
https://www.ethiopianreporter.com/139304
ዜና የክልሉን ሕዝብ ሥጋት ላይ የጣለው የሕወሓት አመራሮች ውዝግብ
ቀን: March 16, 2025
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ፣ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተጠቅመው ትግራይን ማጥፋት የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ በመጥቀስ፣ ‹‹ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች ከኤርትራ መንግሥት ጋር እየሠሩ ነው፤›› የሚለውን ጨምሮ ካቀረቧቸው ማብራሪያዎች በኋላ፣ በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ሕወሓት ክንፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በሁለቱ የሕወሓት ክፍሎች መካከል ያለው የፖለቲካ ውጥረት መካረርን ተከትሎ 24 የምዕራቡ ዓለም አገሮችና የአውሮፓ ኅብረት ወደ ግጭት መመለስ እንደማይገባ ማሳሰቢያ ሲሰጡ፣ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የሰላምና ፀጥታ ካቢኔ ቢሮ በበኩሉ፣ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የቀረበው ጥያቄ ኃላፊነት የጎደለው ነው ሲል ወቅሷል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት የሚመራውን የፖለቲካ ድርጅቱን ክንፍ በተደጋጋሚ ሲወቅስ የቆየው ሌላው የሕወሓት ክንፍ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ፣ በተመሳሳይ ቀን ሐሙስ መጋቢት 4 ከሰዓት በመቀሌ ከተማ በሰጡት መግለጫ፣ በትግራይ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ምክር ቤት የሾማቸውን ተሿሚዎች ወደ ሥራ ገበታቸው የማስገባትና አገልግሎት የማስጀመር እንጂ ሌላ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴ እየተደረገ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ግጭት የሚጋብዝ ነገር እንደሌለና የፕሪቶሪያ ስምምነት ዓላማዎች ተኩስ ማቆም፣ ሕገ መንግሥቱን ማረጋገጥና ሌሎችን ጨምረው ያብራሩት አቶ አማኑኤል፣ ሕወሓት ስምምነቱን ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር ተቀናጅቶ ከማስፈጸም በስተቀር ሌላ ፍላጎት የለውም ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በስምምነቱ ዙሪያ የፌዴራሉን መንግሥት ይወቅስ እንደነበር ጠቅሰው፣ ‹‹በመግለጫው ግን አቶ ጌታቸው በስምምነቱ እንቅፋት የሆንነው እኛ ነን ብሏል፣ ይህ አግባብ አይደለም፤›› በማለት ተችተዋል፡፡
በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት የትግራይ የቀድሞ ሠራዊት ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ሒደት (ዲዲአር) በሚመለከት፣ ‹‹ድርጅቱ እንቅፋት ሆኗል›› በሚል የቀረበውን ወቀሳም በተመለከተ ምላሽ ሰጥተዋል።
‹‹እኛ ዲዲአር ጊዜውን ባልጠበቀና የሕዝቡን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል መንገድ መፈጸም የለበትም አልን እንጂ ይቅር አላልንም፤›› በማለት የቀረበባቸውን ውንጀላ አቶ አማኑኤል አጣጥለዋል፡፡
ሕወሓት መፈንቅለ መንግሥት እየፈጸመ ነው ለሚለው፣ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሉ የድርጅቱን ውሳኔዎች እያስፈጸመ ነው በሚል ለቀረቡት ክሶችም የአፀፋ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
‹‹በስምምነቱ መሠረት ሕወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ከላይ ሆኖ ይመራል፡፡ በተለይም ደግሞ ከዞን እስከ ቀበሌ ባሉት መዋቅሮች ሕጋዊ መንግሥት ነው፡፡ ከላይኛው እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው የሕወሓት መዋቅር ነው፤›› ብለው፣ ‹‹ሕወሓት በማን ላይ ነው መፈንቅለ መንግሥት የሚያካሂደው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
