ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

March 16, 2025

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሰጡት መግለጫ ብዙ ጉዳዮችን በግልጽ ያስቀመጠ ነበር፡፡ ትግራይ ክልልን ከሁለት ዓመታት አሰቃቂ ጦርነት እንዲላቀቅ ያደረገው የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ከእነ አካቴው መፍረሱ ይፋ ባይሆንም፣ ነገር ግን እሳቸው ሲመሩት የቆዩትና በስምምነቱ መሠረት ተመሥርቶ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር መደበኛ ሥራውን እየሠራ መቀጠል የሚችልበት ሁኔታ ችግር ውስጥ መውደቁን ያረጋገጠ ይመስል ነበር፡፡

ይህንን በተመለከተም፣ ‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፌዴራል መንግሥቱ አካል ነው፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በሕግ የተቋቋመው አስተዳደር ግን ‹‹ሥልጣን ፈላጊ›› ባሉት የሕወሓት ቡድን የተነሳ ሥራውን እየሠራ የሚቀጥልበት ዓውድ መነፈጉን በግልጽ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በአዲስ አበባ መግለጫ እየሰጡ በነበሩበት ሰዓትና ከዚያ ወዲህም ቢሆን፣ በትግራይ በተለያዩ ከተሞች የሕወሓት አንደኛው ክንፍ ይህንኑ የተለያዩ ዕርምጃዎች ሲወስድ ይስተዋል ነበር፡፡ የሕወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሆኑት አቶ አማኑኤል ፍሰሐና ፍሰሐ ሀብተ ጽዮን (ዶ/ር) በትግርኛና በእንግሊዝኛ እያፈራረቁ በሰጡት መግለጫ፣ ወደ አዲስ አበባ የሄዱት አቶ ጌታቸው ረዳን ‹‹ሕገወጥና ብሔራዊ ክህደት የፈጸሙ›› እያሉ ሲያወግዙ ተደምጠዋል፡፡

የሕወሓት ክንፍ ከመግለጫ ምላሽ ባለፈ ግን መሬት ላይ ዕርምጃ መውሰዱ መቀጠሉም ሲነገር ሰንብቷል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንጋፋ የትግራይ ፖለቲከኛ፣ ‹‹በክልሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቆጣጠራቸው የነበሩ የመንግሥት ቢሮዎችንና መዋቅሮችን የሕወሓት ኃይል እየተቆጣጠረ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር ሲሠሩ የነበሩ የሥራ ኃላፊዎች በሕወሓት መታሰርና መሳደድ ጀምረዋል፤›› የሚሉት ፖለቲከኛው የሕወሓት ሌላው ክንፍ የእነ ጌታቸውን መዋቅር ሙሉ ለሙሉ እንደተቆጣጠረው ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ በትግራይ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ሪፖርተር የጠየቃቸው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሳልሳዊ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃነ አጽበሃ ከባድ ሥጋት ያጠላበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹መቀሌ ነው ያለሁት፡፡ አቶ ጌታቸው የጦር መኮንኖቹን አሰናበቱ የሚለው ዜና ከተሰማበትና በሕወሓት ውስጥ ውጥረቱ መባባስ ከጀመረበት ቀን ጀምሮ ፍርኃትና ጭንቀት በሕዝቡ ዘንድ መፈጠሩን እያስተዋልኩ ነው፡፡ ባንኮች አካባቢ ረዣዥም ሠልፎች ይታያሉ፣ ገበያም አካባቢ በእጥፍ ጨምሯል፣ ሌላም አካባቢ እንደዚሁ ነው፡፡ በዚህ ግርግር ለመጠቀም አንዳንድ ነጋዴዎች ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝቡን ለብዙ ጉዳት ዳርጎታል፡፡ አሁንም ድረስ ልጆቻቸው የት እንደደረሱ የማያውቁ፣ ብዙ የቤተሰባቸው አባል ወደ ጦርነት ገብቶ የረገፈባቸው ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ የከፈለው ዋጋ ከባድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስሜቱ አሁንም ገና ትኩስ ነው፡፡ በቅጡ እርማቸውን ያላወጡ እናቶች አሉ፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ በሕወሓት መካከል መሰንጠቅ መፈጠሩና ሌላ ዙር ጦርነት ሊፈጠር ነው የሚል ሥጋት መጫሩ ነገሩን አባብሶታል፡፡ አስከፊ ጠባሳ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያሳረፈው የኤርትራ ሠራዊት ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች አገሮችም በዚህ ዙር ጦርነት ሊሳተፉ ይችላል መባሉ ደግሞ የሕዝቡን ጭንቀት አባብሶታል፡፡ በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ሰማይ ደግፎ ይዞ ነው ያለው ማለት እችላለሁ፤›› በማለት በትግራይ ያጠላውን የሥጋት ደመና ገልጸውታል፡፡  

