March 7, 2025

 ነፃ አስተያየቶች

ቀን የካቲት 2017
በአንዳርጋቸው ጽጌ

  1. ከአጻጻፍና ከይዘት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች

ሀ) የቅርጽ ጉዳይ

የማንበብ ባህል እየተዳከመ መጥቷል። በመሆኑም ሰፊ ትንታኔ የሚጠይቁ ጉዳዮችን በአጭሩ ጨምቆ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ተረድቻለሁ። የአማራ ህዝብ የሚገኝበት ሃገረ ኢትዮጵያና፣ ሃገረ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና ከየትኛው አካባቢ የበለጠ የተወሳሰቡ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ችግሮች ያሉበት ነው። በዛ ላይ እየተወሳሰበ የመጣው የቅርብና የሩቅ መንግስታትና ሃገራት እንዲሁም የአለም አቀፍ ኩባንያዎች ጂኦ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት የቀጠናውን ችግር በማባባስ የሚጫወተው ሚና አለ። እንዲህ አይነት የተወሳሰቡ ሃገራዊ፣ ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ተጽእኖዎች ባሉበት አካባቢ የአማራ ህዝብ የሚያደርገውን የህልውና ትግል በሚገባ ለመተንተን እንኳን ረጃጃም ጽሁፎች አይደለም የዳጎሱ መጽሃፍትም ቅም የሚሉት አይደለም።

ችግሩ ግን በሚገባ ያልተማረው ብቻ ሳይሆን የተማረ የምንለውም፣ መጽሃፍ አይደለም ረጃጃም ጽሁፎችን ማንበብ ካቆመ ቆይቷል። ቀደም ብሎም ቢሆን ማንበብ መጻፍ የማይሆንለት የኢትዮጵያ ሆነ የአማራ ምሁር፣ እድሜ ለማህበራዊ ሚድያ መጻፉንም ማንበቡን እርግፍ አድርጎ ትቶታል።

ምሁሩ ሳይቀር ከሙያው ውጭ የቀረችውን የማወቅ ፍላጎት የሚያረካው ዘመን ያመጣቸውን የተግባቦት መሳሪያዎች ከድንቁርና በመጣ ድፍረት ተቆጣጥረው ያሻቸውን የሚናገሩበትን የዩትዩብ፣ የቲክቶክ የትዊተር፣ የፊስቡክና የኢንስተግራም ሸቃጮችን በማዳመጥ ሆኗል። ይህ ሁኔታ፣ እጅግ አደገኛ የሆነ ከእውቀት የተጣላ በስሜት የሚነዳ፣ የግብስብስ መረጃዎች ሱሰኛ (የጃንክ መረጃዎች ጃንኪ a junkie for junk information ) ፈጥሯል። ይህን ባህል ግምት ውስጥ በማስገባትና ፈረንጆቹ “ለአሮጌ ውሻ አዲስ ትሪክ ማስተማር አይቻልም” የሚሉትንም ብሂል በመጋፋት እኔም በተቻለ መጠን የወቅቱን የአማራ ህዝብ የህልውና አደጋ ምልከታዎቼን የራሳቸው አርስት ባላቸው አጫጭር ጽሁፎች አማካይነት ለማቅረብ ተገድጃለሁ።

ለ) ጽሁፍ ለማን የተጻፈ ነው?

ይህ ጽሁፍ የተጻፈው በአማሮች መሃከል መደረግ ለሚገባው ውይይት ነው። የታሪክና የግል ህይወት ምጸት በሚመስል መልኩ እነዚህን ቃላቶች የዛሬ 32 አመት “ የአማራ ህዝብ ከየት ወዴት” በሚል ርእስ ባሳተምኳት ትንሽ መጣጥፍ ውስጥ መገኘታቸው አስገርሞኛል። በገጽ 5 መጨረሻ ላይ” የዚህ ጽሁፍ አላማ አንድና አንድ ብቻ ነው። ዛሬ በሃገራችን ውስጥ ባለው ሁኔታ በተለይም የአማራውን ህዝብ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በአማራውና በአማራው ውስጥ ብቻ መደረግ ላላበት ውይይት የራሳችንን መንደርደሪያ ሃሳቦች ለማቅረብ ነው” ይላል። በዚህ ጽሁፍ ላይ አማራ ያልሆኑ አስተያየት ቢሰጡበት ማስቆም አይቻልም። በበኩሌ ከጽሁፉ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ካሉ ምላሽ የምሰጠው ከአማሮች ለሚመጡት ብቻ ነው።

