March 1, 2025

 ነፃ አስተያየቶች

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

የካቲት 23 ቀን፣ 1888 ዓ.ም የዛሬ 129 ዓመት ፤ የተደራጀ ኃይል ያለውን ፣ የኢጣሊያንን  ሠራዊት ፣ የእናት አገሩ መደፈር አንገብግቦት የምኒሊክን የክተት ጥሪ ተቀብሎ ፣ በአብዛኛው  በትርና ጎራዴ ታጥቆ ፣ ከመላው ኢትዮጵያ ተሞ የመጣው  የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሠራዊት በታላቅ ተጋድሎ አደዋ ላይ አሸንፎታል ።

በዚህ ድል ምኒልክ እና ጣይቱ በመሪነት የሚጠቀሱ ዋንኞቹ መሪዎች  ነበሩ ። መሪዎች በአንድ አገር በጎና መጥፎ ታሪክ  ውስጥ  ያላቸው  ሚና  ቀላል  አይደለም ።

የአገራችንን የኢትዮጵያ ታላላቅ መሪዎችን መቅደላ ፣ ጉንደት ፣ ጉራዕ ፣ ዶጋሊ ፣ መተማ ፣ አደዋ ፣ ኡጋዴን ፣ ኤርትራ ላይ ያላቸውን ታላቅ አበርክቶ ታሪክ  ያስታውሰናል ።

የቀደሙትን አባቶቻችንን የዘመናት ተጋድሎ ለታሪክ ትተን ፤ አፄ  ቴዎድሮስ ፣ አፄ  ዮሐንስ ፣ ዓፄ ምኒልክ አፄ  ኃይለሥላሤ ፣ ጓድ መንግስቱ  በመሯት ኢትዮጵያ እንኳ ባለ አገሩ ዜጋ በዘውግ ሳይከፋፈል በአንድነት እና በፍቅር ተሳስሮ ፣ ለአገሩ  ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ ሚስቱን፣ ልጁን ፣ እናቱን ፣ አባቱን ፣ ወንድሙን ፣ እህቱን እና ዘመድ አዝማዱን  ከውርደት ፣ ከባርነት እና ከአሰቃቂ ሞት   አድኖል ። እነዚሁንም በመንበረ   የአገሩን ዳር ድንበር በደሙ አስከብሯል ።  ምንም እንኳን ከአደዋ ድልም በኋላ ፣ “ባህረ ነጋሽን  ” ኤርትራ ” በማለት ጣሊያን ቢያስተዳድራትም  ቅሉ  ።

” ባህረ ነጋሽን ” የዛሬዋን ” ኤርትራ ”  እስከ 1876  ዓ/ም ጀግናው ኢትዮጵያዊ  ራሥ አሉላ አባ ነጋ ያስተዳድሯት እንደነበር ይታወቃል ።  የያኔዋን ” ባህረ ነጋሽ ” የዛሬዋን “ኤርትራን ” አቶ መለሥ በወርቅ ሣህን ላይ በማድረግ  ለሥትራቴጂክ ጠላቶቻችን የዛሬ 33 ዓመት እንካችሁ በማለት  ፣ የሥልጣናቸው ማደላደያ ቢያደርጓትም ቅሉ  ።

( ይህንን ስጦታ አሜሪካኖች እንኳ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ተቃውመውታል   ። ቢያንስ በደርድር አሰብን ኢትዮጵያ መያዝ ነበረባት በማለት  ። ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ  ለማልማት ከፍተኛ መዋለ ነዋይ ማፍሰሷ እና ከእርሷ ውጪ የወደብ ተጠቃሚ እንደሌለ ስለተገነዘቡ ነው  ፤ ኢትይጵያን ወደብ አልባ ማድረግ ለኤርትራም እንደማይበጅ የተናገሩት ። የኢሣያስ ለሽንፈት ና ለውድቀት የሚዳርግ ጫዎታ እና ስግብግብነት በወቅቱ እንዳልጣማቸው ኸርማን ኮሆን በገደምዳሜ ተናግረው ነበር ።  )