ከሰሞኑ በትግራይ ፖለቲካ የተፈጠረው ቀውስ በፓርቲው ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሲብላላ የቆየው መሰንጠቅ ወይም የሥልጣን ሽኩቻ ውጤት መሆኑ ይነገራል፡፡ አንዳንዶች የአቶ ጌታቸው ረዳን ቃል ተውሰው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ተፈጽሞበታል ቢሉም፣ ሆኖም በተቃራኒው የቆመው የሕወሓት ኃይል ግን ‹‹ሕግ የማስከበር ዕርምጃ›› መውሰዱን ነው የተናገረው፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጉዳዩን መፈንቅለ መንግሥት ቢለውም ሆነ የሕወሓት ሌላው ክንፍ በፊናው ጉዳዩን ሕግ ማስከበር የሚል ስም ቢያወጣለትም፣ በወቅቱ የተፈጠረው ክፍፍልና ፍጥጫ የጦርነት ሥጋት መጋረጡን ሁሉም ይስማሙታል፡፡ የሕወሓት የእርስ በእርስ ግብግብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መሬት ላይ ያልወረደ የቃላት መወራወርና የሚዲያ ውዝግብ ሆኖ ነበር የዘለቀው፡፡ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ለረዥም ጊዜ ገለልተኛ ነኝ ሲል የቆየው የጦር ኃይሉ ከፍተኛ መኮንኖች የእነ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ሕወሓት ቡድንን ደግፈው መግለጫ እስካወጡበት ጊዜ ድረስ፣ የትግራይ ፖለቲከኞች ውዝግብ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ እንደገለጹትም ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት›› ሆኖ ነበር የከረመው፡፡

የጊዜያዊ አስተዳደሩና የሕወሓት ጽሕፈት ቤቱ ቡድን አንዱ ሌላውን ከሥልጣን አንስቼዋለሁ መባባላቸውም ሆነ አንዱ ሌላውን ዕውቅና መንፈጉ ባለፉት ወራት የተለመደና በተደጋጋሚ የታየ ሁኔታ ነበር፡፡ ገለልተኛ ሆኖ መቆሙ የሚነገረውን የፀጥታ ኃይሉን ስም እየጠሩ አንዱ በሌላው ላይ ዕርምጃ እንዲወስድና ሕግ እንዲያስከብር መጋበዛቸውም የተለመደ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ፌዴራል መንግሥቱን፣ ምርጫ ቦርድን፣ እንዲሁም የፕሪቶሪያ አደራዳሪዎችን በስም እየጠሩ አንዱ የሌላውን ሕገወጥ አካሄድ እንዲያርሙ ጥሪ ማቅረባቸውም የተለመደ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ጦሩ (የፀጥታ ኃይሉ) አንድ ወገን ለይቶ ከሕወሓት ጽሕፈት ቤት ጎን ቆሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ‹‹ብሔራዊ ክህደት የፈጸመ ቡድን›› ብሎ ሲፈርጅ ሁሉም ነገር አፍጦ የወጣ መሰለ፡፡

