙ መንገዶች ነው።
አንዱ መንገድ በእስላማዊ አብዮታዊ ዘቧ በኩል ነው። ድሮን እና ሚሳኤል የሚያቀርበውም ይኸው አብዮታዊ ዘብ ነው።
ምንም እንኳ የኢራንን ያህል ለሔዝቦላህ ስንቅም ትጥቅም የሚያቀርብ ባይኖርም፤ ሔዝቦላህ ሌሎች የገንዘብ ምንጮች የሉትም ማለት አይደለም።
በተለይ ኢራን በተጫናት ከባድ ማዕቀብ የተነሳ እንደ ቀድሞው ለሔዝቦላህ ስንቅ እና ትጥቅ እንደልብ ማቅረብ እየተቸገረች መጥታለች ይላሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አጥኚዎች።
የሚላከው የገንዘብ መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተመናምኗል።
በሔዝቦላህ ዙሪያ መጽሐፍ የጻፉት ማቲው ሌቪት እንደሚያስረዱት ከሆነ፤ በዚህ ወቅት ሔዝቦላህ ገንዘብ እያገኘ ያለው ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ በማድረግ ዘዴ (Money laundering) ነው።
‘አልቃርድ አል ሐሰን’ የብድር እና የቁጠባ ፋይናንስ
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በሔዝቦላህ ስም ገንዘብን ወደ ሕጋዊነት ‘የሚያጥበው’ ይህ አልቃርድ አልሐሰን የተሰኘ የብድር እና የቁጠባ ባንክ ነው የሚለው መረጃ በብዙዎች ይታመናል።
ይህ የብድር እና የቁጠባ ተቋም በሊባኖሳውያን ዘንድ በማኅበራዊ አገልግሎቱ ነው ይበልጥ የሚታወቀው።
እስራኤል የአየር ጥቃት ከመሰንዘሯ በፊት 30 ቅርንጫፎቹ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ብዙዎቹ ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ ከመኖሪያ ሕንጻዎች ሥር ነው የሚገኙት።
ማንኛውም ሊባኖሳዊ ከወለድ ነጻ አነስተኛ ብድር ከፈለገ ወደዚህ ተቋም ነው የሚሄደው። መያዣ ወርቅ እና ተያዥ ግለሰብ ይጠይቃል።
የቁጠባ ደብተር ይሰጣል።
በ2021 ሟቹ ሐሰን ናስራላህ ይህ ተቋም ከተመሠረተ ጀምሮ በድምሩ 37 ቢሊዮን ዶላር ለ2 ሚሊዮን ሊባኖሳውያን ብድር ማቅረቡን ገልጸው ነበር።
ጆሴፍ ደሐር ደራሲ እና ተመራማሪ ናቸው። “ይህ ባንክ ለትርፍ አልተቋቋመም። ዋናው ተግባሩ ለሔዝቦላህ ደጋፊዎች የገንዘብ አቅም በመፍጠር አቅማቸውን ማጠናከር ነው” ይላሉ።
ባንኩ ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት ሂደት ተሳትፎ እንዳለውም ይጠረጥራሉ።
እስራኤል የዚህን ተቋም ቅርንጫፎች ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ “የአሸባሪዎች የገንዘብ ምንጭ” ነበር ስትል አውግዛዋለች።
አሜሪካም በዚህ ተቋም ላይ ማዕቀብ ጥላለች። ዋናው ምክንያት ባንኩ የሔዝቦላህ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር መስመር ሆኖ ያገለግላል የሚል ነው።
ባንኩ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ክሶቹን ውድቅ አድርጓል።
የሚሰጠው አገልግሎትም ለማንም ያልወገነ እና ማኅበረሰቡን ለመጥቀም ነው ይላል።
ከኢራን ጋር “አንዳችም ግንኙነት የለኝም” ብሏል።
ተቋሙ ይህን ይበል እንጂ ስፓይደር-ዚ (SpiderZ) የተሰኘ መረጃ ጠላፊ ቡድን በፈረንጆቹ 2020 የዚህን ባንክ ቋት ሰብሮ ገብቶ የተበዳሪዎችን ስም ዝርዝርን ይፋ አድርጎ ነበር።
