የመቀለ ከተማ

ከ 2 ሰአት በፊት

በደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የህወሓት ክንፍን የሚደግፉ የትግራይ ኃይል አባላት መቀለ ኤፍኤም 104́.4 እና የከተማዋን ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሐሙስ፣ መጋቢት 3/2017 ዓ.ም. ተቆጣጥረዋል።

በተመሳሳይም ይኸው የህወሓት ክንፍ ከዚህ ቀደም በከተማው ምክር ቤት ተመርጠዋል ያላቸውን ረዳኢ በርሔን (ዶ/ር ) ድጋሚ የከተማዋ ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።

በፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከዚህ ቀደም በሌላኛው የህወሓት ክንፍ የተሾሙትን ከንቲባ እንቅስቃሴ በማገድ አቶ ብርሐነ ገብረየሱስን የመቀለ ከንቲባ አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።

በሁለቱ የህወሓት ክንፎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ነዋሪዎች ያሏት መቀለ ያለ ከንቲባ እና ያለ ሕዝባዊ አገልግሎት ለአራት ወራት ቆይታለች።

በደብረ ፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍን የሚደግፉ የትግራይ ሠራዊት አዛዦች መሪነት በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች እና ወረዳዎች የሚገኙ የጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅሮችን በማፍረስ ጽህፈት ቤቶችን ተቆጣጥረዋል።

እንዲሁም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ተሹመው የነበሩ አመራሮችን በመተካት ላይ ይገኛሉ።እየተሾሙ ያሉት አመራሮች በትግራይ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ምርጫ ተካሂዶ የተቋቋመው ምክር ቤት የሾማቸው አመራሮች ናቸው።

ለሁለት ዓመት የዘለቀውን የትግራይን ጦርነት የቋጨው የሰላም ስምምነት ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ ተቀባይነት የለውም ባለው ምርጫ የተቋቋመው የትግራይ መንግሥት እንዲፈርስ ተደርጓል።

ሆኖም ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማቋቋም በፈጀው ስድስት ወራት ውስጥ ሕገወጥ በተባለው ምርጫ የተሾሙ አመራሮች የክልሉ ከተሞች እና ዞኖችን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል።

የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ የጊዜያዊ አስተዳዳደሩን መሪነት የተረከቡት አቶ ጌታቸው ረዳ አብዛኞቹን አመራሮች በማንሳት በራሳቸው ሾመዋል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ የከተማ እና የዞን አመራሮች ከመንግሥት ሥራ በበለጠ የፓርቲውን ተግባራት አስቀድመዋል በማለት በአዳዲስ አመራሮች መተካታቸውም ይታወሳል።

“እኔ በምክር ቤቱ የተሾምኩ ሕጋዊ ከንቲባ ነኝ። በመቀለ ከተማ እና በሌሎች ከተሞች ማቋቋሚያ አዋጅ 341 ማንኛውም ከንቲባን የሚሾመው አሸናፊው ፓርቲ ነው” ሲሉ አዲሱ የመቀለ ከንቲባ ረዳኢ በርሔ መናገራቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

“ሉዓላዊ ሥልጣን የሕዝብ መሆኑ እየታወቀ ይሄንን በመጣስ የከንቲባውን ጽህፈት ቤት በመዝጋት ሕዝብ አገልግሎት እንዳያገኝ ተደርጓል” ያሉት ከንቲባው “አሁን ግን በምክር ቤቱ የተመረጠው ከንቲባ ሥራውን በይፋ ጀምሯል” ሲሉ አስታውቀዋል።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት፤ ፓርቲው በሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል እና በምክትል ሊቀመንበሩ ጌታቸው ረዳ በሚመሩ ቡድኖች ተከፍሎ እየተወዛገበ ይገኛል።

ለወራት በገለልተኝነት ከቆዩት የትግራይ ሠራዊት አዛዦች መካከል አብዛኞቹ በደብረፂዮን ለሚመራው ወገን ድጋፍ መስጠታቸውን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ስጋት ተፈጥሯል።

በደብረዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ የተሾሙት አዲሱ የመቀለ ከንቲባ ረዳኢ በርሔ (ዶ/ር )
የምስሉ መግለጫ,በደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ የተሾሙት አዲሱ የመቀለ ከንቲባ ረዳኢ በርሔ (ዶ/ር )

“ሠራተኞች ግራ ተጋብተዋል”- የኤፍኤም መቀለ 104.4 ሠራተኞች

በሌላ በኩል ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራውን የህወሓት ክንፍን የሚደግፉ የትግራይ ኃይል አባላት በከተማዋ የሚገኘውን ኤፍኤም መቀለ 104.4ን ትናንት ሐሙስ መቆጣጠራቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል።

ትናንት ረፋድ ላይ የትግራይ ኃይል አባላት የሬድዮ ጣቢያውን በመቆጣጠር በደብረጽዮን በሚመራው የህወሓት ክንፍ የተሾመውን ኃላፊ እና አዲስ የአመራር ቦርድ በግዳጅ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በትግራይ ኃይሎች ታጅበው፤ በኃይል ሬድዮ ጣቢያውን ተቆጣጥረዋል። አሁን ሠራዊቱ የሬድዮ ጣቢያውን እየጠበቀው ነው፤ ሠራተኞች ግራ ተጋብተዋል” ብለዋል።