ጦሩ ከሕወሓት ጽሕፈት ቤት ጎን ወግኖ መቆሙን ተከትሎ በርካታ የትግራይ ወጣቶች በየከተሞቹ ተቃውሞ በማድረግ የጦሩንና የሕወሓትን አቋም ሲያወግዙ ታይተዋል፡፡ በትግራይ ሰላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን ያሉ ወገኖች በሠልፍ አደባባይ ወጥተው የፀጥታ ኃይሉ ገለልተኛነቱን ጠብቆ እንዲቆም አሳሰቡ፡፡ የሕወሓት የእርስ በእርስ ችግር ተወግዶ ሁለቱም የሕወሓት ቡድኖች በጋራ የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር እንዲሠሩ ሕዝቡ በአደባባይ ተቃውሞዎች ሲጠይቅ ነበር፡፡

የሁለቱ ሕወሓት ቡድኖች ውዝግብ በጦዘ ቁጥር በየመሀሉ ሲሆን እንደሚታየው ሁሉ፣ ከዚያ ወዲህም የሁለቱ ኃይሎች መሪዎች ሲጨባበጡና ጎን ለጎን ቆመው የሚታዩባቸው ፎቶ ግራፎችና ምሥሎች ይፋ መሆኑ ቀጥሎ ነበር፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) እና በአቶ ጌታቸው ኃይሎች መካከል ውጥረቱ ረግቦ ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጠረ የሚል ስሜት ሲፈጥሩ ቢታይም፣ ነገር ግን ወዲያው በመግለጫ መካሰሱና መወዛገቡ ተመልሶ ቦታውን ሲተካ መታየቱ ቀጥሎ ነበር፡፡

‹‹ሲሞላ ይፈሳል ሲከር ይበጠሳል›› እንደሚባለው ይህ የሁለቱ ኃይሎች ውዝግብ ተወጥሮ በመጨረሻ ከሰሞኑ ፈንድቷል፡፡ አቶ ጌታቸው በደብዳቤ ሦስት የጦር መኮንኖችን ማገዳቸውን ተከትሎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሕወሓት ጋር መጋጨት ብቻ ሳይሆን፣ የፀጥታ ኃይሉም እንደማይታዘዘው በይፋ ታየ፡፡ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው የሁለቱ ኃይሎች ውዝግብ በይፋ ፈንድቶ በአዲጉዶም፣ በአዲግራትና በመቀሌ ከተሞች ሰዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭትና የተኩስ ልውውጥ ተደረገ፡፡ ሕወሓት በጦሩ ታጅቦ የመንግሥት ቢሮዎችን መቆጣጠር ሲጀምር አቶ ጌታቸው ወደ አዲስ አበባ መግባታቸው ተሰማ፡፡ አቶ ጌታቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩን ከሞት ለመታደግ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ከበቂ በላይ ምክንያት አለው ማለታቸው በትግራይ ክልል ታላቅ ብሔራዊ ክህደት ፈጸሙ በሚል ጡዘቱ በረታ፡፡

አሁን ትግራይን የተቆጣጠረው የሕወሓት ኃይል ከፌዴራል መንግሥት ጋር ዳግም ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ ከኤርትራ ሠራዊት ጋር አጋርነት መፍጠሩ እየተነገረ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ወደ ቦታው ለመመለስ በሚል ወደ ትግራይ ከገባ በትግራይ ቀጣናዊ ጦርነት ሊፈጠር ይችላል እየተባለ ነው፡፡

በትግራይ የተፈጠረው ምን እንደሆነ የበለጠ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጋበዙት አንጋፋው ፖለቲከኛ ነገሩ ወደ ጦርነት እያመራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡን በዲፕሎማሲ ከሠራና ሁሉም ወገን ለሰላም ዝግጁ ከሆነ ሰላም ሊመለስ ይችላል፡፡ ትግራይን የተቆጣጠረው ኃይል ከፌዴራል መንግሥት ጋር መነጋገሩ የማይቀር ነው፡፡ ሆኖም ጊዜያዊ አስተዳደሩ መፍረሱን ፌዴራል መንግሥት ተቀብሎ የእነሱን ጥያቄ ያስተናግዳል ወይ የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ አቶ ጌታቸውም ሆነ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር የነበሩ ሜዳ ላይ እንዲቀሩ መንግሥት ይወስናል የሚለውም ወሳኝ ነው፡፡ ፕሪቶሪያ በአመዛኙ አበቃለት ወደ የሚያስብል ደረጃ ደርሷል፡፡ ነገር ግን ዳግም መደራደርና ማሻሻልም ይቻላል፡፡ በትግራይ ተፈጥሮ የነበረው የሰላም ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ተስፋም ቢሆን ከባድ አደጋ ተጋርጦበታል፤›› በማለትም ነው ያብራሩት፡፡

