ጌታቸው ረዳ፣ ታደሰ ወረደ እና ድብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል

ከ 4 ሰአት በፊት

የትግራይ ክልል ከሁለት ዓመት አንጻራዊ ሰላም በኋላ እንደገና ወደ ዳግም ቀውስ ለመግባት ጫፍ ላይ ደርሷል። በየትግራይ ጦርነት በአንድ ጎራ ሆነው የአዲስ አበባን መንግሥት የተዋጉት የህወሓት አመራሮች አሁን በሁለት ጎራ ተከፍለው ተፋጠዋል።

በፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ቡድን ባለፉት ጥቂት ቀናት በክልሉ የሚገኙ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶችን መቆጣጠር ጀምሯል።

የህወሓት ሌላኛው ክንፍ አባል እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው አራት ከፍተኛ ትግራይ ሠራዊት አመራሮችን አግደዋል።

ሁለቱም ቡድኖች እርስ በእርስ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ በመጣል ይካሰሳሉ።

አቶ ጌታቸው ረዳ የእሳቸው ባላንጣ የሆነው ቡድን የወረዳ፣ የቀበሌ እና የከተማ ከንቲባዎችን “ማህተም እየቀማ” መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም “የወረዳ ማህተም፣ የቀበሌ ማህተም አሁን የከተሞች ከንቲባዎችን ማህተም እየለቀመ የሚውል ኃይል፤ ኮስተር ብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ‘ልደራደር ነው’ ብሎ ይመጣል” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በክልሉ እየተካሄደ ያለውን ቀውስ “መፈንቅለ መንግሥት” ሲሉ ጠርተውታል።

የዶ/ር ደብረጽፂን ክንፍ በበኩሉ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ባወጣው መግለጫ “ትግራይ ውስጥ የተጀመረው ሕግ እና ሥርዓት የማስከበር ሥራ . . . የተጀመረውን ሰላም ስምምነት ትግበራ ይበልጥ የሚያጠናክር” መሆኑን ገልጿል።

በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ከአንጻራዊ ሰላም እንዴት ወደዚህ ቀውስ ተሸጋገረ? ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ወዲህ የነበሩ ቁልፍ ክስተቶች የትኞቹ ናቸው?

የፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት

ለሁለት ዓመት የቆየውን ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት ያስቆመው በዘላቂነት ግጭት የማስቆም ስምምነት የተደረሰው ከሁለት ዓመት አምስት ወራት በፊት ጥቅምት 23/2015 ነበር።

የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ለአስር ቀናት ድርድር ላይ ነበሩ።

በድርድሩ ማብቂያ ላይ በተፈረመው ባለ 12 ነጥብ ስምምነት ሁለቱ ወገኖች በአገሪቱ መኖር ያለበት የጦር ኃይል አንድ መሆኑን እና የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ተስማምተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ሁሉን አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም እና በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ ወንጀሎች እና የመብት ጥሰቶች ደግሞ በሽግግር ፍትህ እንደሚታዩ ስምምነቱ ተጠቅሷል።

የናይሮቢው የአፈጻጸም ውል

ከፕሪቶሪያ ስምምንት መፈረም አስር ቀናት በኋላ ኅዳር 3/2015 ዓ.ም. የመንግሥት እና የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች ደቡብ አፍሪካ ላይ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።

ከስምምነቱ በፊት ወታደራዊ አዛዦቹ በናይሮቢ ለአምስት ቀናት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመው አጠቃላይ ስምምነት ተግባራዊ በሚደረግበት ዝርዝር ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር።

ይህ ስምምነት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ የትጥቅ መፍታትን እንዲሁም ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን ጉልህ እርምጃ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ተናግረው ነበር።

በጊዜው ሁለቱ ወገኖች “ትጥቅ የሚፈታበትን እና የመከላከያ ሠራዊት ወደ መቀሌ በሚገባበት ዕቅድ ላይ” መስማማታቸውን መንግሥት ማስታወቁ አይዘነጋም።

የተቋረጡ አገልግሎቶች መጀመር

በሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት ወቅት መብራት፣ ውሃ እና የቴሌኮም አገልግሎት በክልሉ ተቋርጦ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የባንክ እና የትራንስፖርት አገልግሎትም አልነበረም።

ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ሁለት ወራት ገደማ በኋላ በታኅሣሥ 20/2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀለ ከተማ በረራ ጀምሯል።