ቀደም ሲል ጣቢያውን መምራት አለብኝ ሲሉ የነበሩት አቶ ዘመንፈስ ፍስሐ እና አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከታጣቂዎች ጋር መምጣታቸውን ሠራተኞቹ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን መተዳደሪያ ደንብ የሚንቀሳቀሰው ኤፍኤም መቀለ 104.4 በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ፈቃድ ከተሰጠው 16 ዓመታትን አስቆጥሯል።

ባለፈው ጥር መጨረሻ ላይ የትግራይ ኃይል አባላት የሬድዮ ጣቢያውን ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጋቸው መገለጹ ይታወሳል።

በወቅቱ በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ በምክር ቤቱ ተሹመዋል ያሏቸው የከተማዋ ከንቲባ ዶ/ር ረዳኢ፣ አቶ ዘመንፈስ ፍስሓን የሬድዮ ጣቢያው ኃላፊ እንዲሆኑ ሾመዋቸው ነበር።

ነገር ግን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በከንቲባነት ተሹሜያለሁ ያሉትን ዶ/ር ረዳኢ በማገድ ብርሓነ ገብረየሱስን በምትካቸው መሾማቸው ይታወሳል።

በመሆኑም የትግራይ ኃይል አባላት የሬድዮ ጣቢያውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቶ ነበር።

የመቀለ ሬድዮ ጣቢያ

ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የትግራይ ኃይል አባላት የሬድዮ ጣቢያውን የተቆጣጠሩት በመደበኛነት ሥርጭቱን እያስተላለፈ በነበረበት ወቅት ነው።

“በአሁኑ ወቅት ቀድመው የተዘጋጁ ፕሮግራሞች እየተላለፉ ነው። ምንም ዓይነት የቀጥታ ፕሮግራሞች የሉም። ከሠራተኞች ጋር ስብሰባ እንደሚካሄድ ነግረውናል” ሲሉ የጣቢያው ሠራተኞች ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የትግራይ ሠራዊት አዛዦች ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለተካሄደው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ ዕውቅና በመስጠት በድርጅቱ ሊቀመንበር የሚመራው የህወሓት ቡድን ከዚህ ቀደም ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፉ የገለጹ ሲሆን፣ ይህም አጋርነታቸው በዶ/ር ደብረፂዮን ለሚመራው ቡድን መሆኑን አመልክቷል።

አዛዦቹ በቅርቡ ባወጡት መግለጫ በጉባኤው ውሳኔ መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በአዲስ እንዲዋቀር ወስነናል ያሉት የትግራይ ሠራዊት አዛዦች “መፈንቅለ መንግሥት አውጀዋል” ሲል የፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጽህፈት ቤት መክሰሱ ይታወሳል።

ውጥረቱ እዚህ እንዴት ደረሰ?

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋዊ ኤክስ ገጻቸው ላይ በአዲጉዶም ከተማ እና በመቀለ አንዳንድ አካባቢዎች የትግራይ ኃይል አዛዦች ማክሰኞ፣ መጋቢት 2/2017 ዓ.ም በሰላማዊ ሰዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ በርካቶች መቁሰላቸውን አስፍረዋል።

ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድንን የሚደግፉ የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ አዛዦች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እየተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በእነርሱ የተሾሙ ግለሰቦችም በኃይል ቢሮዎችን እየተቆጣጠሩ ነው።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የፌደራል መንግሥት በክልሉ ጣልቃ መግባትን ጨምሮ “የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ” በቂ ምክንያት እንዳለው ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ የመንግሥትን መዋቅር አፍርሰዋል በሚል ሦስት የሠራዊት አዛዦችን ያገዱ ሲሆን፣ በሌ/ጄኔራል ፍስሃ ኪዳኑ (ፍስሃ ማንጁስ) የሚመራው የትግራይ ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ውሳኔውን እንደማይቀበል ካሳወቀ በኋላ የቢሮ ኃላፊውም በተመሳሳይ ዕግድ ተጥሎባቸዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ለራሱ የግል እና የቡድን ጥቅም ሲባል የሕዝብን ሠላም፣ የፕሪቶሪያን ስምምነት፣ የአገሪቱን መረጋጋት እንደ መያዣ ከተጠቀመ አካልጋር እንዳይደራደሩ” ሲሉ በትናንትናው ዕለት በሸራተን ሆቴል ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠይቀዋል።

የትግራይ ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ በበኩሉ “በራሳችን አቅም ሊፈቱ የሚችሉ የውስጥ እና የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ሦስተኛ ወገን መጋበዝ አሳፋሪ ነው” በማለት በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።

“በዚህ ረገድ የትኛውም የኃይል እንቅስቃሴ ችግሩ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲሸጋገር እና እንዲባባስ ያደርጋል” ያለው መግለጫው “ሕዝቡም ደስተኛ እንደማይሆን” መግለጫው አክሎ ገልጿል።

በትግራይ ለወራት የቆየው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ያለው ውጥረት እና ፍጥጫ ከሁለቱ ዓመት የደም አፋሳሽ ጦርነት ባላገገመው ሕዘብ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።