የሳልሳዊ ወያኔው አቶ ብርሃነ በበኩላቸው፣ ሕወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲመሠረት በሒደት ለራሱ በሚመች መንገድ ሊጠቀምበት አስቦ ወደ ሰላም ስምምነቱና ወደ ጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታው መግባቱን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ባሰበው መንገድ አልሄድ ሲለው ግን ቡድኑ በኃላፊነት ያሉትን አቶ ጌታቸው ረዳን በራሱ ታማኝ በሚለው ሰው ለመተካት ከባድ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሕወሓትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ግጭት መፍጠሩን ነው ያስረዱት፡፡

‹‹ሕወሓት መንግሥትና ፍፁም የበላይነት የጨበጠ ኃይል ነበር፡፡ ደም አፋሳሽ ጦርነት በትግራይ ከተካሄደ በኋላ ግን ሁሉንም አቃፊና አሳታፊ የሆነ ሥርዓት በትግራይ እንዲፈጠር ለመስማማት ተገደደ፡፡ በአዋጅ ቁጥር 359/1995 መሠረት፣ እንዲሁም በፕሪቶሪያ በተስማማውና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መመሥረቻ ደንብ መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተመሠረተ፡፡ ነገር ግን ሒደቱ አካታችና አቃፊ መንገድን የተከተለ ስላልነበር እኛ በጊዜው ተቃውሞ ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ይህም ቢሆን ሕወሓት አልተስማማውም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩን መቆጣጠር ነበር የፈለገው፡፡ በአንድ ከተማ ሁለት ከንቲባ በአንድ ዞን ሁለት አስተዳዳሪ ሲሾም ቆየ፡፡ ተቃዋሚዎች፣ ወጣቱና ምሁራን ፖለቲካው እንዲሰፋና ዴሞክራሲ እንዲበቅል ግፊት ስናድርግ ቆይተናል፡፡ ሆኖም ሕወሓት ይህ ለህልውናዬ አደገኛ ነው በማለቱ ጊዜያዊ መንግሥቱን ለማፍረስ መሥራት ጀመረ፡፡ እኛ ከኢትዮጵያ ትግራይን ለመገንጠል የምንታገል ፓርቲ ብንሆንም፣ ነገር ግን ተወደደም ተጠላም እስክንለያይ ድረስ የአገሪቱን ሕግ አክብረን መንቀሳቀስ ግዴታ ስላለብን ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባዔ አድርጉ ሲለን በሥርዓቱና በሕጉ መሠረት አድርገናል፡፡ ሕወሓት ግን ይህን አልተቀበለም ጥሶታል፡፡ ያደረገውን ጉባዔ ዳግም እንዲያደርግ ቢታዘዝም እስካሁን አላደረገም፡፡ በስተመጨረሻ ሰላማዊ ትግል እንደማያዋጣው ሲያውቅ ጦሩን ከጎኑ አሠልፎ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ አሁን የሚታየው ከቀበሌ ጀምሮ በወረዳና በከተሞች መዋቅር እያፈረሱና ቢሮዎች እየሰበሩ መንግሥትን ወደ መቆጣጠር ነው የገቡት፡፡ የሚፈልጉትን እያሰሩ፣ እየሰወሩና የሚፈልጉትን እያስፈራሩ በኃይል ሥልጣኑን ቀምተዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ሠርቷል ባንልም፣ ነገር ግን የሞተ መንግሥትም ቢሆን ሕጋዊ ሥርዓት ይሻለናል ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ አሁን ሕወሓት እየሄደበት ያለውን መንገድ እንቃወማለን፡፡ አሳፋሪ ያልተገባ ድርጊት ብቻ ሳይሆን፣ ትግራይን ዳግም ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ በአስቸኳይ ክልላዊ ብሔራዊ ጉባዔ ተጠርቶ ሁሉንም አካታች መንግሥት መመሥረት አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ጦርነቱ ከተጀመረ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ቀውስ የሚፈጠር በመሆኑ ሕወሓት ይህን ድርጊት አቁሞ ወደ ጠረጴዛ ፖለቲካ መምጣት አለበት፤›› በማለት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡    

