በጋዜጣዉ ሪፓርተር

March 16, 2025

በሃይማኖት ደስታ

በአዲስ አበባ ከተማ መደበኛ ባልሆነ ንግድ መሰማራት የሚችሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ መሆናቸውን የሚደነግግ ደንብ መፅደቁ ታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ4ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ስብሰባው ተወያይቶ ካፀደቃቸው ረቂቅ ደንቦች መካከል፣ ‹‹መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ›› ይረዳ ዘንድ እንደተዘጋጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ›› ደንብ ቁጥር 184/2017 ሆኖ ከፀደቀው ሕግ አጠቃላይ ይዘት ጋር በተገናኘ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህን ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ ‹‹ካቢኔው ያፀደቀው አዲሱ ደንብ በመዲናዋ አንድ ግለሰብ መደበኛ ባልሆነ ንግድ ላይ ሊሰማራ የሚችለው፣ የአዲስ አበባ ከተማ መታወቂያ ካለውና የከተማዋ ነዋሪ ከሆነ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ አስገዳጅ መሥፈርት አስቀምጧል፤›› ብለዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪ መሆን የሚለው መሥፈርት እንዴት በአስገዳጅነት ሊቀመጥ ቻለ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተክሌ፣ ‹‹የከተማ ነዋሪነት ጉዳይ አንዱ መሥፈርት ሆኖ ሊቀመጥ የቻለው፣ በዚህ ንግድ የሚሰማሩ አካላት ሕጋዊ ሆነው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡ በዚህ የንግድ ሰንሰለት የሚሰማሩ ዜጎች ሕጋዊነት በክልል መታወቂያ አይረጋገጥም ማለት ግን አይዳለም ሲሉ፤›› አስረድተዋል።

‹‹ነገር ግን በአዲስ አበባ ከተማ ጫና አለብን፡፡ ከክልሎች (ከገጠር ወደ ከተማ) የሚደረግ ፍልሰት አለ፣ ይኼን ፍልሰት ማበረታታት የለብንም፡፡ ስለዚህ በዚህ የንግድ ሥርዓት ላይ የሚሰማራ ሰው ቋሚ አድራሻ ታውቆ፣ የከተማ አስተዳደሩ መታወቂያ ሊኖረው ይገባል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ለመቆጣጠር አያስችልም፡፡ የመሥሪያ ቦታ ሰጥተህ ነጋዴውን ልታጣው ትችላለህ፡፡ ነጋዴው ገብቶ የሚወጣበት ዓይነት የንግድ ሥርዓት ነው የምንዘረጋው፡፡ ይህ ደግሞ የንግድ ሥርዓቱን ለማስተዳደር፣ ለመቆጣጣር፣ የንግድ ዕድሳት ለማድረግ፣ የገቢ ደረጃውን ተከታትሎ ግብር ለማስከፈል፣ እንዲሁም ከኢመደበኛ ወደ መደበኛ ለማሸጋገር ያስችላል፡፡ መደበኛ ባልሆነ ንግድ የሚሰማሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ስለመሆናቸውና በዚህ ሥራ በተወሰነ የጊዜ ገደብ፣ ዘርፍና ቦታ መሰማራትና መሸጋገር እንደሚችሉ እርግጠኛ መሆን አለብን ከሚል ዕሳቤ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም እንዳለ የተናገሩት ኃላፊው፣ ለከተማዋ የፀጥታና ደኅንነት ሥጋት እንዳይሆን፣ የትራፊክ እንቅስቃሴን እንዳያስተጓጉል፣ ሕግና ሥርዓት ተከትለው የሚሠሩ ነጋዴዎችን እንዳይጎዳ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት ተፈጻሚነቱን መከታተል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደ አዲስ ተዘጋጅቷል።

ከዚህ በፊት ደንብ ቁጥር 88/2000 የሚባል ሕግ ወጥቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተክሌ፣ በአፈጻጸሙ ላይ በነበረበት ክፍተት ምክንያት በአግባቡ መተግበር ባለመቻሉ፣ ያንን አሻሽሎ እንደ አዲስ ማውጣት ማስፈልጉን ገልጸዋል። አዲሱ ደንብ ከዚህ በፊት ሥራ ላይ ውሎ የነበረውን ደንብ በመተካት ሥራ እንደሚውልም ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል።

