ሱዳን፤ የትይዩ መንግሥቱ ምሥረታ የተካሄደባትን ኬንያ፤ አርኤስኤፍን በመደገፍ የከሰሰች ሲሆን፣ ኬንያ በበኩሏ፣ ሰላም ለማምጣት ለሚደረግ ጥረት ብቻ በገለልተኝት የንግግር መድረክ ማመቻቸቷን በመግለጽ ራሷን ተከላክላለች።
የምስሉ መግለጫ,ሱዳን፤ የትይዩ መንግሥቱ ምሥረታ የተካሄደባትን ኬንያ፤ አርኤስኤፍን በመደገፍ የከሰሰች ሲሆን፣ ኬንያ በበኩሏ፣ ሰላም ለማምጣት ለሚደረግ ጥረት ብቻ በገለልተኝት የንግግር መድረክ ማመቻቸቷን በመግለጽ ራሷን ተከላክላለች።

ከ 4 ሰአት በፊት

ሱዳን ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ከሠራዊቱ ጋር እየተዋጋ ያለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ)ን በናይሮቢ ማስተናገዷን ተከትሎ ከኬንያ የሚገቡ ምርቶችን በሙሉ አገደች።

ባለፈው ወር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና ተባባሪዎቹ በሱዳን ትይዩ መንግሥት የመመስረት ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልጽ መመስረቻ ቻርተር በኬንያ ተፈራርመዋል።

የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ምርቶቹ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የጣለው እገዳ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እና “ብሔራዊ ደህንነቷን ለመጠበቅ” ነው ብሏል።

በጦርነት የምትታመሰው ሱዳን ሻይ፣ የምግብ እቃዎች እና የመድኃኒት ምርቶችን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን ከኬንያ ታስገባለች።

የሱዳን ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ከኬንያ በሁሉም ወደቦች፣ አየር መንገዶች፣ እና መሸጋገርያ ኬላዎች የሚመጡ ማንኛውም ዓይነት ምርቶች ከዛሬ ጀምሮ ተጨማሪ መመርያ እስኪሰጥ ድረስ ታግደዋል” ብሏል።

አስከትሎም “ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት እገዳውን በአስቸኳይ እንዲያስፈጽሙ” አዝዟል።

በኬንያ እና በሱዳን መካከል ያለው ውጥረት ለበርካታ ወራት እየተባባሰ መጥቷል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው በሚል በአገር ውስጥ ሰፊ ትችት ገጥሟቸዋል።

ሱዳን፤ የትይዩ መንግሥቱ ምሥረታ የተካሄደባትን ኬንያ፤ አርኤስኤፍን በመደገፍ የከሰሰች ሲሆን፣ ከአገሪቱም አምባሳደሯንም ጠርታለች።

ኬንያ በበኩሏ፤ ሰላም ለማምጣት ለሚደረግ ጥረት ብቻ በገለልተኝት የንግግር መድረክ ማመቻቸቷን በመግለጽ ራሷን ተከላክላለች።

ከዚህ ቀደም ያላትን በቀጣናው የሚደረጉ ንግግሮችን የማስተባበር ልምድንም በማሳያነት ጠቅሳለች።

ሱዳን፣ ኬንያ አርኤስኤፍ የሚያደርጋቸውን ስብሰባዎችን ማስተናገዷ “ከጠላትነት ጋር አቻ ነው” ብላለች።

ነገር ግን ኬንያ ስብሰባዎቹን ማዘጋጀት በሱዳን ያለውን ጦርነት ለማስቆም መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን በመግለጽ “ከዚህ ውጪ የተለየ ዓላማ የለውም” ስትል ተሟግታለች።

ሁለቱ አገራት ጠንካራ የንግድ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ ኬንያ ለሱዳን በተለይም በግብርና እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጠቃሚ አጋር ነች።