አማሮች ስል በአማራ ፋኖ የሚመራው የአማራን የህልውና ትግል ፍትሃዊ ነው ብሎ የሚያምን ማንኛውም ሰው ማለቴ ነው። እንዲህ ከሆነ ማኛውም ኢትዮጵያዊ የአማራን የህልውና ትግል ፍትሃዊነት ከተቀበለ አማራ ነው። የአማራ ቁስል ቁስሌ፣ ህመሙ ህመሜ ነው በማለት በድርጊቱ እኔም አማራ ነኝ እያለን ስለሆነ። እንዲህ አይነቱ ግለሰብ ጥያቄ ቢጠይቀኝ ለመመለስ ቢሞግተኝ ለመሞገት ዝግጁ ነኝ። ከዚህ ውጭ አንድ ግለሰብ ዘርማንዘሩ እስከምንጅላቱ አማራ መሆኑን ሊቆጥር ይችላል። በድርጊት ግን እንደ ዳንኤል ክብረት፣ ዳኛቸው አሰፋ፣ በለጠ ሞላ፣ አረጋ ከበደ፣ ተመስገን ጥሩነህ፣ አገኘሁ ተሻገር፣ ብናልፍ አንዱ አለም እና ሌሎችም የንጉስ አብይ አህመድ የቤተ መንግስት ባሪያ ሆኖ እስከመጣ ድረስ አማራ ሊሆን አይችልም። በእንዲህ አይነቱ ፍጥረት ለመጠየቅም ወይም ለመሞገትም ፈቃደኛ አይደለሁም።

ንጉስ አብይ ባቋቋማቸው፣ ለሆዳቸው ባደሩ ባሪያ የሚድያ ጄነራሎቹም በሚመሩ የማህበራዊ ሚድያዎችና ሰራዊቶቻቸውም ለመጠይቅ ፈቃደኛ አይደለሁም። ይህ ጽሁፍ በዋንኛነት ማንን ቀንድ ሊያስበቅል እንደሚችል ሰለማውቅ የኦሮሞ ብልጽግና የሚድያ ሰራዊት እና ጸረ አማራና ኢትዮጵያ ሃይሎች የአማራ ስም እየተጠቅሙ ዘመቻ እንደሚከፍቱበት ግልጽ ነው።

እንደተለመደው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ደግሞ የአማራ ህዝብ “ደሃ እንጂ ደደብ አይደለም” በሚል የህዝብ መተማመን ላይ ቆሜ እውነትን በድፍረት መጻፍ ግድ የሚል ሆኖ አግኝቸዋለሁ ።

በበኩሌ የዚህን ጽሁፍ ጉዳይ “በአማሮችና በአማራ ወዳጆች መሃል ለሚደረግ ውይይት” በሚል ያጠርኩት ከማንም ለሚነሳ ማናቸውም ጥያቄ ወይም አስተያየት ምላሹን መስጠት ወይም ሃሳቡን ማስተናገድ ከባድ ስለሆነ አይደለም። ያለንበት አዋካቢና አሰቃቂ ሁኔታ የሚያቀናጣ የትኩረትና የጊዜ የተትረፈረፉ እድሎች ስለማይሰጠን ብቻ ነው።