ረቂቅ ደንቡ መደበኛ ባልሆነ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች በተለያዩ የንግድ ዓይነቶች ተሰማርተው እንዲሠሩ የታሰበ ነው ተብሏል። ‹‹ይህም በከተማዋ መሬትና ልማት ቢሮ ለመነገጃ ተብሎ በተለዩ ዋና ዋና መንገዶችና በሚሰጡ ሌሎች ቦታዎች ገደብ ተቀምጦ፣ ለተወሰኑ ሰዓታት እንዲሠሩ የሚፈቀድበት ሒደት ይኖራል ማለት ነው፤›› ሲሉ አቶ ተክሌ ተናግረዋል። ይኼ ሲሆን ግን ለዚህ ንግድ ተብሎ የሚመረጡ ቦታዎች፣ በመደበኛ የንግድ እንቅስቃሴው ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡

መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ የብቃት ማረጋገጫና የተለየ የፈቃድ ዓይነት እንደማያስፈልገው የገለጹት ቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹በደንቡ መሠረት የሚነገዱ ንግዶች የገንዘብ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆነ፣ ማለትም በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚያገኙት ገቢ 200 ሺሕ ብር ከደረሰ፣ ወደ መደበኛ ንግድ የሚሸጋገሩበት አሠራር ይኖራል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በዚህ የንግድ እንቅስቃሴ በእኛ ዕሳቤ ተንቀሳቅሰው ሻይ፣ ቡና፣ ሶፍት፣ ማስቲካና መፋቂያ የሚሸጡትን ጭምር ያካትታል፤›› ሲሉ ጠቅሰዋል። ሆኖም በጣም ዝቅተኛ ገቢ የሚገኝባቸው ናቸው ተብሎ የሚታመኑ የንግድ ዓይነቶች ሲኖሩ፣ የከተማዋ ንግድ ቢሮ በመመርያ ሊወስን የሚችልበትን ዕድል ረቂቅ ደንቡ ማካተቱን አቶ ተክሌ አያይዘዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው ረቂቅ ደንብ የማስተግበር ኃላፊነት የተሰጣቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ፣ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣንና የፀጥታ ተቋማት እንደ ሁኔታው መቀየርና መሻሻል የነበረባቸው ጉዳዮች ላይ ቅንጅት ፈጥረው በጋራ እየሠሩ እንዳልነበረ ያወሱት የቢሮ ኃላፊው፣ አሁን ግን ሰብሰብ ብለው ውሳኔ የሚያስተላልፉበት አሠራር ረቂቅ ደንቡ ማካተቱን ገልጸዋል።

በከተማ ደረጃ በምክትል ከንቲባ የሚመራና ተጠሪነቱ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሆነ አስተግባሪ ግብረ ኃይል እንደሚኖርም አቶ ተክሌ ተናግረዋል። ግብረ ኃይሉ ከቦታ ልየታና ከንግድ እቅስቃሴዎች ጋር የሚኖሩ አጠቃላይ ሁኔታዎችን እየገመገመ ውሳኔ እያሳለፈና ዕርምጃ እየወሰደ መሥራት እንዲቻል የተቋቋመ ነው ብለዋል።

ግብረ ኃይሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ተካተውበታል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት በኩል የሚጨመሩ ተቋማት እንደሚኖሩ ተነግሯል።

ግብረ ኃይሉ መደበኛ ያልሆነ ንግድ መደበኛውንና አጠቃላይ የገበያ ሥርዓቱን የማይጎዳ መሆኑን ማስተዳደር፣ የግብይት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ፣ የገቢ መጠን መለየት፣ ከኢመደበኛ ወደ መደበኛ የሚደረጉ የሽግግር ሁኔታዎች ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠትና የማሻገር ሥራዎችን እንደሚከናወን ተብራርቷል።

በኢመደበኛ ንግድ ለመሰማራት ከተቀመጡ መሥፈርቶች መካከል ዕድሜ ተጠቃሹ ሲሆን፣ ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች ብቻ በዘርፉ ፈቃድ አውጥተው መሥራት እንደሚችሉ ተገልጿል። ደንቡ ዜጎች በማኅበር ተደራጅተው የሚሠሩበት ዕድል ይዞ መምጣቱም ተመልክቷል።

የከተማው ንግድ ቢሮ በሚያወጣው መሥፈርት (ስታንዳርድ) መሠረት የወረዳ ንግድ ቢሮዎች ምዝገባ እንደሚፈጽሙም ተጠቅሷል። ከዚያም በተዋረድ ከወረዳ ወደ ክፍለ ከተማ፣ ከክፍለ ከተማ ወደ ማዕከል የመረጃ ፍሰት ይኖራል ተብሏል፡፡

