
https://www.ethiopianreporter.com/139300/
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ችክዌ ኢህሄክዌያዙ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጉብኝት ባደረጉበት
ማኅበራዊ አሜሪካ ያቋረጠችው ድጋፍ ተፅዕኖ እንዳላሳደረበት የኅበረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተናገ
ቀን: March 16, 2025
የአሜሪካ መንግሥት ባቋረጠው የፋይናንስ ድጋፍ ምክንያት በሥራው ላይ ተፅዕኖ እንዳልደረሰበት፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ወደ ሥልጣን ከመጡ ስድስት ሳምንታት ያስቆጠሩት ፕሬዚዳት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት በገቡ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ለአገሮች ሲያደርገው የነበረው ድጋፍ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የትራምፕ ውሳኔ በአፍሪካ ጤና አጠባበቅ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማምጣቱ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ አሜሪካ አ.ኤአ. በ2024 ወደ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ የጤና ዘርፍ ብቻ ዕርዳታ ማቅረቧን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአሜሪካ ለጤናው ዘርፍ ይቀርብ የነበረው ድጋፍ በመቋረጡ፣ ወሳኝ የሚባሉ አገልግሎቶች ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጥር የጤና ዘርፍ ተዋንያን እየገለጹ ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በምርምር ሥራዎቹ ላይ ምንም ያጋጠመው ችግር የለም ብለዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የምትሠራቸው ምርምሮች መሆናቸውን በመግለጽ፣ ‹‹አሁን በምንሠራው ሥራ የተለየ ያጋጠመን ተፅዕኖ የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሥራዎች በመንግሥት ዓመታዊ ዕቅድ፣ በራስ አቅምና በኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የሚከናወኑ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር፣ የበሽታዎች ቅኝትና መከላከል፣ ቅድመ ዝግጁነትና ምላሽ፣ ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን መከላከልና የቁጥጥር ሥራዎች ያለ ምንም ችግር እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በኢንስቲትዩት ላይ ወደፊት ሊኖሩ በሚችሉ ተፅዕኖዎችና ይጠበቃሉ ተብለው ለሚታሰቡ ክፍተቶች ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን፣ ‹‹በራስ አቅም ለመንቀሳቀስ አማራጮችን ቀይሰን እየሠራን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ችክዌ ኢህሄክዌያዙ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አበባ ጉብኝት ሲያደርጉ ነው፡፡
ለአፍሪካ ዳይሬክተሩ ሪፖርተር የፋይናንስ እጥረትን በተመለከተ ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት መውጣቷና ዕርዳታ ማቆሟ ትልቅ ተግዳሮት ሊሆን ቢችልም፣ እንደ አኅጉር በርካታ የአፍሪካ አገሮች ለራስ ችግር መፍትሔ ለመስጠት መነሳሳት እየታየ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መነሳሳት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ለተቋረጠው የፋይናንስ ድጋፍ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹ለበርካታ የአፍሪካ አገሮች የሚገጥማቸውን ማነቆ በራሳቸው አቅም እንዲፈቱ የሚያደርግ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ነገር ግን ወቅቱ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከሌሎች ጋር መሥራት እንዳለብን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ዕርዳታ መቋረጥ በኢትዮጵያ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጫና የኢትዮጵያ መንግሥት ሊመልሰው ይጋባል ብለው፣ የዓለም ጤና ድርጅት ግን የ194 አባል አገሮች ድርጅት በመሆኑ፣ አሜሪካ ከድርጅቱ ብትወጣም አባል አገሮች ተባብረው መሥራታቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
‹‹አባል አገሮች ከጅምሩ ችግሮችን በኅብረት ሆነው ለመፍታት ከ75 ዓመታት በፊት የመሠረቱት ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ችግሮች አሁንም አሉ፡፡ ስለዚህ አገሮች ተላላፊ በሽታዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የጤና ፖሊሲና የጤና ፋይናንስ የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት አለባቸው፡፡
አሜሪካ ከድርጅቱ በመውጣቷ አዝነናል፡፡ በቀጣይም ሁሉንም አካላት በማነጋገር የማቀራረብ ሥራ እንሠራለን፤›› በማለት አክለዋል፡፡
ትልቁን የፋይናንስ ምንጭ በማጣታችን ችግር ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ለምናገለግለው ሕዝብ መሥራታችንን አናቆምም፡፡ ምንም ፈታኝ ሁኔታ ቢገጥመንም አባል አገሮችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማገዝ የዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ ይቀጥላል፤›› ብለዋል፡፡