የሚገርመውና አሁንም የታሪክና የግል ህይወት ምጸት ይመስል፣ ቀደም ብዬ በጠቀስኳት መጣጥፍ ላይ የዛሬ 32 አመት፣ የአማራ ህዝብ ወከባ ውስጥ መሆኑን፣ በፍጥነት መንቀሳቅስ እንዳለብን የሚገልጽ ቃላቶች መጠቀሜ ራሴን አስገርሞኛል። ያች ትንሽ መጣጥፍ እዛው ገጽ 5 ላይ “የአማራ ህዝብ ……… ራሱን በፍጥነት ማዘጋጀት ካልቻለ፣ ይህ ህዝብ በሚሊዮኖች በረሃብ የሚረግፉበት፣ በሚሊዮኖች የሚሰደድብት፣ እንደ ህዝብ ክብሩ፣ ነጻነቱና ህልውናው ከማይጠበቅበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገባ መጠራጠር አይኖርብንም” ብላ ነበር። ህልውና የምትለውን ቃል ልብ በሏት።

አሁንም ልክ እንደ ዛሬ 32 አመቱ የአማራ ህዝብና ከዚህ ህዝብ አብራክ ነው የወጣሁት ብሎ የሚያስብ ምሁር፣ ትኩረትን ሳይበታትኑ እንደሌዘር አነጣጥሮ ስራን እየለዩ አድምቶ መስራት የሚጠይቅ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ዘመን ውስጥ መገኘነቱን መረዳት አለበት።

በ32 አመታት ውስጥ ለአማራው በበጎ መልኩ የተቀየረ ነገር የለም። የባሰ እንጂ። በመሆኑም ነው እርባና በሌላቸው፣ መሬት ላይ ያለውን በአማራ ህልውና ላይ ያሰፈሰፈውን መአት በፍጥነት መፍትሄ በመስጠት አስተዋጽኦ በሌላቸው የትኛዎቹም አጀንዳዎች ላይ፣ ማንኛውም ህልወናዬ አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ የሚያምን አማራ መጠመድ የለበትም የምለው። “በጉንጭ እና ብእር አልፋ ምልልሶች የሚጠፋ ጊዜ ሊኖረን አይገባም ።

ሐ) የጽሁፉ ይዘት በተመለከተ

ይህ ጽሁፍ ራሳቸውን በቻሉ የተለያዩ፣ ነገር ግን ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። ሁሉም ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ምልከታዎች የግልና የምር ናቸው። አንዳቸውም ለማምታታትና ለማሳመን (to confuse and convince) የተጻፉ አይደሉም። ሁሉም ጉዳዮች ሰፊ ትልልቅ ርእስ የተሰጣቸው ቢምስልም አሁን በቀጥታ የአማራ ህዝብ ከሚያደርገው የህልውና ትግል ጋር በተያያዘ ቅኝት የተጻፉ ናቸው። የሃሳብ ቦርጭ እንዳይኖራቸው አድርጌ ለማቅረብ ሞክሪያለሁ። ጽሁፉ በሚከተሉት 13 ርእሶች የተከፋፈለ ነው።

  1. ያለፈው እና መጪው ዘመን ለአማራ፤
  2. የአማራ የህልወና ትግል የአማራ ታጋዮች የጋራ ግንዛቤ፤
  3. የአማራ ትግልና የፋኖ ማኒፌስቶ
  4. የአማራ የህልውና ትግል፣ አማራ ልሂቅ፣ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት
  5. የ1960ዎቹ ትውልድና አማራነት የአማራ ህልውና ትግል
  6. ህብረ ብሄራዊ የሆነው የጸረ ወያኔ ትግል እና አዲሶቹ የአማራ ብሄረተኞች
  7. በአማራ አሸናፊነት ላይ የተመሰረተ የአማራ ህዝብ የህልውና ማስከበር ክንውን፣ ሃገራዊ ቀጠናዊና አህጉራዊ አንደምታው
  8. ወዳጅ ማብዛት ጠላትን መቀነስ የአማራ ስትራተጂ
  9. የአማራ ህዝብ የህልወና አደጋ ምንጮች ብዙ ናቸው። ሁሉን አደጋዎች በአንድ ጊዜ መጋፈጥ አይቻልም።
  10. የፋኖ አመራር አንድነት፣ የዳይስፖራ ድጋፍና አንድነት ትስስር
  11. የአማራ የህልወና ትግል በጤነኛ እና በታመሙ ብሄረተኞች እንቃስቃሴ ላይ ያሳደረው ተጽእኖና አንደምታው።
  12. የአማራ ህዝብ ለህልውና መከበር የሚያደርገው ትግልና ኤርትራ፣
  13. የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል የመጠንም የአይነትም እመርታ እንዲያሳይ፤

