በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት ዳግም ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ተፈጥሯል
የምስሉ መግለጫ,በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት ዳግም ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ተፈጥሯል

ከ 2 ሰአት በፊት

በትግራይ ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም.የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ አብቅቷል።

አሁን ከጦርነት ጠባሳ ባላገገመችው በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ የሚገኙ ነዋሪዎች ዳግም ወደ ግጭት ይገባ ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው።

በመቀለ ከተማ ሕዝቡ የከፋ ነገር ከመጣ በሚል እየተዘጋጀ ነው።

የሸቀጣ ሸቀጥ እቃዎች ዋጋ እየናረ መምጣቱን ተከትሎ ሸማቾች ለክፉ ጊዜ በሚል ሸመታ ላይ ተጠምደዋል።

በባንኮች አካባቢ ገንዘባቸውን ለማውጣት የሚፈልጉ ሰዎች ረዣዥም ሰልፎችን ይዘው ይታያሉ።

ከተማዋን ለቅቆ ለመውጣት የገንዘብ አቅሙ ያላቸው ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ የአውሮፕላን ትኬት እየቆረጡ ነው።

ከመቀለ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎች ለቀናት ሙሉ በሙሉ ትኬት ተቆርጦ አልቋል።

አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ “ይህ ሁሉ የሚሆነው ከጭንቀት የተነሳ ነው” ይላል።

ትግራይ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው እና የግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል ተብሎ የሚገመተው አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ማዕከል ነበረች።

በ2015 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሁለቱ ዋና ዋና ተፋላሚ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሠላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ አፈ ሙዞች ዝም ማለት ችለዋል።

ይህም ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ክልሉን እንዲመራ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም አስችሏል።

ነገር ግን ከቅርብ ወራት ወዲህ በህወሓት ውስጥ ባሉ ከፍተኛ አመራሮች እና በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር መካከል የስልጣን ሽኩቻ እየጨመረ መጥቷል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ አንዳንድ የህወሓት ሰዎች ስልጣን በኃይል ለመንጠቅ ሞክረዋል ሲል ይከስሳል።

ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛቸውን “ከውጭ ተዋናዮች” ጋር ይሰራሉ በሚል ይካሰሳሉ።

ሁለት ሴቶች አዛውንትን ግራ እና ቀኝ ደግፈው እዘው

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

አሁን በ2015 የተፈረመው የሠላም ስምምነት ሊፈርስ ይችላል፣ አልፎ ተርፎም በኢትዮጵያ እና በጎረቤቷ ኤርትራ መካከል ቀጥተኛ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ተከስቷል።

የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥትን በመደገፍ በቀጥታ ወታደሮቹን በማሰማራት ተሳትፏል።

ነገር ግን የሁለቱ አገራት ግንኙነት የፕሪቶርያ ሠላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ እየሻከረ መጥቷል።

በመቀለ ከተማ ነዋሪዎች ቀጣይ ግጭት ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት ገብቷቸዋል።

ጫማ በመጥረግ ሕይወቱን የሚመራው እና እድሜው በሀያዎቹ የሚገመተው ተስፋይ ገብረአብግዚ “ወጣቶች ግጭት ሰልችቷቸዋል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በጦርነቱ ወቅት ብዙ ሰዎች የመዋጋት ፍላጎት ነበራቸው፤ አሁን ግን ተሰላችቷል።”

አትክልቶችን በመሸጥ የምትተዳደረው እና እድሜዋ በ50ዎቹ የሚገመተው ሐይማኖት ገብረማርያም ደግሞ በ2013 የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሁለቱ ልጆቿ በትግራይ በኩል ጦርነቱን መቀላቀላቸውን ትናገራለች።

ሴት ልጇ በሰላም ስትመለስ ወንድ ልጇ ደግሞ የአካል ጉዳት አጋጥሞታል።

ወደ “ጨለማው ዘመን” መመለስ እንደማትፈልግ የምትገልጸው ሐይማኖት፣ አሁን ያለው ሁኔታ “በጣም አሳሳቢ ነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

“አሁንም የምንኖረው ካለፈው ጦርነት ቁስል እና ጠባሳ ጋር ነው። ዳግመኛ እንባችንን ማፍሰስ አንፈልግም።”

ፀጋነሽ ካሳ በማዕከላዊ ትግራይ፣ ሽሬ የምትኖር የቀድሞ ታጋይ ስትሆን፣ በጦርነቱ ወቅት እግሯ ክፉኛ ቆስሏል።

አሁን በክራንች የምትራመድ ሲሆን በቋሚነት ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋታል።

ለቢቢሲ ጦርነት “ቤተሰቤን አቃውሶታል” ብላለች።

“የአካል ጉዳተኛ ነኝ፤ የቤተሰቤ ኢኮኖሚ ላሽቋል። ያንን እንደገና ማየት አልፈልግም። በድንኳን ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንኳን አልተመለሱም።

አክላም “ማንም ሰው ሌላ [ዙር ጦርነት] ማስተናገድ አይችልም” ብላለች።

የትግራይ ክልል ጦርነቱ ካስከተለው አስከፊ ጉዳት ሙሉ በሙሉ አላገገመም።

ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች አሁንም ወደ ቀያቸው መመለስ አልቻሉም።

አንዳንድ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማትን ጨምሮ ገና አልተጠገኑም።

በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በግልጽ የሚታይ ጭንቀት ቢኖርም መደበኛ ሕይወት ግን ቀጥሏል።

ንግዶች እና ሱቆች በመደበኛነት እየሰሩ ናቸው፤ እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ ብዙ የጸጥታ ኃይሎች አይታዩም

ነገር ግን በአፍሪካ አስከፊ ከሚባሉ መካከል አንዱ የሆነውን ጦርነት በቅርቡ ያስተናገደችው ከተማ ነዋሪዎች እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እና መግለጫ በንቃት እና በቅርበት ይከታተላሉ።

በአንድ ቡና መሸጫ ካፌ ውስጥ የተሰባሰቡ ወጣቶች አንገታቸውን ስልካቸው ውስጥ ቀብረው ይታያሉ።

በቅርቡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከፌዴራል ባለስልጣናት ጋር “ለመመካከር” በሚል አዲስ አበባ ከሄዱ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምለሽ እየተመለከቱ ነው።

በሌላ ካፌ እንዲሁ አንድ ወጣት ሐሙስ ዕለት በተቃዋሚው የህወሓት ቡድን የተሾመው፣ አዲሱ የከተማዋ ከንቲባ ሕዝቡን ለማረጋጋት እንደሚያደርግ ለመስማት እየጠበቀ መሆኑን ተናግሯል።

ሁሉም ሰው፣ የሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ምን እንደሚያመጡ ለማየት እየጠበቀ ያለ ይመስላል።