
ከ 4 ሰአት በፊት
ኡዲኪ ሴቬሪዮ በምዕራባዊ የደቡብ ሱዳን ኢኳቶሪያል ግዛት በሚገኝ ጫካ ውስጥ ተደብቋል።
የ43 ዓመቱ ደቡብ ሱዳናዊ አሁን ሀገሪቱ ውስጥ ባለው ውጥረት ምክንያት ከተደበቀበት ከወጣ ሊገደል እንደሚችል ይናገራል።
የዓለማችን በዕድሜ ትንሿ ሀገር ወደለየለት ግጭት ታመራለች የሚል ስጋት ተጭሯል።
በሀገሪቱ ላይኛው ናይል ግዛት በደቡብ ሱዳን ጦር እና ራሳቸውን ዋይት አርሚ (ነጩ ጦር) ብለው በሚጠሩ ወጣቶች ዘንድ ግጭት ተነስቷል።
ኡዲኪ በሺዎች ከሚቆጠሩ በግጭቱ ምክንያት ከተፈናቀሉ ደቡብ ሱዳናዊያን መካከል ነው።
“የዝናቡ ወቅት እየመጣ ነው። የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰብል ለመዝራት የእርሻ መሬት የሚያዘጋጅበት ወቅት ነበር። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ይህን ማድረግ አልቻልንም። አንዳንዶች ቤታቸው ናቸው። ሌሎች ደግሞ ጫካ ውስጥ ተደብቀዋል። ሁሉም ፍርሐት ውስጥ ነው” ይላል።
በናጌሮ ከተማ የምግብ እና መድኃኒት እጥረት አጋጥሟል። ገበያው ጭር ብሏል። ነጋዴዎች ዕቃ ጭነው የሚመጡበት መንገድ ከተዘጋ ሁለት ወራት አልፈውታል።
በተመሳሳይ ግዛት ነዋሪ የሆነችው ሱዛን ሳይመን በግጭቱ ምክንያት ከመኖሪያ ጎጆዋ መፈናቀሏን ትናገራለች። በዚህ ምክንያት እራሷን እና ልጇን መመገብ ተስኗታል።
“ቤታችን እያለን የፈለግነው ሠርተን መኖር እንችል ነበር። አሁን በሌሎች ላይ ጥገኛ ለመሆን ተገደናል። ያለንበትን ችግር የሚያውቁት እኒህ ሰዎች ናቸው” ትላለች።
“ከአንዳንድ መልካም ሰዎች እርዳታ እያገኘን ቢሆንም ሁኔታዎች እንዲቀየሩ ነው ፀሎታችን።”

ያልተረጋገጠ ሰላም
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ደቡብ ሱዳን በአውሮፓውያኑ 2011 ነው ከሱዳን ተገንጥላ የዓለማችን በዕድሜ ትንሿ ሀገር የሆነችው።
ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር የሀገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ሲሆኑ ሪዬክ ማቻር ደግሞ የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ።
ነገር ግን ከሁለት ዓመት በኋላ ፕሬዝደንት ኪር ሙሉ ካቢኒያቸውን አባረው ማቻር መፈንቅለ መንግሥት እያሴሩ ነው ብለው ከወቀሱ በኋላ በሀገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ።
በዚህ አምስት ዓመት በዘለቀ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በ2018 የሰላም ስምምነት ተፈረመ። ሁለቱም አካላት አዲስ ሕገ-መንግሥት ለማፅደቅ፣ ምርጫ ለማካሄድ፣ የጦር ኃይሎቻቸውን ለማዋሃድ እንደሁም የሕዝብ ቆጠራ ለማካሄድ እና የታጠቁ ኃይሎችን መሳሪያ ለማስፈታት ተስማሙ።
ነገር ግን እስካሁን ከስምምነቱ ማዕቀፎች አንዱም ተፈፃሚ አልሆነም። በሀገሪቱ የተለያዩ ግጭቶች መከሰታቸውም ቀጥሏል። በተመሳሳይ ከጎረቤት ሀገር ሱዳን የሚቃጡ ትንኮሳዎችም ነበሩ።
በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የተነሳው በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 2023 ነው። በጄነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሀን የሚመራው የሱዳን ጦር እና በጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሹ ኃይል (አርኤስኤፍ) ወደ ለየለት ጦርነት ገቡ።
በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት በሱዳን ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ደቡብ ሱዳን ይገኛሉ።
በዚህ ግጭት የተነሳ በ2024 የደቡብ ሱዳን ዋናው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ፈንድቶ ሀገሪቱ ሁለት ሦስተኛው ዓመታዊ ገቢዋን አጥታለች።
የነዳጅ ማስተላለፊያው መፈንዳት የፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርን መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ከትቶታል።
ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ እንደሚለው ፕሬዝደንቱ ከነዳጅ የሚያገኙት ገቢ በማሽቆልቆሉ ምክንያት “አገዛዛቸው እየተዳከመ መጥቷል።”
- ኡጋንዳ ውጥረት ወደ ነገሰባት ደቡብ ሱዳን ልዩ ጦር ማሰማራቷን አስታወቀች11 መጋቢት 2025
- በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ሄሊኮፕተር ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ8 መጋቢት 2025
- የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ጄኔራል መታሰር የሰላም ስምምነቱን የሚጥስ እንደሆነ ተገለጸ6 መጋቢት 2025

የወቅቱ ግጭት
በኪር እና ማቻር መካከል አሁን ግጭት የተቀሰቀሰው በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር መባቻ ነው። ከማቻር ጋር ግንኙነት ያላቸው የኑዌር ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰነው ናሲር ከተማ የሚገኘው የጦር ካምፕ ላይ ጥቃት አደረሱ።
የማቻር ታጣቂዎች ይህን ያደረጉት ባለፈው ወር የኪር ኃይሎች ኡላንግ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ነው የሚሉ ዘገባዎች አሉ።
ፕሬዝደንት ኪር የዋናው ተቃዋሚ አባል የሆኑትን ጄነራል በቁጥጥር ሥር አዋሉ። ሌሎችም የሱዳን ፒፕልስ ሊቤሬሽን ሙቭመንት ኢን ኦፖዚሽን አባላትም ታሰሩ።
የተቃዋሚው ኃይል ቃል አቀባይ የጦር ጄነራል መታሰራቸው ስምምነቱን “የሚጥስ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
በኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የደቡብ ሱዳን ተንታኝ የሆኑት ዳንኤል አኬች ግጭቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ ይችላል ይላሉ።
ነገር ግን ጎረቤት ሀገራት የሆኑት የኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ መሪዎች ጣልቃ ከገቡ ሁኔታው ሊቀዛቀዝ ይችላል የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ።

ሰብአዊ ጉዳት
ባለፈው ማክሰኞ የኡጋንዳ ጦር አዛዥ ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ሀገራቸው ፕሬዝደንት ሳልቻ ኪርን ለማገዝ ልዩ ኃይል ወደ ደቡብ ሱዳን ማሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ደቡብ ሱዳን ግን ከኡጋንዳ ወታደራዎ ድጋፍ መቀበሏን አስተባብላለች።
የወቅቱ ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት እጅግ አስከፊ በሆነ ጎርፍ ምክንያት 400 ሺህ ደቡብ ሱዳናውያን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት 90 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።
10 ሺህ ገደማ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ ተሰደዋል። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ወደ ኢትዮጵያ የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ይላል።
ኤምኤስኤፍ ደግሞ በግጭቱ ምክንያት በርካታ ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን እና የመድኃኒት እጥረት መኖሩን አስታውቋል።