ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ከ 4 ሰአት በፊት

የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር እንዲደረስ የታቀደውን የተኩስ አቁም ሃሳብ እንደሚስማሙበት ቢገልጹም፤ በርካታ “ጥያቄዎች” የጫሩ ከባድ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ የሰጡት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር ባደረገችው ውይይት የቀረበውን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ዕቅድ መቀበሏን ተከትሎ ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በዕቅዱ ዙሪያ ፑቲን የሰጡትን ምላሽ “የማይጨበጥ” ከማለት ባለፈ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ በሩሲያ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የባንክ ዘርፎች ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥላለች።

ፑቲን ሐሙስ ዕለት በሞስኮ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተኩስ አቁም ሃሳቡን “ትክክለኛ ሲሆን እኛም እንደግፈዋለን። ነገር ግን ልንወያይባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች አሉ” ብለዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ወደ ዘላቂ ሠላም ሊያመራ እና የዚህን ቀውስ መንስኤ ማስወገድ ሊኖርበት ይገባል ብለዋል ፑቲን።

“ከአሜሪካውያን አጋሮቻችን ጋር መደራደር አለብን። ምናልባትም ወደ ዶናልድ ትራምፕ ስልክ እደውላለሁ” ብለዋል።

“ለዩክሬን ወገን ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉ ጥሩ ነው” ሲሉ ፑቲን አክለዋል።

“እኛ ብንደግፈውም ግን ልዩነቶች አሉን።” ብለዋል።

ዩክሬን ባለፈው ዓመት ወታደራዊ ዘመቻ በማድረግ የተወሰነ አካባቢ የተቆጣጠረቸበት የኩርስክ ግዛት አንደኛው ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን ፑቲን ተናግረዋል።

ሩሲያ ኩርስክን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራለች ከማለት ባለፈ በስፍራው ያሉት የዩክሬን ወታደሮች “ተቆራርጠዋል” ብለዋል።

“ለመውጣት እየሞከሩ ቢሆንም እኛ ግን ተቆጣጥረናል። መሳሪያቸውን በየቦታው ጥለዋል።”

“ኩርስክ ውስጥ ለዩክሬናውያን ሁለት አማራጮች ብቻ አሉ፤ እጅ መስጠት ወይም መሞት” ብለዋል።

ፑቲን የተኩስ አቁም እንዴት እንደሚሠራ የቀረቡ አንዳንድ ጥያቄዎችን ሲገልጹም “እነዚያ 30 ቀናት እንዴት ጥቅም ላይ ይውላሉ? ዩክሬን እንድትደራጅ ነው? እንድታጠቅ ነው? ሰዎችን ለማሰልጠን ነው? ወይስ እነዚህ ነገሮች አይሆኑም? እንዴትስ ቁጥጥር ይደረግበታል?” ሲሉ ጠይቀዋል።

“ትግሉ እንዲቆም ማነው ትዕዛዙን የሚሰጠው? ምን ዋጋስ ያከፍላል? ከሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በሚሆን ስፍራ ማን የተኩስ አቁሙን እንዳፈረሰ ማን ነው የሚወስነው? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ከሁለቱም ወገን ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ይጠይቃሉ። ማንስ ይቆጣጠረዋል?” ሲሉ በርካታ ጥያቄዎችን ወርውረዋል።

ፑቲን “በቀጥታ አልቀበለውም አላለም” ነገር ግን “በተግባር ውድቅ ለማድረግ እያዘጋጀ ነው” ሲሉ ዘለንስኪ በምሽት በሚያስተላልፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው ላይ ተናግረዋል።

“ፑቲን በእርግጥ ይህን ጦርነት መቀጠል እና ዩክሬናውያንን መግደል እንደሚፈልግ በቀጥታ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ለመናገር ይፈራል።” ሲሉ ዜሌንስኪ ተችተዋል።