ኤርትራን ከእናቷ  ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሤራ ፣ እጅግ የሚያንገበግብ ፣ ለአገር  ፍቅር መሞትን ከንቱ ና የከንቱ ከንቱ  የሚያደርግ ታላቅ የቅኝ ገዢዎቻችን ሤራ ነበር ።

( ዛሬም የኤርትራ መንገጠል የንገበግበናል ። ከብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ቃጠሎው አልበረደም ። ለታላቋ  ሉአላዊት አገር ኢትዮጵያ የባህር በር ሲሉ ዘራይ ደረስ ና  አሉላ አባ ነጋ ከእስትራቴጂክ ጠላቶቻችን ጋር የሰሜኑንን ህዝብ አስተባብረው  በጀግንነት ተዋግተዋል ።  ጀግኖቾቹ አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰዋል ። ህይወታቸውን ሰጥተዋል ።  እነዚህን ኩሩ እና ጀግና ኢትዮጵያዊያንንም የማይረሳ አገር ተረካቢ ትውልድ አገራችን ዛሬም አገሬ አላጣችምና ነው ንዴቱና ቁጭቱ እየበረታ የመጣው  ።

በጥቅምና በብልጭልጭ ነገር የማይደለሉ ፣ አገራቸውን ከራሳቸው በፊት የሚያስቀድሙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም አሉ ።

ምዕሪብውያኑ ግን ዛሬም በጥቅም እየደለሉን  ፣ ሰውነታችንን  ዘንግተን ፣  ሟች መሆናችንን ክደን ፣ በጭፍን ጥላቻ እንድንገዳደል እያደረጉን ነው ።

በቁስ ሰቀቀን እና በሆድ ተገዝተን ፣ አፈር ለሚሆን ሰውነታችን እና ጥለነው ለምንሄደው  ቁስ የበለጠ ተጨናቂ አድርገውናል ።  ከአንድ መሐፀን የወጣ ወንድማችንን እንኳ እያስካዱን በጠላትነት እንድንተያይ አደርገውን በፀፀት ወደማቃብራችን ይሸኙናል    ።

ለህዝብና ለሀገር እንዳንጨነቅ በማድረግ አገራችንን እና ህዝባችንን በምፅዎት ኗሪ ሆነው እንዲኖሩ ለማድረግ ረቂቅ ሴራቸውን እየተገበሩ ያሉትን ምዕራብውያን አና  ሌሎችንም ትርፋቸውን ብቻ የሚያሰሉትን  ቱጃሮች  ይህ እሣት የሆነ ትውልድ ጠንቅቆ ያቃቸዋል ።

አደዋ ላይ እነዚህን አልጠግብ ባይ በዝባዥ ኃይሎችን ድል ለማድረግ መቻላችን ከነሱ ያላነሰ እንደውም የሚበልጥ አእምሮ እና ልብ እንዳለን የተገነዘብንበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳልና   ።

በዛው ሞራል እንዳንቀጥል ግን በከፋፍለህ ግዛ መንገድ ፣ እንዴት በቋንቋ እንደለያዩን ፣  ከ1928  እስከ 1933 ፣ የአምስቱን ዓመት የተጋድሎ ዘመን  ሤራቸውን በመመርመር መረዳትም ችሏል ።

ይኽንን እውነት እነ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ ፍንትው አርገው በግለ  ታሪክ መፀሐፋቸው ፅፈውት አንብቧልና ።