በትግራይ በሕወሓት መከፋፈል የተፈጠረውን አደጋ ለመፍታት ፌዴራል መንግሥቱ ምን ዓይነት መንገድ ይከተላል የሚለውን በተመለከተ ኅትመት እስከገባን ድረስ የተሰጠ ማብራሪያ የለም፡፡ ጉዳዩ የፌዴራል መንግሥቱ ወደ ትግራይ የፀጥታ ኃይሉን እንዲያስገባ መነሻ የሚሆንና ከሕወሓት ጋር ጦርነት ዳግም እንዲቀሰቀስ የሚያደርግ ነው እያስባለ ነው፡፡ ነገሩ ከትግራይ ባለፈም የአማራና የአፋር ክልሎችን የሚያካልል ተጨማሪ ግጭት ያዋልዳል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ አሁን በውጭ የሚገኙትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር ሆነው የቆዩት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ እንደገመቱት ከሆነ ደግሞ፣ ሕወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ማፍረሱ የኤርትራን ሠራዊት የሚጋብዝ ጦርነት ሊያዋልድ የሚችል፣ እንዲሁም በሱዳን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር የሚጋመድ ጦርነት በኢትዮጵያ የሚፈጥር አጋጣሚ ሊሆን ይችላል በሚል እየተፈራ ነው፡፡        

ሕወሓት የአቶ ጌታቸው አስተዳደርን ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሥራቱና ፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በመጠየቁ ብሔራዊ ክህደት የፈጸመ ሲል ወንጅሎታል፡፡ ይሁን እንጂ ሕወሓት ከኤርትራ ጋር መተባበሩ ምን ዓይነት ስያሜ ሊሰጠው ይችላል ሲሉ በተቃራኒው የሚጠይቁም በርካቶች ናቸው፡፡ 

አቶ ጌታቸው በሐሙሱ መግለጫቸው ትግራይን በወቅቱ የከበበው ሁኔታ ምን ዓይነት መልክ ያለው እንደሆነ ሰፊ ማብራሪያ ሲሰጡ ውለዋል፡፡ ‹‹አንዳንዴ ትንሽ ፈሪኃ እግዚአብሔርም ያስፈልጋል፤›› ያሉት ጌታቸው፣ የፌዴራል መንግሥቱን ዝም ብሎ መውቀስና መኮነን ብቻ ሳይሆን ራሱ ሕወሓት የፈጠረውን ችግርም በሰፊው ሲዘረዝሩ ተደምጠዋል፡፡ በመግለጫቸው ካነሱት ሰፊ ሐሳብ ደግሞ የሚከተሉትን ይዘቶች እናገኛለን፡፡