አየር መንገዱ በረራ ከመጀመሩ ሁለት ቀናት በፊት ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ መቀለ ተጉዘው ነበር።

ከአየር ትራንስፖርት በተጨማሪ ከሁለት ዓመት በላይ ተቋርጠው የነበሩት የኤሌክትሪክ፣ የስልክ እና የባንክ አገልግሎቶች በዚያው ሰሞን ዳግም ተጀምረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ዳግም በተጀመረበት ታኅሣሥ 20/2015 ዓ.ም. የፌደራል ፖሊስ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ገብቷል።

የፌደራል ፖሊስ አባላቱ ወደ ከተማዋ በመግባት “የፌደራል መንግሥቱን ተቋማት የመጠበቅ ሥራ” መጀመራቸው አስታውቆ ነበር።

የሀላላ ኬላው የገጽ ለገጽ ንግግር

ከእርስ በርስ ጦርነቱ እና ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምንት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከህወሓት አመራሮች ጋር በደቡብ ምዕራብ ክልል ዳውሮ ዞን ሀላላ ኬላ ሪዞርት ጥር 26/ 2015 ዓ.ም. ተገናኙ።

በሀላላ ኬላው ውይይት የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ፣ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የአሁኑ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና ሌሎችም በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

በትግራይ በኩል ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ተንሳይ፣ ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ አምባሳደር ወንደሙ አሳምነው እና ሌሎችም ተገኝተው ነበረ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋም

በመጋቢት 12/2015 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው ስበሰባ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን የሚያቋቁም ደንብ አጽድቋል።

በዚሁ ዕለት ደንቡን መሠረት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አድርገው ሹመዋል።

አቶ ጌታቸው ከሹመታቸው አንድ ሳምንት በኋላ 27 አባላት ያሉትን የጊዜያዊ አስተዳደራቸውን ካቢኔ ይፋ አድርገዋል።

በአቶ ጌታቸው ካቢኔ ውስጥ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በተደገው ጦርነት የትግራይ ኃይሎችን ሲመሩ የነበሩት ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ቀድሞው የአገሪቱ ሠራዊት ኤታማዦር ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።

ህወሓት ከሽብረተኝነት መዝገብ መሰረዝ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ያቋቋመው ደንብ በጸደቀ ማግስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን ከአሸባሪነት መዝገብ ሰርዞታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን ከአሸባሪነት የሰረዘው የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ሲሆን፣ ውሳኔው በ61 የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ነው።

የሰላም ስምምነቱ፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሓት ላይ የተላለፈውን የአሸባሪነት ውሳኔ ፍረጃ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲነሳ ያመቻቻል” የሚል ድንጋጌ አለው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን በአሸባሪነት የፈረጀው፤ ከጦርነቱ መቀስቀስ ከወራት በኋላ በሚያዝያ 2013 ዓ.ም ነበር።

የቡድን መሳሪያዎችን ትጥቅ ማስፈታት

በኅዳር 2015 ዓ.ም. የተቋቋመው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በጥር ወር በትግራይ ክልል የቡድን መሳሪያዎችን የማስረከብ ሂደት አስጀምሯል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን “በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄዱ የቆዩት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ በማስፈለጉ” የተቋቋመ ነው።

የህወሓት ኃይሎች ታጥቀዉት የነበረዉን ከባድ ጦር መሳሪያ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማስረካባቸው ተዘግቧል።

የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ መፍታት በፕሪቶሪያው ስምምነት ከሰፈሩ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

ኮሚሽኑ ባለፈው ኅዳር ወር ደግሞ ትጥቅ ያስረከቡ የቀድሞ ተዋጊዎችን በትግራይ ክልል ተቀብሎ ወደ ዲሞብላይዜሽን ማዕከላት ማስገባት ጀምሮ ነበር።

አደጋ ያንዣበበበት የህወሓት ህልውና

ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ህወሓት በኃይል እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕጋዊ ፓርቲነት ዕውቅናው መሰረዙ ይታወቃል።

የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2016 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ኃይል እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፉ ለነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ሕጋዊ ዕውቅና የሚሰጥ አዋጅ አጸደቀ።

ይህ የምርጫ ሕጉ ማሻሻያ አዋጅ ህወሓት መልሶ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችለው ሲሆን፣ ህወሓትም በምርጫ ቦርድ የተሰረዘበት ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ጥያቄ አቅርቧል።