‹‹በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥም ሃምሳ ሲደመር አንድ ውክልና ያለው ስምምነቱን የፈጸመው ሕወሓት ነው፡፡ በስምምነቱ መሠረት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተወያይተን ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ጊዜያዊ አስተዳደር ልናቋቁም ነው የተስማማነው፡፡ ስለዚህ እኛም ሆንን ሠራዊቱ ወደ መፈንቅለ መንግሥት አልገባንም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሕግ ለማስከበር እንቅስቃሴ ሲጀመር፣ ትግራይ ልትፈርስ ነው፡፡ ጦርነት ሊቀሰቀስ ነው፡፡ እያሉ ሕዝብን ማሸበር ተገቢ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ከሁለት ዓመታት በላይ ከባድ በሆነ ጦርነት ውስጥ አልፏል፡፡ ይህንን ያላገገመ ሥነ ልቦና ተጠቅሞ ሕዝብን ማሸበር ተገቢ አይደለም፤›› ሲሉም አቶ አማኑኤል የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዚዳንት ውንጀላዎች አጣጥለዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ግን፣ ‹‹የእኔ ምክትል የፀጥታ ኃይል ተወካይ ነው። የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ነው። አንዳንዴ የመንግሥት አካል መሆናቸውን ይረሱታል፡፡ የእኔ ምክትል ‹መንግሥት እንደ እዚህ ዓይነት ነገሮች መሥራት አለበት› ብሎ ሲያማርር እሰማዋለሁ። የትግራይን ሰላምና ፀጥታ የማስከበርን ሥራ፣ ጌታቸው በግሉ በብዕር ወይ በጋዜጣዊ መግለጫ ሊያረጋግጠው አይችልም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም፣ ‹‹የፀጥታ ኃይሉ የመንግሥት አካል መሆን አይደለም ችግር የሆነው። የፀጥታ ኃይሉን ወክለው የገቡ ሰዎች፣ ራሳቸውን የመንግሥት አካል አድርገው አለመቁጠራቸው ነው። ራሱን ነፃ አካል (Independent) አድርጎ የሚያምን ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ አማኑኤል በበኩላቸው፣ በትግራይ የፀጥታ ኃይልና በሕወሓት፣ እንዲሁም በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ያለውን ግንኙነት በማስመልከት፣ ‹‹ከድርጅቱ የተባረሩ ሕገወጥ አካላት፣ ሠራዊቱ ራሱን የቻለ ኃይል መሆኑን ዘንግተው ለማፍረስ ሲታተሩ እያየን ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ የሰጡት መግለጫም ይህንኑ ግልጽ ያደረገ ነው፡፡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በሚመለከትም ከዚህ ቀደም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፌዴራሉን መንግሥት ይወቅስ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በስምምነቱ እንቅፋት የሆንነው እኛ ነን ብሏል፣ ይህ አግባብ አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሕወሓት ሕገ መንግሥቱንና የፕሪቶሪያውን ስምምነት፣ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅሞችን መሠረት አድርጎ ነው ሲሠራ የቆየው፡፡ ስለዚህ ሠራዊቱ ሕወሓት ልኮት አይደለም ሥራውን እየሠራ ያለው፡፡ እዚህ ውስጥ ግን ብዙ የተበላሹ ነገሮች አሉ፡፡ እነሱን እስከምናስተካክል ድረስ ግን ሠራዊቱ ሕገ መንግሥቱንና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ነው እያስፈጸመ ያለው እንጂ የእኛም ሆነ የማንም ተላላኪ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ወደ አዲስ አበባ ትሄዳላችሁ ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ችግሩ አዲስ አበባ የመሄድ ወይም ያለመሄድ አይደለም ያሉት የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር፣ ‹‹ከፌዴራል መንግሥት ጋር የፕሪቶሪያው ስምምነት ያስተሳስረናል፡፡ ገና ያላጠናቀቅናቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚኖሩ ግንኙነቶች ዛሬም ይሁን ነገ ይቀጥላሉ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹መቼ ነው የምትሄዱት ለሚለው ጥያቄ የቀጠሮ ጉዳይ ነው የሚሆነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹አቶ ጌታቸው እንዳለው ሥልጣን ለመለመን አይደለም የምንሄደው፤›› ብለዋል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሕወሓት ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር ሆኖ እንዳቋቋመው በመግለጽ፣ በተለይም የፕሬዚዳንቱ ቦታ በሁለትዮሽ ስምምነት ላይ የተመሠረተ እንደሚሆንና ይህንን የተመለከተ ውይይት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ከኤርትራ መንግሥት ጋር በተያያዘ፣ ‹‹ከኢትዮጵያ መንግሥት ተቃራኒ በሆነ መንገድ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ምንም ዓይነት ሴራም ሆነ ግንኙነት የለንም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በተደጋጋሚ እንደገለጽነው የትግራይ ሕዝብ ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር ሰላምን ስለሚሻ ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከአማራም ሆነ ከአፋር ሕዝቦች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ብቻ ነው የምንፈልገው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ ምንም ዓይነት ግንኙነት የለም፡፡ የኤርትራ አመራሮችም ሆነ ሰላዮች ገብተዋል በሚል የሚናፈሰው መረጃ ‹በሬ ወለደ› ዓይነት ውሸት ነው፤›› ሲሉ አቶ አማኑኤል ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከኢሮብ እስከ ኦምሃጀር አካባቢ ድረስ ያሉ የትግራይ ግዛቶች ላይ ያለውን የኤርታራ ሠራዊት እንዲያስወጣ የፌዴራሉን መንግሥት መጠየቃቸውን ገልጸው፣ ‹‹በዚህ ጥያቄ መሠረት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከኤርትራ መንግሥት ጋር እንድንወያይ የፌዴራሉ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ ከዚያ ውጪ ግን አሁን የተለየ ወደ ግጭት የሚያስገባ እንቅስቃሴ የለም፤›› ብለዋል፡፡
የወረዳና የዞን አመራሮች ሹመት የመንግሥት ኃላፊነት ነው ተብሎ ለሚቀርበው መከራከሪያም ሲመልሱ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶሪያው ስምምነት ውጤት እንደሆነና ሕወሓት በ2012 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ የማገልገል መብት አለው ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን ረስቶ ሕወሓትን ከፖለቲካው ለማስወጣት ፖለቲካዊ አጠባ ሲያደርግ፣ ሕወሓት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲከፈትበት ከሕዝቡና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ሆኖ የማስተካከል መብት አለው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ቁልፍ ኃላፊነት ያላቸው አካላት የመዋቅሩ ጉዳይ በፌዴራል መንግሥት እጅ ብቻ እንዲሆን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው፣ የፌዴራሉ መንግሥት ግን ጣልቃ መግባት እንደማይፈልግና ሕወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን አሳታፊ በሆነ መንገድ እንዲያቋቁም ባስቀመጠው አቅጣጫና ስምምነት መሠረት እየተሠራ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ሐሙስ በአዲስ አበባ የሰጡትን መግለጫ አጠቃላይ ይዘት በሚመለከት በሰጡት አስተያየትም፣ ‹‹ጉዳዩ የትግራይ ክልል ሳይሆን የሌላ ሦስተኛ ወገን እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡ የትግራይ ሕዝብ፣ የፀጥታ ኃይሉም ሆነ የትግራይ ልሂቃን ለዚህ አያንሱም፡፡ ጉዳዩ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እጅ እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፣ ተገቢነትም የለውም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሕገ መንግሥት ትግራይ ውስጥ ቢከበር የኢትዮጵያ መንግሥት የሚጎዳው ነገር አይኖርም፡፡ ወደ ግጭት የሚያስገባ ነገርም የለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የሰላምና ፀጥታ ካቢኔ ቢሮ፣ በክልሉ እየተካረረ የመጣው ፖለቲካዊ ውጥረት ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳያመራ በሰከነ መንፈስ በውይይት ለመፍታት ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ፍላጎት ከማጣት፣ እንዲሁም መጠፋፋትን በመምረጥ ሳይሳካ ቀርቷል ሲሉ በተመሳሳይ ቀን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቢሮው ፖለቲካዊ ውጥረቱ በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ሕዝቡን ወደ ከፋ ሁኔታ እያስገባ ነው ያለ ሲሆን፣ ከሰሞኑም ሁኔታውን ይበልጥ የሚያባብስ ሁኔታ እንዳለና ችግሩን የሚያባብሱ መግለጫዎችና ውሳኔዎችም እየተሰጡ እንደሆነ ገልጿል፡፡