የሩስያው መሪ ብዙ “ምንም የማይሠራ” በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል ሲሉ ዜለንስኪ ተናግረዋል።

ከፑቲን አስተያየት እና ከዜለንስኪ ምላሽ በኋላ በሁለቱም ወገኖች አቋም መካከል ግልጽ የሆነ መለያየት መኖሩ ታይቷል።

ዩክሬን ባለ ሁለት ሂደት እንዲኖር ትፈልጋለች፤ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እና ቀጥሎም የረጅም ጊዜ እልባት እንዲኖር።

ሩሲያ በበኩሏ ሁለቱን ሂደቶች መለየት እንደማትችል ከመግለጽ ባለፈ ሁሉንም ጉዳዮች በአንድ ስምምነት ውስጥ መወሰን አለባቸው የሚል አቋም አላት። ሁለቱም ወገኖች አቋማቸውን ለማንጸባረቅ የቆረጡ ይመስላሉ።

ሩሲያን ለሠላም ጥሪው እምቢተኛ እንደሆነች አድርጋ በማቅረብ ዩክሬን በሩስያ ላይ ጫና እንደምትፈጥር ታምናለች። ሩሲያ፣ በበኩሏ ስለኔቶ መስፋፋት እና ስለዩክሬን ሉዓላዊነት ያሏትን መሰረታዊ ስጋቶቿን ለማቅረብ አሁን ዕድል እንዳላት ታምናለች።

ይህ ደግሞ ለዶናልድ ትራምፕ ችግር ይፈጥራል። አፋጣኝ ውጤት እንደሚፈልጉ ግልጽ በማድረግ ጦርነቱን በቀናት ውስጥ ለማቆም ቃል ገብተዋል።

ፑቲን በዚህ መልኩ ለመንቀሳቀስ የሚፈልጉ አይመስልም።

ፕሬዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፑቲንን አስተያየት ተከትሎ በዋይት ሃውስ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ከሩሲያው መሪ ጋር ለመገናኘት “እንደሚፈልጉ” እና ለ30 ቀናት የሠላም ስምምነቱ ሩሲያ “ትክክለኛውን ነገር ታደርጋለች” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

“ከሩሲያ የተኩስ አቁምን ማየት እንፈልጋለን” ብለዋል።

ቀደም ብለው ከኔቶ ዋና ጸኃፊ ማርክ ሩት ጋር በኦቫል ኦፊስ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ቀደም ሲል ከዩክሬን ጋር በዝርዝር ጉዳዮች መወያየታቸውን ትራምፕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“ከዩክሬን ግዛት ስለሚጠበቁ እና ስለሚነጠቁት እንዲሁም ደግሞ ስለሌሎች የመጨረሻ ስምምነቱ ጉዳዮች እየተነጋገርን ነበር” ብለዋል።

“የመጨረሻ ስምምነት ብዙ ዝርዝሮች ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።”

ዩክሬን ኔቶ ስለመቀላቀልበት ጉዳይ ትራምፕ በሰጡት አስተያየት “መልሱ ምን እንደሆነ ሁሉም ሰው ያውቀዋል” ብለዋል።

በሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ ላይ የተጣለው አዲስ ማዕቀብ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካን የክፍያ ስርዓት የበለጠ በመገደብ ለሌሎች አገራት የሩሲያን ነዳጅ መግዛት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው አድርገዋል።

በሌላ በኩል ፑቲን ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በሞስኮ በዝግ መክረዋል።

ቀደም ብሎ የክሬምሊን ረዳት ዩሪ ኡሻኮቭ በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ሃሳብ ውድቅ አድርገውታል።

ረቡዕ ዕለት ክሬምሊን ፑቲን በወታደራዊ ልብስ የሩስያን ኩርስክ ግዛት ሲጎበኙ የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቷል። ሩሲያ ቁልፍ የሆነችውን የሹድዛ ከተማን መልሳ መያዟን አስታውቃለች።