‹‹መልሶ ማቋቋምና ተፈናቃይ መመለስን ያስቆምነው ራሳችን ነን ሁሉንም ጥፋት ለፌዴራል መንግሥት እየሰጠሁ መቀጠል አልችልም፡፡ አንድ የሕግ ተቀባይነት ያጣ የሕወሓት አንጃ ጉባዔ አድርጌያለሁ በሚል ስም ብቻ ደጋፊዎቼ የሚላቸውን ከፍተኛ መኮንኖችን ተጠቅሞ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው በትግራይ ችግር የፈጠረው፡፡ በሞኖፖሊ ሥልጣን ይዞ የቆየ ኃይል ነው ይህ ኃይል፡፡ ጦርነቱ እንዳይቀር አንዳች ሥራ ያልሠራ ኃይል ፕሪቶሪያ የፈጠረውን ዕድል ከመጠቀም ይልቅ፣ ትርምስና ሌላ ዙር ጦርነት መፍጠር ነው ሥራው ያደረገው፡፡ ተፈናቃይ ወደ መኖሪያው የመመለስ ችግር የእኛው የራሳችን ችግር ነው፡፡ ሠራዊቱን ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋሙ የተሰናከለውም በእኛው ችግር ነው፡፡ አሁን ያለው ጉባዔ አድርጌያለሁ የሚል ቡድን የሐሳብ ልዩነት አይቀበልም፡፡ በረሃ እያለን የተጠቀምናቸውን ቃላት ካልደገምንና ካልተሳደብን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አድረሃል የሚል ነው፡፡ በጎን ግን እኔ እሻላለሁ እያለ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን የሚለምን ኃፍረት የለሽ ቡድን ነው፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት በግልጽ የትግራይ የፀይታ ኃይል ትጥቅ ፈቶ የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንደሚሠራ ያዛል፡፡ የተስማማነው አንድ መከላከያ ሠራዊት እንደሚኖር ነው ትግራይ የተወሰነ ፀይታ ኃይል ብቻ ይኖረዋል፡፡ መልሶ ማቋቋሙ የተቋረጠውና ከ75 ሺሕ በላይ የዚህ ተጠቃሚ ለመሆን የሚጠባበቅ ታጣቂ ህልም የተጨናገፈው በእኛው ትርምስ ነው፡፡

‹‹ትግራይ ግን በአሁኑ ሰዓት በፌዴራል ሥርዓቱ የሚወከልበት ሌላ ነገር የለም ከፕሪቶሪያ ውጪ፡፡ የፖለቲካ ውይይት በአግባቡ መደረግ ነበረበት አልተደረገም፡፡ ትግራይ ከሁሉ አስቀድሞ ማረጋጋት ሲገባ መቀሌን ሳይቀር የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ነው የተሞከረው፡፡ ፕሪቶሪያ በአግባቡ ቢፈጸም እኮ ጊዜያዊ አስተዳደር ትግራይ አያስፈልጋትም፡፡ በራሳችን ጥፋት የተፈጠሩ ጥፋቶችን መጥቀስም ያስፈልጋል፡፡ የእኔ ሥራ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እየተገናኙ ፕሪቶሪያን ማስፈጸም ነው፡፡ አሁን ሦስት/አራት ሰው እኔ ጊዜያዊ አስተዳደር ልሁን የሚል አለ፡፡ እኔ ሥልጣኔን አቆዩልኝ እያልኩ አይደለም፣ ትግራይ ወደ ጦርነት እንዳይገባ ስል ነው ይህን የማደርገው፡፡ ሰላም ተፈጥሮ ተጠያቂ ላለመሆንና ሥልጣን ለመያዝ ሲሉ ወደ ጦርነት መግባት የሚመርጡ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡

‹‹ትጥቅ ማስረከብ ጀምረናል እሱን ለማስቀጠል ግን በእኛው የተፈጠሩ ችግሮች አላስቻሉም፡፡ ወደ 175 ሺሕ በሁለት ዙር ትጥቅ አስፈትቶ መልሶ ለማቋቋም ዕቅድ ብንይዝም በእኛው ችግር አልተቻለም፡፡ ፌዴራል መንግሥቱ አደናቀፈን ብዬ ግን ደብዳቤ ጽፌ አውቃለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ይህ መቆም አለበት፡፡ እኔም ሞቅ ሲለኝ ትግራይ ነፃ አገር ትሁን እላለሁ፡፡ አገር መሆን ስለተመኘህ ብቻ ግን አታደርገውም፡፡ አሁም ፓስፖርቴ የኢትዮጵያ ነው፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ በጥሞና አይቶ መሆን በሚቻልበት አግባብ ጉዳዩን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የፌዴራል ተቋማት ያልተቀበሉትን ምርጫ ካላደረኩ ማለት ግጭትን የሚጋብዝ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ትርምስ ፈጥሮ መጠቀም የሚፈልግ አካል አለ፡፡