አንድ ግለሰብ እነዚህና ሌሎች የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን ሲያሟላ በዘርፉ ተሰማርቶ ለመነገድ ፈቃድ እንደሚያገኝ የጠቆሙት አቶ ተክሌ፣ ዓመታዊ የገቢ ግብር መክፈል ግዴታ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል። በዚህ የንግድ ዓይነት ላይ የሚሰማሩ ዜጎች በደረጃ (ሐ) ግብር ከፋዮች ዝርዝር ውስጥ ይጠቃለላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

እነዚህ ነጋዴዎች የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ ከሆነ ደረሰኝ መቁረጥ እንደሚኖርባቸው ተገልጿል። ይኼ ማለት ‹‹ያለ ደረሰኝ ግብይት መፈጸም አይችሉም›› ማለት እንደሆነ አቶ አክሌ አስረድተዋል። የተሰጠው ፈቃድ ለባለቤቱ ስለሚሆን፣ የወሰደው ሰው በውክልና ለሌላ ግለሰብ አሳልፎ መስጠትና ማስነገድ እንደማይፈቀድለትም ተጠቁሟል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ግለሰብ የተቀመጡ ክልከላዎችን አልፎ በሕግ ያልተፈቀዱ ተግባራትን ሲፈጽም የተገኘ እንደሆነ እንደ ማንኛውም የወንጀል ድርጊት አስቀድሞ የንግድ ፈቃዱ እንዲሰረዝ ከተደረገ በኋላ፣ በመደበኛ የወንጀል ሕግ እንደሚጠየቅ የጠቀሱት ኃላፊው፣ የፍትሕ ብሔር ተጠያቂነትም በዚያው ደረጃ አብሮ ይኖራል ብለዋል። ሆኖም አስተዳደራዊ ዕርምጃ ተወስዶ የንግድ ፈቃዱ ስለመቀማቱ ቅሬታ ያለበት ማንኛውም አካል በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ቅሬታውን የሚያቀርብበት አሠራርና ማዕቀፍ መቀመጡን አያይዘዋል። ቅሬታውን የተቀበለው አካል ደግሞ ጉዳዩን አጣርቶ በአሥር የሥራ ቀናት ምላሽ መስጠት እንዳለበት በደንቡ መካተቱን አቶ ተክሌ አስረድተዋል። እነዚህን ነጋዴዎች ለመከታተል የሚያስችል የደረት ባጅ፣ ምናልባት ልዩ መለያ (ባር ኮድ) እንዲኖረው ተደርጎ ሊሠሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በመርህ ደረጃ መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ንግድ እንደማይበረታታ የጠቆሙት አቶ ተክሌ፣ ‹‹ከዚህ በፊት መደበኛ ነጋዴው ያልተሸጠለትን ዕቃ ወደ ውጭ አውጥቶ የሚያስነግድበት ተለምዷዊ አሠራርን በመስበር፣ በዚህ ንግድ ተሰማርቶ ያለው ግለሰብ ወደ መደበኛ ንግድ የሚሸጋገርበት ሕጋዊ ሒደት እንዲኖር በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሠራበት ነው፤›› ብለዋል።  

‹‹ደንቡን ለማሻሻልና እንደገና ለማዘጋጀት በእኛ በኩል ወራት ወስዷል፤›› ያሉት የቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹ይኼ ንግድ እንዴት ይመራል? እንዴትስ ሕጋዊ ተደርጎ ማስተዳደር ይቻላል? የሚሉ ጉዳዮችን በሚመለከት የአገሮች ተሞክሮ ላይ መሠረት ያደረጉና ከዓመት ያላነሰ ጊዜ የፈጁ የተለያዩ ጥናቶች ተደርግዋል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የፀደቀው ደንብ ከየካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ብዥታ እንዳይፈጥር ከንግድ ቢሮ ጋር በመሆን የማሳወቅና የስርፀት ሥራዎች ከተከናወኑ በኋላ ወደ አፈጻጸም ይገባል ተብሏል።

በዚህ የንግድ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ አካላትን መመዝገብ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠትና በንግድ ሥርዓቱ ላይ ማሰማራት ስለሚሆን በተወሰኑ ሳምንታት ውስጥ ደንቡ ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከ20,000 ሺሕ በላይ ዜጎች በኢመደበኛ ንግድ ተሰማርተው ይገኙ የነበረ ሲሆን፣ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት አብዛኞቹ ተበታትነው አሁን የቀሩት 4,880 ያህል እንደሆኑ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ያገኘው መረጃ ያሳያል።