ለሚቀጥሉት 13 ተከታታይ ቀናት ከዚህ በላይ በዘረዘርኳቸው ርእሶች የጻፍኳቸውን ጽሁፎች በፌስቡክና በትዊተር ገጼ አጋራችኋለሁ ተከታተሉ። ለሌሎችም አጋሩ

የአማራን የህልውና አደጋ ከመከላከል ትግል ጋር የተያያዙ የተመጠኑ የግል ምልከታዎች!

March 8, 2025

 ነፃ አስተያየቶች

ቀን የካቲት 2017
በአንዳርጋቸው ጽጌ

ክፍል ፡2 ያለፈው እና መጪው ዘመን ለአማራ፤

ነብይ፣ ጠንቋይ፣ ሳንቲስት መሆንን አይጠይቅም። ያለፉትን መቶ ለመሙላት ጥቂት አመታት የቀረውን ዘመን በደንብ ማጤን ብቻ በቂ ነው። የውጭና የሃገር ውስጥ የአማራ ጠላቶች ተቀናጅተው አማራውን በማንነቱ ለይተው የመከራ ዶፍ አውርደውበታል።

አማራ ባላፉት መቶ አመታት ውስጥ በማንነቱ ላይ ጥቃት ሳይደርስበት ያለፉ ዘመናት ቢኖሩ መንግስታዊ ስርአቱን የተቆጣጠሩት አካላት ማንነታቸውን በኢትዮጵያዊነት የሚገልጹ በሆኑበት ዘመን ብቻ ነው። የኢትዮጵያዊ ገዥዎች ኢትዮጵያውያን በነበሩበት ዘመንም ቢሆን የአማራ ህዝብ በማንነቱ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አይድረስበት እንጂ ከፍቶት ካመጸ በገዥዎች እሳትና ብረት ተቀጥቅጧል።

በተለይ ግን ኢትዮጵያዊ በ1983 አ/ም ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አማራ በሆኑ ጽንፈኛ ብሄረተኞች እጅ ከወደቀች ጊዜ ጀመሮ የአማራ እጣ፣ ስቃይ፣ ሰቆቃ፣ ዋይታ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል፣ መፈናቅል መሰደድ መዋረድ ሆኗል። የ27 አመቱ የወያኔ አገዛዝ የአማራ ህዝብ በማንነቱ ተለይቶ እንዲጠቃ ህገመንግስታዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊና ዲፕሎማሲያዊ መደላደሎችን አመቻችቷል። ደግመ ደጋግመን በአማራ ጥላቻ ዙሪያ ወያኔ ስለቀረጸው የ1967 አ.ምቱ ፕሮግራሙ ማላዘን አያስፈልገንም።

ወያኔ ከስልጣን ከወረደ በኋላም ከመቼውም ዘመን በላይ የአማራ ህዝብ መጨፍጨፍና መፈናቀል ገጥሞታል። የጸረ አማራ አመለካከት የሚጋሩ ሃይሎች በህብረት የፈጸሙት ነው። ሆኖም ግን አሁን የአማራ ህዝብና ወንድሙና እህቱ የሆነው የትግራይ ህዝብ ያሉበትን አሰቃቂ ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብተን ወደ ኋላ እየተመለስን መካሰሱ ለማንም እንደማይበጅ ማወቅ አለብን።

የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ ዛሬ የሚገኙበት በህልውና ስጋት፣ በሰቆቃ በስቃይ የተሳሰረ የጋራ እጣ፣ ቀድሞም በታሪክ በባህል በቋንቋ በእምነት የተሳስሩትን ያህል ተመሳሳይ መሆኑን እያየን ነው። በበኩሌ ከወያኔ ጋር በተያያዘ የአማራ ህዝብ ያለፈበትን እጅግ አስዛኝና በመከራ የተሞላ ምእራፍ ለታሪክ ጸሃፊዎችና የተረጋጋና ጤነኛ የፖለቲካ አየር ለሚሰፍንባት የሂሳብ ማወራረድ ዘመን ከመተው ውጭ አማራጭ ያለን አይመስለኝም። በትንሹም ቢሆን በጥቅምት 2021 አ.ም በአምስት ክፍል በተከፋፈለ የፌስ ቡክ ጽሁፌ ሂሳብ ሲወራረድ ከአማራ ልሂቅ ይልቅ እዳ ያለበት የትግራይ ልሂቅ መሆኑን በሚገባ ማሳየት ችያለሁ። ይህን አንብቦ አሉላ ስለሞን ሳይቀር “እውነት ነው” የሚል ዳርዳርታ ያለው ንግግር ሲናገር ሰምቸዋለሁ።

መጪው ዘመን ለሁለቱም ህዝቦች ያረገዘው አደጋ ካለፈው የባሰ ነው። ይህ በጋራ የዘመናት ባህልና እሴት መተሳሰር ብቻ ሳይሆን በመጪው አስከፊ ዘመን የጋራ እጣ ጭምር መተሳሰራችን መቀበል፣ መናገር የአንድ ወገን፣ የአማራ ብቻ ስራ መሆን አይችልም። አማራው ይህ የገባው ይመስላል። ፋኖዎች በእስር ቤት ያገኗቸውን 16 የትግራይ ወታደራዊ መኮንኖች ሁኔታዎችን አመቻችተው ወደ ትግራይ የላኩት ይህ ገብቷቸው ነው። የትግራይ ህዝብ እንደሚገባው የሚያጠያይቅ አይደለም። የትግራይ ልሂቅ ግን ይህን መረዳት ይችል ይሆን የሚል ጥያቄ ምላሽ የሚያስፈልገው ነው።

አማራውን በተመለከተ መጪው ዘመን በአደጋና በመልካም እድል የተሞላ ነው። አደጋው አማራው እስከዛሬ ድረስ አይቶት የማያውቀው ጭፍጨፋ፣ እስራት እንግልት መፈናቀል መሰድድ ሊያጋጥመው የሚችልበት እድል እየጨመረ የሚሄድ መሆኑ ነው። ባለፉት ስድስት አመታት የአብይ አህመድ አገዛዝ ከመቼውም ዘመን ከፍቶ እንድናየው ያደረገ የአማራ ህዝብ እልቂት ምን እንደሚመስል አሳይቶናል። ያየነው እልቂት የአማራ ስቃይ ቅምሻ እንጂ፣ በዘረኝነት የተለከፉት የአማራ ጠላቶች ለአማራው የደገሱለት ዋናው ድግስ አይደለም። ድግሱ ምን እንደሚመስል በሰሞኑ አብይ አህመድ አዲስ አባባን ጠቅልሎ፣ ወደመተከል እና ወደ ወሎ እያማተረ የኦሮሞን ግዛት በዘር ማጽዳት ፍጅት ለማስፋት እየተዘጋጀ እንደሆነ በኦፌኮና በኦነግ ቃል አቀባዮቹ በኩል ነግሮናል።