‹‹ትግራይ ውስጥ በሚፈጠር ትርምስ ለማትረፍ ከሚፈልጉ ኃይሎች አንዱ የሻዕቢያ መንግሥት ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ደግሞ ሁሉንም አማራጭ ለሥልጣን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚጠባበቅ ኃይል አለ፡፡ ከተቻለ ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ካልሆነም የተሻለ ዋጋ ላቀረበ ተገዝቶ ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት የሚያማትር አለ፡፡ ትግራይን ከጥፋት ያተረፈ የፕሪቶሪያ ስምምነት በመፈረሙ ካኮረፈው ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ፌዴራል መንግሥትን ለመውጋት የሚፈልግ ጥቂት ኃይል አለ፡፡ ክልላችንን ለቀጣናዊ ጦርነት በየቀኑ እያጋለጠ ያለ ኃይል አለ፡፡

‹‹ፕሬዚዳንት አውርደናል አሉ አትችሉም ተባሉ፡፡ እገሌን አድርግልን አሉ አይመለከታችሁም ተባሉ፡፡ አሁን ከንቲባ በመሻርና ማኅተም በመንጠቅ ፍላጎቱን ማሳካት ነው የሚፈልገው፡፡ ፌዴራል መንግሥቱ ለምን ዝም አለ ብዙዎች ይሉኛል፡፡ እኔ በበኩሌ ይዋጣላቸው ብሎ ሊሆን ይችላል እላለሁ፡፡ ሕወሓት ልምድ ያለው ድርጅት ነው፣ እኛ ጣልቃ መግባት አንፈልግም የፌዴራል ባለሥልጣናት ይሉኛል፡፡ አሁን በተፈጠረው ቀውስ ግን ዝም ማለት አግባብ አይመስለኝም፡፡ ጦር ማዝመት ሳይሆን ከዚያ በመለስ ፌዴራል ማድረግ የሚችለው ብዙ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ትግራይ ሌላ ዙር ጦርነት የናፈቀው እያስመሰሉ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ እኛ ግን ከበቂ በላይ ሞተናል፣ ከበቂ በላይ ረግፈናል በቂ መሠረተ ልማት ወድሞብናል፡፡ ሌላ ዙር ጦርነት አንፈልግም ነው የምንለው፤›› ብለዋል፡፡

ይህን መሰል ይዘት ያለው የአቶ ጌታቸው መግለጫ በወቅቱ በትግራይ የተፈጠረውን ሁኔታ ግን በተሟላ ሁኔታ ብቻውን ይገልጸዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከአቶ ጌታቸው ወገን በተቃራኒ የቆመው የሕወሓት ኃይል ምን መሳይ አቋም በአሁኑ ወቅት እያንፀባረቀ እንደሆነ በዝርዝር መመልከት አስፈላጊ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ትግራይን የከበበውና ለቀጣናዊ ጦርነት ኢትዮጵያን ዳግም ሊዳርግ ይችላል ተብሎ እየተፈራ ያለው ሥጋት ምንጩ ምን እንደሆነ የበለጠ ለመረዳት አቶ ጌታቸውን የሚቃወመው ሕወሓት የሚያነሳቸው አጀንዳዎችን መመርመር እንደሚጠይቅ ይገመታል፡፡

ከሰሞኑ ወደ ሦስት ሰዓት የረዘመ ቃለ መጠይቅ በሆራይዘን ዩቲዩብ ላይ የሰጡት የሕወሓት ከፍተኛ አመራሯ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ)፣ ሕወሓት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ከፈጠረው ውዝግብ ጀምሮ በብዙ ጉዳዮች የሚከተላቸውን አቋሞች በሰፊው አብራርተዋል፡፡ ፈትለወርቅ በቆይታቸው የሚከተሉትን ይዘቶች በዋናነት አንስተዋል፡፡