አንድ መቀመጫውን ዋሺንግተን ያደረገ ተቋም ይህን የተጠለፈ መረጃ መሠረት አድርጎ ባወጣው ዘገባ 400 ሺህ ስሞች ከሔዝቦላህ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የተሳሰሩ ናቸው ይላል።
ይህ ተቋም እንደሚለው ከሆነ ከስም ዝርዝሮቹ ውስጥ ‘ቫሊ አል ፋቂ’ የተሰኘው ስም ከኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኾሜኒ ቢሮ ጋር የተሳሰረ ነው።
ባንኩ በበኩሉ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ምንም ዓይነት የሐዋላ ሥራ ውስጥ እንደማይሳተፍ፣ ከውጭ አገር ምንም ዓይነት የገንዘብ ቅብብል እንደማያደርግ ይፋ አድርጓል።
“ማንኛውም ሊባኖሳዊ ከባንካችን መጠቀም ይችላል፤ ማንኛውም ግለሰብ ደግሞ ለበጎ ዓላማ የሚውል እርዳታን መለገስ ከፈለገ አንከለክልም” ብሏል።

አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ
ኤፍዲዲ የተባለው ተቋም በ2020 ባወጣው ሪፖርት ሔዝቦላህ ከሊባኖስ ውጪ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ የገንዘብ ምንጮች እንዳሉት አረጋግጫለሁ ብሏል።
እንደ ተቋሙ መረጃ ከሆነ ሔዝቦላህ በአፍሪካ ዋና የገንዘብ ምንጩ የአልማዝ እና የከበሩ ሥዕሎች ንግድ ነው።
በ2019 የአሜሪካ ግምጃ ቤት ውድ የሥዕል ውጤቶችን ሰብስቦ በመሸጥ የሚታወቀውን ናዚም ሰኢድ አሕመድን “ዋና የሔዝቦላህ ገንዘብ ለጋሽ” በሚል ማዕቀብ ጥሎበት ነበር።
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ናዚም ሰኢድ አሕመድ በሕገወጥ አልማዝ ንግድ ውስጥ እጁ አለበት ብሏል።
ይህ ግለሰብ አሁን የት እንዳለ አይታወቅም።
የአደጋኛ ዕጽ ዝውውር እና የክሪፕቶከረንሲ ንግድ

ሔዝቦላህ በደቡብ አሜሪካ ከአደገኛ ዕጽ ንግድ ዝውውር ጋር ስሙ ይነሳል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን ምርመራ ሪፖርት መሠረት በቬንዙዌላ የሚሊዮን ዶላር የአደገኛ ዕጽ ዝውውር ውስጥ ሔዝቦላህ እንደሚሳተፍ ይገልጻል።
ሔዝቦላህ ከዚህ ባሻገር ከኮሎምቢያ የፋርክ አማጺ ቡድን ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም ይላል፤ የተባበሩት መንግሥታት የወንጀል፣ የምርመራ እና የፍትህ ጥናት ኢኒስቲትዩት።
የአማጺ ቡድኑ አርጀንቲና-ብራዚል እና ፓራጓይ ድረስ የሚዘልቅ የአደገኛ ዕጽ ዝውውር ውስጥ ተሳትፎ አለው ይላል።
ባለፉት አሥርታት የአሜሪካ ግምጃ ቤት በእነዚህ አገራት የሚገኙ በርካታ ቢዝነሶች ላይ ማዕቀብ ጥሏል። ምክንያቱ ደግሞ ሔዝቦላህን ይደግፋሉ የሚል ነው።
በ2023 ማዕቀብ የተጣለበት ሐሰን ሙካሌድ የተባለ ሊባኖሳዊ፣ የአሜሪካ ማዕቀብ ፖለቲካዊ ግብ ያለው ነው ይላል።
ሔዝቦላህ ከዚህ ሌላ ቁጥጥር በማይደረግበት የበይነ መረብ የገንዘብ ዝውውር – ክሪፕቶከረንሲ ንግድ ውስጥም ተሳትፎ እንዳለው ይነገራል።
ያም ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የንግድ ኩባንያዎች በግዙፍ ጨረታዎች ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ከጀርባቸው ሔዝቦላህ እንዳለ ተደርሶበታል።
አንድ ሌላ ጥናት ደግሞ በሶሪያ ድንበር ከሚካሄድ የነዳጅ ዝውውር ጋር በተያያዘ ሔዝቦላህ በወር እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ትርፍ ያጋብሳል።
ይህ ግን የአሳድ መንግሥት ከመገርሰሱ በፊት የወጣ ሪፖርት ነው።