ነገር ግን ቦርዱ ፓርቲው የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘ እና በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ መወሰኑን አስታውቋል።

ቦርድ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ መሠረት የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነትን መመለስ የሚል ባለመኖሩ መሆኑን ጠቅሶ ነበር።

ነገር ግን ህወሓት የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት እንጂ በምርጫ ቦርድ ዳግም መመዝገብን እንደማይቀበል ሲያሳውቅ፣ ቦርዱ ባለፈው ታህሳስ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲያደርግ አሳስቦ ነበር።

ሆኖም ግን ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ በመጠናቀቁ ለሦስት ወራት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በምርጫ ቦርድ ታግዷል።

ህወሓት በበኩሉ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሕጋዊ ተፈጻሚነት የለውም ሲል ባወጣም መግለጫ ተቃውሞውን ገልጿል።

አወዛጋቢው 14ኛው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ

ህወሓት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በአመራሮቹ መካከል አለመግባባትን የፈጠረው እንዲሁም በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያላገኘውን 14ኛ ጉባኤውን አካሄደ።

ይህ በህወሓት ውስጥ ያለውን ልዩነት ያሰፋው ጉባኤ በአመራሮቹ መካከል ክፍፍልን በመፍጠር ያለፈ ሲሆን፣ የክልሉ ጊዜያዊ አተዳደር ፕሬዝዳንት እና ምክትል ሊቀመንበሩን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አመራሮቹ እራሳቸውን ከስብሰባው አግልለዋል።

በዚህ ሁሉ ውዝግብ መካከል የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል ለሊቀመንበርነት በድጋሚ መመረጣቸው ሲነገር፣ አቶ ጌታቸው እና እራሳቸውን ከጉባኤው ያገለሉ አባላት ከህወሓት አመራርነት ብቻ ሳይሆን ከአባላነት እንዲሰናበቱ ተወስኗል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩን “የማስተካከል” ሙከራ

ዶ/ር ደብረፂዮን በህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ሥራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ አስታውቀዋል።

አክለውም ከዚህ ቀደም ህወሓትን ወክለው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የገቡ አመራሮች፣ በአሁኑ ጉባኤ ባለመሳተፋቸው እና ባለመመረጣቸው ህወሓትን መወከል አይችሉም ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ህወሓት የታገዱት አመራሮች፣ በህወሓት ውክልና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያላቸው ኃላፊነት ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ እንደሚፈልግ ገልጿል።

ባለፈው ጥር ወር ደግሞ በክልሉ ያሉ የወታደራዊ አመራሮች ህወሓት በወሰነው መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ በአዲስ እንዲዋቀር መወሰናቸውን ገልጸዋል።

ይህንን የህወሓት ሊቀመንበር እና የወታደራዊ አመራሮቹ ሐሳብ “የመፈንቅለ መንግሥት” ፍላጎት ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ አስተዳደራቸው እርምጃ እንደሚወስድ አሰጥንቅቆ ነበር።

የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦች መታገድ

በክልሉ ያሉ ሁኔታዎች ተባብሰው አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አራት የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን አግደዋል።

ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊሰ፣ ሜጀር ጄነራል ማሾ በየነ፣ ብርጋዴር ጄነራል ምግበይ የታገዱት ሰኞ መጋቢት 1/2017 ዓ.ም. ሲሆን፣ በማግስት ማክሰኞ ደግሞ ጄነራል ፍሰሐ ኪዳኑ ላይ ጊዜያዊ ዕግድ ተጥሎባቸዋል።

የሠራዊቱ አመራሮቹ ላይ ዕገዳው የተላለፈው “ከመንግሥት ውሳኔ ውጪ መላ ሕዝባችንን እና ወጣቱን ወደ ግርግር፤ የፀጥታ ኃይላችንን ወደ እርስ በርስ ግጭት ብሎም ሕዝባችንን ወደማይወጣበት አዘቅት የሚያስገባ አደገኛ እንቅስቃሴ” በማድረግ በሚል ነው።

አቶ ጌታቸው ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ለትግራይ ቲቪ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ወታደራዊ አዛዦቹ፤ “ውሳኔ” ያሉትን ተግባራዊ ለማድረግ “ሁሉንም እርምጃዎች” መውሰድ በመጀመራቸው እንደታገዱ ገልጸዋል።