የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው

ዜና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ምክረ ሐሳብ እንዲቀርብ ኢትዮጵያ…

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: March 16, 2025

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ከምኞት ባለፈ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚያስችሉና አፈጻጸሙን የሚያፋጥኑ ምክረ ሐሳቦች፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የባለሙያዎች ኮሚቴ በኩል እንዲቀርብ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ጠየቁ።

ሚኒስትር ደኤታዋ ስምምነቱ በተፈለገው ፍጥነት መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እንዳይደረግ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ሲሉ የጠቀሷቸው የመሠረተ ልማት ግንባታ ክፍተቶች፣ የአገሮች ወጥነት የጎደላቸው የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረቶችና በአገሮች መካከል ያለው የኢኮኖሚ አቅም ልዩነቶችን ዕውቅና እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

ከጠቀሷቸው ጉዳዮች እኩል ወሳኝ ሲሉም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ሽግግር አጀንዳ የአኅጉሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆኑትን፣ በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶችንና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አካታች ያደረገ መሆን ይገባዋል ብለዋል።

ሚኒስትር ደኤታዋ የባለሙያዎች ኮሚቴው ስምምነቱን በተፋጠነ መልኩ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር እየተጋረጡበት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት፣ ዋነኛውን ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚታመንም ጠቅሰዋል።

‹‹የባለሙያዎች ኮሚቴው ስትራቴጂክ፣ ተግባራዊ መደረግ የሚችሉ ምክረ ሐሳቦች ማቅረብ የሚችልበት አቅም ያለው መሆን፣ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ምኞት ብቻ ከመሆን ባለፈ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችለው የለውጥ መሣሪያ እንዲሆን ያስችለዋል፤›› ሲሉ የሚቀርቡት ምክረ ሐሳቦች ጥናቶችን በተገቢው ቦታና ሁኔታ ላይ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ፣ አጋርነቶች አባል አገሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎችና የአኅጉሪቱ ቀጣናዎች መካከል ስኬታማ ትብብር መፍጠር የሚያስችሉ ሆነው እንዲቀረጹ አሳስበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያዘጋጀው 43ኛው አኅጉራዊ የኢኮኖሚ ልማት፣ የገንዘብና የፕላን ሚኒስትሮች ጉባዔ በባለሙያዎች ደረጃ በአዲስ አበባ ከረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ሰመሪታ በጉባዔው ባደረጉት ንግግር፣ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ለማፋጠን፣ አገሮች በመካከላቸው ያለውን የመሠረተ ልማት ትስስር የሚያሳልጡ ግንባታዎች፣ ኢንቨስትመንትን የሚያሳድጉ የንግድ ፖሊሲዎች፣ የጉምሩክ ሒደትን የተመለከቱ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶች ላይ የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።