ኬንያ ወደ ሱዳን በርካታ ምርቶችን የምትልክ ሲሆን፣ በቀዳሚነት ሻይ፣ በተጨማሪም ቡና፣ ትምባሆ እና ሌሎች እንደ ሳሙና፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች እና የመድሀኒት ምርቶችን ይከተላሉ።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ሻይ በኬንያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ምርት ሲሆን፣ ይህ የሱዳን እርምጃ የንግድ ልውውጥንም ሆነ ሰፊውን ኢኮኖሚ ያናጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆኑት ኬን ጊቺንጋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ይህ እገዳ ትልቅ ጉዳት አለው፤ የውጭ ምንዛሪ ችግርን ያስከትላል። ይህ ማለት የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ ከንግድ በላይ የሚዘልቅ ተፅዕኖ አለው።”

ሱዳን የኬንያ ሻይ በብዛት ከሚሸጡባቸው አምስት መዳረሻዎች መካከል አንዷ ስትሆን አምራቾች የእገዳው ተፅዕኖ አሳስቧቸዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ የሻይ ንግድ ማህበር (ኢኤቲኤ) በሂደት ላይ ያሉ ኮንትራቶች እና በጉዞ ላይ ያሉ ጭነቶች ስጋት እንዳሳደረበት ገልጿል።

“በአሁኑ ጊዜ ሻይ በፖርት ሱዳን ይገኛል። ቀደም ሲል የተላኩ በርካታ ኮንቴነሮችም አሁን በጉዞ ላይ ናቸው” ብለዋል።

በዚህ ውሳኔ የተነሳ በኬንያ የወደብ ከተማ ሞምባሳ ውስጥ ግዙፍ ክምችቶች መንቀሳቀስ አይችሉም።

“ይህ በገዢዎች ላይ ከባድ ኪሳራ ያስከትላል፤ እናም ቀስ በቀስ ተጽዕኖው ወደ አምራቾች እና ገበሬዎች ይወርዳል” ሲል ማህበሩ አስጠንቅቋል።

የአርኤስኤፍ አማካሪ ኤል ባሻ ተቤግ በኤክስ ገጻቸው ላይ ቡድኑ በሚቆጣጠራቸውው አካባቢዎች የኬንያ ምርቶች ወደ ሱዳን እንዲገቡ ዋስትና እንደሚሰጥ በመግለጽ ኬንያን ለማረጋጋት ሞክረዋል።

ነገር ግን ፖርት ሱዳን በጦር ኃይሉ እጅ ስትሆን በካርቱም እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የወታደራዊው መንግሥት መቀመጫ ሆናለች።

የኬንያ መንግሥት እስካሁን በይፋ አስተያየት የሰጠው አስተያየት ባይኖርም የግብርና ሚኒስትር ሙታሂ ካግዌ ግን በቅርቡ አገራቸው በሱዳን ያለውን የገበያ ተደራሽነት ችግር ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን እየፈተሸች መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ በሁለቱ አገራት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ ኬንያ ወደ ሱዳን የምትልከው የሻይ ምርት ተጎድቷል።

በቅርቡ የወጣ ዘገባ እንደሚያሳየው ኬንያ ባለፈው ዓመት ወደ ሱዳን ከላከችው ምርት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት የ12 በመቶ ቅናሽ ታይቷል።

በሱዳን እአአ በሚያዝያ 2023 የጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ ሲሆን፣ የተለያዩ ምርቶችን አቅርቦት ሰንሰለትን በማስተጓጎል፣ የንግድ ድርጅቶች መደበኛ ሥራ ለመስራት ያላቸውን አቅም ገድቧል።

ለንግድ በጣም አስፈላጊ የሆኑት ወደቦች እና የድንበር ኬላዎች በሁከቱ የተነሳ ወድመዋል ወይም ተስተጓጉለዋል።

ይህም ኬንያን ጨምሮ በሱዳን እና በጎረቤቶቿ መካከል ያለውን የሸቀጥ ፍሰት በእጅጉ ቀንሷል።

ግጭቱ የሱዳን ዋና ከተማን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱን ክፍል ያወደመ ሲሆን፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ሲዳርግ፣ ከ12 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ማፈናቀሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።