እንዲህ አይነቱ የአብይ አህመድ ትልም የአበደ፣ ሃገር መምራት የተሳነው የአንድ ሰው የእውር ድንብር ጉዞ አድርጎ ማየት ትልቅ ስህተት ነው። በሃሰት ትርክትና በአማራ ጥላቻ አእምሯቸው የተቃወሰ አክራሪ የኦሮሞ ልሂቅ በሙሉ የሚጋራው ነው። ጥላቻን የፖለቲካ ነዳጅ አድርገው የግል ስልጣን እና ጥቅም ማስጠበቂያ ያደረጉ ጽንፈኞችን ከዚህ የተለየ ነገር ማሰብ ይችላሉ ብሎ መቃዠት አያስፈልግም። እነዚህ ሃይሎች በህግ፣ በሰላማዊ ድርድር ከአማራ ጀርባ ላይ ይወርዳሉ ብሎ ማሰብ የኔ ትውልድ ከፈጸመው ጥፋት የከፋ በአዲሱ የአማራ ትውልድ የሚደገም ትልቅ ታሪካዊ ጥፋት ይሆናል።

የአማራ የህልውና አደጋ ዋናው መመከቻ፣ የአማራ ህዝብ ክንድ ብቻ ነው። ስልጡን ፖለቲካ የሚባል ነገር በማይታወቅበት ሃገርና ቀጠና፣ የፖለቲካ ጉልበት ገና ለዘመናት የጥሬ ጉልበት ውጤት ሆኖ በሚቀጥልበት ሃገርና ቀጠና አማራ ትጥቁንና አንድነቱን አላልቶ ህልውናውን ከቶውኑ ማስከበር እንደማይችል መታወቅ አለበት።

መልካም አጋጣሚ ሊሆን የሚችለው ነገር አንድ ነገር ብቻ ነው። የአማራ ህዝብ የተደቀነበትን አደጋ መረዳቱ፣ ይህን አደጋ ለመቀልበስ መሳሪያ ያነሱበትን ሃይሎች ለመከላከል እንደ ህዝብ መሳሪያ ማንሳቱና የመሳሪያ ጉልበቱ በከፈተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑ ነው። ይህ መልካም አጋጣሚ ግን የበለጠ እንዲጎለብት፣ የጎደሉት በርካታ ነገሮች ገና መሟላት ይገባቸዋል። ፋኖን ብቻ አይደለም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር አማራ እንደ አንድ ወታደር በጋራ ካልቆመ፣ እንደአንድ ወታደር የአማራ የህልውናን አደጋ ግዙፍነት የተረዳ ንቃተ ህሊና ከሌለው፣ ይህን ግዙፍ አደጋ የሚመጥን ጠንካራ መሪ ድርጅት ከሌለው፣ አንድ ወጥ የሆነ የረቀቀ የፖለቲካ፣ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያው ስትራተጂና ታክቲክ ከሌለው፣ ይህ የመልካም እድል ጅማሮ ሊጨናገፍ፣ የተፈራው ከፍተኛ የህልወና አደጋ እውን መሆን ይችላል።

የዚህን ጽሁፍ ክፍል 1 እና 2ን በንባብ ያቀረበልንን EMS አመሰግናለሁ። ለመዳዳመጥ የሚከተልውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ

https://youtube.com/watch?v=NBbZEo5swNc%3Ffeature%3Doembed

የአማራን የህልውና አደጋ ከመከላከል ትግል ጋር የተያያዙ የተመጠኑ የግል ምልከታዎች!

March 10, 2025

 ነፃ አስተያየቶች

ቀን የካቲት 2017
በአንዳርጋቸው ጽጌ

ክፍል ፡ 3 የአማራ የህልወና ትግል የአማራ ታጋዮች የጋራ ግንዛቤ፤

የአማራን የህልውና አደጋ ከመከላከል ትግል ጋር የተያያዙ የተመጠኑ የግል ምልከታዎች!

March 11, 2025

 ነፃ አስተያየቶች

ቀን የካቲት 2017
በአንዳርጋቸው ጽጌ

ክፍል 4 ፡የአማራ ትግልና የፋኖ ማኒፌስቶ