( አንድ ሰው በቋንቋ ልዩነት ብቻ እንዲጠላ የማድረግ ሥነ ልቡና በተደራጀ መልኩ በዜጎች ልብ እንዲሰርፅ የተደረገው በአምሥቱ ዓመት የኢጣሊያን ወረራ ጊዜ ነበር ።  መለሥም ” የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው ? ” ሲል ይኼ ስነ ልቡና ተጠናውቶት ነው ። ይኸ አፍረሽ ስነልቡና ግን በቅኝ ገዢ አገሮች ውስጥ የለም ። በደቡብና ሰሜን አሜሪካም የለም ። በዛሬዋ ኢሲያ አህጉርም የለም ። ኧረ ከኢትዮጵያ በስተቀር ዛሬ በአፍሪካም የለም ። ሰው በቃ ሰው ነው ። ቋንቋ አይደለም ። ከክርስቶስ ልደት በፊት 2000 ዓመት አስቀድሞ  የነበረውን ዝርያ ከቶም ቆንቋ አይገደውም ነበረ  ።  ከ15 ሺ ዓመት አስቀድሞ የነበረው ደግሞ  በምን ቆንቋ እንደሚግባባ አይታወቅም ነበር   ። (ሁሌም አዲስ ለሆነ ሆድ  ፣ ምቾትና ድሎት በማሰብ  ብቻ  የተፈጥሮን አመጣጥ መካድና የታሪክን እውነት  በውሸት መተካት ከንቱ ተግባር ነው ።  የራስን ትርክት ጎልቶ እንዲወጣ በማድረግ ዘላለማዊ ላልሆነ ምቾት ና ድሎት ሲባል የሚተገበር  ከንቱነት ደግሞ በታሪክ ሁሌም የሚያሶቅስ ይሆናል  ።    )

ታሪክ ለሥመ ጥር እና አርቆ አሳቢ መሪዎች ፣ የሰጠው ክብር በዚህ ትውልድ እንደገና ሊታደስ ይገባዋል ።እኛ ኢትዮጵያዊያን በአደዋ ድል አማካኝነት የተጎናፀፍነው ድል ለአፍሪካ ነፃነትን ፣ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መውጣትን አጎናፅፏል ። የጥቁር የበታችነት እና ያለማወቅ ሐሰተኛ የነጮች ትርክት  በኢትዮጵያዊያን የአደዋ ድል ነበር  የተገለጠው  ።

” ነጭ  ኃያልና ሁሌም ተመላኪ ነው ” ብለው የሚያምኑ ቅኝ ገዢውች ጥቁር ኃያልና የአምላክ መገለጫ ክንድ እንዳለው የተገነዘቡት በአደዋ ድል ነው ።

ወደ አድዋ ፣ በሦሥት አቅጣጫ እየገሰገሰ የመጣው ፣ በሦሥት ጀነራሎች  የተመራው የሠለጠነው የኢጣሊያ ጦር  የተሸነፈው  ያለአንዳች ስስት ፣  ደረቱን ለጥየት በሰጠው ጥቁር  ኢትዮጵያዊ መሆኑ የጥቁሮች ትንሣኤ ነበረ   ።

ይኽ ድል በዛን ወቅት የዓለምን ኃያላን ያስደገጠ ነበር ። በተቃራኒው መላውን ጥቁር ህዝብን ያስፈነደቀ ነበር ። መላው ጥቁር ህዝብ የፈነደቀው  የነጭ የበላይነት አደጋ ላይ በመቀልበሱ ነው ። ” ጥቁርም ነጭን መግዛት ፣ ማሸነፍ መማረክና ምህረት ማደረግ ይችላል ። ” በማለት በጥቁሮቹ  ኢትዮጵያዊያን ድል አማካኝነት ሥነ ልቡናው ታደሱ ለነፃነት መፋለም የጀመረው ከአደዋ ድል በኋላ ነው ።

ከድሉ በኋላ ፣ በጀነራል ባራቴሪ ፊት አውራሪነት የሚመራውን  ጦር  ያ  በአገር ፍቅር ስሜት ልቡ የነደደው የኢትዮጵያ ባለ አገር አደዋ ላይ ድል ሲያደርገው የኢጣሊያን ህዝብ ለሚንሊክ ታላቅ የጀግና ክብር ሰጥቶ ነበር ።

የኢጣሊያንን ንጉስ ልጅ  ( አልጋ ወራሹን ) በእንኮኮ በመሸከም ፣ ህዝቡ በአጀብ ከቦ ” ምኒልክ ለዘላለም ይኑር ! ” በል እያለ ፣ ቀኑንን ሙሉ በሮም አደባባይ  እንዲጮኽ  እንዳደረገ መላው ጥቁር ህዝብ  ሲሰማ ደግሞ ፣ ያንን ጥቁር ንጉሥ አፄ ምኒልክን በእጅጉ ወዶታል ።

https://youtube.com/watch?v=_lAjWnnOgwI%3Ffeature%3Doembed