
ከ 3 ሰአት በፊት
አሜሪካ በመዲናዋ ዋሽንግተን ተቀማጩን የደቡብ አፍሪካውን አምባሳደር ልታባርር መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታወቀች።
አምባሳደር ኢብራሒም ራሱል “በታላቋ አገራችን ተቀባይነት የላቸውም” ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተናግረዋል።
ማርኮ ሩቢዮ፣ አምባሳደሩ አሜሪካን እንዲሁም ዶናልድ ትራምፕን የሚጠሉ ናቸው ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ከስሰዋቸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም “ዘረኛ ፖለቲከኛ” ሲሉ የፈረጇቸው ሲሆን “ከእሱ ጋር የምንወያየው ምንም ነገር የለም” ብለዋል።
ይህ ያልተለመደ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ በሁለቱ አገራት መካከል እየተካረረ የመጣውን ውጥረት የሚያሳይ ነው።
አምባሳደር ኢብራሒም በቅርቡ ስለ ትራምፕ አስተዳደር የሰጧቸውን አስተያየቶች ጠቅሶ የጻፈውን የቀኝ ክንፍ አክራሪ ሚዲያ የሆነውን ብሬይትባርትን ሩቢዮ ዋቢ አድርገዋል።
“ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ላይ ባሉ ሰዎች ላይ ጥቃት ጀምረዋል። በአገራቸው እንዲሁም በውጭ አገራት የበላይነትን ለማስፈን እየሞከሩ ነው” ሲሉ አምባሳደሩ በአንድ ዝግጅት ላይ ተናግረዋል።
- የትግራይ ክልል ቀውስ፡ ከፕሪቶሪያ ወዲህ መቼ ምን ተከሰተ?ከ 4 ሰአት በፊት
- አንጎላ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ፖለቲከኞችን አላስገባም አለችከ 3 ሰአት በፊት
- ሱዳን ተፋላሚዬን ትደግፋለች በሚል ከኬንያ የሚገቡ ምርቶችን በሙሉ አገደችከ 4 ሰአት በፊት
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
አክለውም የማጋ (አሜሪካን በድጋሚ ታላቅ እናድርግ) እንቅስቃሴ “በአሜሪካ ውስጥ እየተከሰተ ላለው ከፍተኛ የስነ ህዝብ አወቃቀር ለውጥ ምላሽ ነው።….በአሜሪካ መራጮች 48 በመቶ ነጭ እንደሚሆኑ ይጠበቃል” ማለታቸው ተጠቅሷል።
ይህንንም ተከትሎ ሩቢዮ አምባሳደር ኢብራሒምን ‘ፐርሰና ነን ግራታ’ (ተቀባይነት የሌላቸው) ሲሉ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ፈርጀዋቸዋል።
ትራምፕ ስልጣን መረከባቸውን ተከትሎ በአሜሪካ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተሞላበት ሆኗል።
ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲ በተወሰኑ “ማኅበሰረሰቦች” ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለአገሪቱ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ አቋርጠዋል።
ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ደቡብ አፍሪካ ከአሜሪካ የምታገኘው የገንዘብ ድጋፍ የኤድስ የአደጋ ጊዜ ዕቅድ በሆነው ፔፕፋር ውጭ ሌላ እንደሌለ ጠቅሰዋል።
ይህም ገንዘብ አገሪቱ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከል ከያዘችው 17 በመቶ ነው ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ስርዓት ከ30 ዓመታት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች አነስተኛ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንዳንድ ሁኔታዎች ያለ ካሳ መሬት መውረስ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ፈርመዋል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በመሬት ባለቤትነት ላይ የሚታየው ታሪካዊ ኢፍትሃዊነት እና ዘረኝነት እንዲስተካከል ጥሪዎች እየቀረቡለት ይገኛሉ።
በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የከሰሰቻት ሲሆን ይህም ጉዳይ በጦር መሳሪያ ጭምር እየደገፈቻት ያለችውን አሜሪካን አስቀይሟል።