ተመስገን ተጋፋው

March 16, 2025

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለጥራጥሬና ለቅባት እህሎች የወጣው የዋጋ ተመን፣ በዓለም አቀፍ ገበያ መሠረት መሆን አለበት ሲሉ ላኪዎች ጥያቄ አቀቡ፡፡

ሚኒስቴሩ በዓለም አቀፍ ገበያ ከሚሸጥበት በተለየ ሁኔታ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሸጡ የዋጋ ተመን በማውጣቱ፣ በርካታ ላኪዎች ከውድድር ውጪ ሆነው ከገበያው ለመውጣት እየተገደዱ መሆናቸውን፣ ላኪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ላኪዎች በአሁኑ ወቅት የጥራጥሬና የቅባት እህሎች በዓለም አቀፍ ገበያ እየተሸጡበት ያለው ዋጋ በቶን ከ1,400 እስከ1,600 ዶላር እንደሆነ፣ ነገር ግን ሚኒስቴሩ እንዲሸጡ ያስቀመጠው የዋጋ ተመን በቶን 1,750 ዶላር መሆኑም ተገልጿል፡፡

‹‹የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የራሱን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ለማሳመርና ዶላር ለመሰብሰብ ብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጥበትን የዋጋ ተመን ከፍ አድርጓል፤›› በማለት ወቀሳ ያቀረቡት ላኪዎች በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ ገዥ ማጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ ከፍ ያለ ዋጋ ተመን ምክንያትም በርካታ ላኪዎች ምርታቸውን ይዘው በመቀመጣቸው፣ ምርቱ ከመበላሸቱ ባለፈ በወቅቱ ተሸጦ ማምጣት የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹በዚህን ያህል ዶላር ይሸጥ›› ብሎ ማውጣቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለጨመረ፣ በአፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት እንደሚኖርበት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ላኪዎች አሳስበዋል፡፡

በተለይ ላኪዎች የዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ እስኪስተካከል ድረስ ምርቱን ሲይዙ የምርት ዘመኑ እንደሚያልፍበት አስታውሰው፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የላኪዎችን ችግር ሳይሆን እያየ ያለው  የራሱን ጥቅም ብቻ ነው፤› ያሉት ላኪዎቹ፣ ‹‹ነጋዴው በዚህን ያህል ዋጋ መሸጥ አያዋጣኝም ይበል እንጂ፣ መንግሥት እዚህ ጉዳይ ውስጥ እጁን ማስገባት የለበትም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከግዥና ከሽያጭ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘም የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ላኪዎች ከአርሶ አደሩ ወይም ከአቅራቢው በሚገዛበት ጊዜ በርካታ ችግሮች እንደሚገጥሙ፣ ለአብነትም ግዥ ከተከናወነ በኋላ በሚጓጓዝበት ወቅት በየመንገዱ ‹‹የኮቴ አምጡ›› የሚሉ አካላትን መጥቀስ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

‹‹መንግሥት እነዚህን ሁሉ ችግሮች ሳይፈታ በላኪዎች ላይ ለዓለም አቀፍ ገበያ ተመን በማውጣት በዚህን ያህል መሸጥ አለባችሁ ማለቱ ተገቢነት የሌለው ነው፤›› ሲሉም ወቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ‹‹መንግሥት የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ፣ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጥበት የተለያዩ አማራጮች ተፈጥረዋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በተለይ ላኪዎች ለአምራቾች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እንዲያመርቱ ከተደረገ በኋላ፣ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ በማስመዝገብ መላክ የሚችልበት አማራጭ መፈጠሩንም ጠቁመዋል፡፡  

በሌላ በኩል ደግሞበ ቨርቲካል ኢንተግሬሽን (Vertical Integration) አማካይነት ላኪዎች መላክ የሚችሉበት አማራጭ ተፈጥሯል ያሉት ላኪዎቹ፣ ነገር ግን በሚኒስቴሩ ሳምንታዊ ማነፃፀሪያ ተብለው እየወጡ ያሉ የዓለም አቀፍ የመሸጫ ዋጋ ተመን ላኪዎች ላይ ችግር መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡

የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ዋጋ ተመን በሁሉም አገሮች የተለያየ እንደሆነ፣ በተለይ ምርቶቹን የሚገዙ አገሮች የኢትዮጵያ ሰሊጥ ተመራጭ እንደሚያደርጉም አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘለዓለም ዘውዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የንግድና ቀጣዊዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራጥሬና የቅባት አህሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሸጥ ያስቀመጠውን የዋጋ ተመን ማስተካከያ እንዲያደርግ ማኅበሩ በየጊዜው ጥያቄ እያቀረበ ነው፡፡

ይሁንና እስካሁን ምንም ዓይነት ማስተካከያ እንዳልተደረገ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በአሁኑ ወቅት የጥራጥሬና የቅባት እህሎች እየተሸጡ ያለበት ዋጋ አንድ ቶን በ1,650 ዶላር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በአሁኑ ወቅት የጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሸጡ ያስቀመጠው ዋጋ በቶን 1,750 ዶላር እንደሆነ ጠቅሰው፣ ዘርፉ ዓለም አቀፉን የዋጋ ተመን ማማከል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር ውይይት አለመካሄዱን ገልጸው፣ ስብሰባ ተካሄዶ ውሳኔ ሲሰጥም ወይ ባለበት ይቀጥላል ወይም ትንሽ የዋጋ ቅነሳ ይደረግበታል የሚል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ገበያ የዋጋ ተመን በጣም መቀነሱን፣ ይህም የሆነበት ምክንያት ዋና ገዥ የሆነችው ቻይና የመግዛት ፍላጎቷ በመውረዱ እንደሆነ አክለዋል፡፡

በዚህ መሠረት ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የዓለም አቀፍ ዋጋን ተመን አውርደው ምርቶቻቸውን እየሸጡ እንደሚገኙ፣ ኢትዮጵያ ላኪዎች ግን ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አቶ ዘለዓለም አስረድተዋል፡፡

ታንዛኒያ፣ ቶጎና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምርቶቻቸውን ለቻይና በአንድ ቶን 1,400 ዶላር እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸው፣ ‹‹መንግሥት የዋጋ ተመን ማስተካከያ ባለማድረጉ የእኛ አገር ላኪዎች ከውጭ ንግድ እያገኙት ያለው ገቢ አነስተኛ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ለማነጋገር የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