‹‹የተፈጠረው ችግር ጥበብ በተሞላው የሰከነ መንገድ መፈታት ሲቻል የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቅ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፤›› በማለት የወቀሰው የፀጥታ ካቢኔ ቢሮው፣ ‹‹ችግሩ ውጫዊ መልክ እንዲይዝና ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር መጠራጠር ውስጥ ከመክተት ባሻገር ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፤›› ብሏል፡፡
‹‹በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት የተመለከቱ መልሶ ማቋቋምና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚያስተሳስሩን ቢታወቅም፣ መሰል ከክልሉ አቅም በላይ ያልሆነን አጀንዳ ሌላ አካል እንዲፈታው መጠየቅ አሳፋሪ ነው፤›› በማለትም ውድቅ አድርጎታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ይህንን ተከትሎ የሚኖር ማንኛውም የኃይል እንቅስቃሴ ችግሩ ሌላ መልክ እንዲይዝና ሕዝብንም አለመረጋጋት ውስጥ የሚከት እንደሆነ አክሎ ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የኒውዚላንድ፣ የጃፓን፣ የኖርዌይ፣ የቤልጂየም፣ የቡልጋሪያ፣ የቼክ ሪፐብሊክ፣ የዴንማርክ፣ የጀርመን፣ የአየርላንድ፣ የግሪክ፣ የስፔን፣ የፈረንሣይ፣ የጣሊያን፣ የሉክዘምበርግ፣ የሃንጋሪ፣ የኔዘርላንድስ፣ የኦስትሪያ፣ የፖርቹጋል፣ የሮማኒያ፣ የስሎቬንያ፣ የፊንላንድ፣ የስዊድን ኤምባሲዎችና የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ በትግራይ ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት በተመለከተ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
በመግለጫቸውም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ለውጦችን፣ ሁኔታዎችንና እየተባባሰ ያለውን ውጥረት በትኩረት እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ‹‹እ.ኤ.አ. ኅዳር 2022 ለተፈጸመው የግጭት ማቆም ስምምነት ሙሉ ድጋፋችንን እንደምንሰጥ ደግመን አጽንኦት እንሰጣለን፤›› ብለዋል። ይህ ስምምነት የመሣሪያ ድምፅ ፀጥ እንዳደረገም አመልክተው በፍፁም ወደ ሁከት፣ ግጭትና ጦርነት መመለስ እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡
ሁሉም ወገኖች አስቸኳይ ውይይት በማድረግ ውጥረቱን በማርገብ ስምምነቱን እንዲጠብቁም ነው ያሳሰቡት፡፡ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም ገልጸዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ‹‹ኤክስ›› ገጻቸው ባሠፈሩት ጽሑፍ ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኃላ ከአሜሪካ፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሣይ፣ ከጣሊያን፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ እንዲሁም በአውሮፓ ኅብረት አምባሳደሮች ጋር በትግራይ ስላለው ሁኔታና አስተዳደራቸው እየገጠመው ስላለው ፈተና ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመው ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ በአዲስ አበባ እያደረጉት ባለው ቆይታ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በተገኙበት፣ የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