‹‹ዛሬ ከመንግሥት ጋር ፕሪቶሪያ ብቻ ነው የሚያገናኘን፡፡ ከብልፅግና ጋር የፓርቲ ውይይት እናደርጋለን፡፡ አንዳንዴ መግለጫ መወራወርና አለመግባባት ይፈጠራል፣ እኛን እስካሁንም አያምኑንም መጠራጠር አለ፡፡ እኛ ግን ሰላም እንደምንፈልግ ነው የምናንፀባርቀው፡፡ የካቲት 3 ቀን ምርጫ ቦርድ እኛን አግጃችኋለሁ ብሎ ደብዳቤ ላከልን፡፡ ሆኖም ከዘያ ወዲህ በአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድና ሌሎች ባሉበት የፕሪቶሪያ ስምምነት ልምድ የተገመገመበት መድረክ ላይ ከብልፅግና ጎን ተቀምጠን ተነጋግረናል፡፡ በአንድ በኩል አግደናችኋል አናውቃችሁም ይሉናል፡፡ በሌላ በኩል እየጠሩ እንነጋገር አብረን እንሥራ ይባላል፡፡ ይህ ነገር ይቁም ነው የምንለው፡፡ ለ50 ዓመታት የታገለ ድርጅት አንመዘግብም በሚል ውዝግብ መፍጠር ለምን ያስፈልጋል? እኛ ለረዥም ጊዜ የኤርትራ ሠራዊት ድንበር አልፎ ትግራይ ገብቶ ጨፍጭፎናል፣ መሬታችንንም ይዞ ይገኛል ስንል ነበር፡፡ ሆኖም እነሱ ይህን ሲክዱ ነበር የቆዩት፡፡ አሁን ደግሞ ድጋሚ ተመልሰው ኤርትራ ትግራይ ገብታ ጨፍጭፋለች፣ መሬትም ይዛለች ማለት ጀምረዋል፡፡ እነሱ ሲፈልጉ ነው ወይ አንድ ነገር ትክክል የሚሆነው? ሰውስ ይታዘበናል ብለው አያስቡም ወይ?

‹‹ፕሪቶሪያ ተኩስ ማቆም ስምምነት ነበር የተፈራረምነው፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ተመልሶ ወደ ጦርነት ላለመግባት ሲባል ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ነበር የተደረገው፡፡ በዚያ ስምምነት ውስጥ ደግሞ ብዙ የማንስማማባቸው የስምምነት ነጥቦች ገብተዋል፡፡ አንዳንዶቹ የማናውቃቸውና ያልሰማናቸው ነጥቦች ነበሩ፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከያዘው ከ27 የካቢኔ አባላት 14 ሕወሓት ይሁን ተባለ፡፡ ቀሪው 13 ወንበር ደግሞ ሠራዊቱን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ሲቪክ ማኅበራት እንዲካፈሉት ተስማማን፡፡ ፕሪቶሪያ ላይ የተደራደረውም ሆነ ትልቁ ፓርቲ ሕወሓት ስለሆነ አብላጫውን ሥልጣን ይያዝ ነው የተባለው፡፡ ለሥልጣን ነው የምንታገለው፣ ሕወሓት የፖለቲካ ፓርቲ ነው እንጂ ዕድር ወይ ማኅበር አይደለም፡፡ ሥልጣን መመኘት ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት ሀጢያት አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ የሥልጣን ፍላጎት ከድርጅት ወጥቶ ግለሰባዊ ሲሆን ነው ትልቅ ችግር የሚሆነው፡፡

‹‹አንዳንዶች አካታች መንግሥት በትግራይ መመሥረት አለበት እያሉ ነገሩን ያሳስቱታል፡፡ ሆኖም ፕሪቶሪያ ላይ አካታች ይሁን ተባለ እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲመሠረት ተፈራራሚዎቹ እየተወያዩ አስተዳደሩን በስምምነት ይፈጥሩታል ነው የተባለው፡፡ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ከሕወሓት አብላጫው ወንበር የሚያዝ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ ከሠራዊቱና ከምሁራን ደግሞ ሁለት ምክትሎች ከፕሬዚዳንቱ ሥር ይኖራሉ ተብሎ ነበር በምሥረታ ጉባዔው ላይ የተስማማነው፡፡ ሕወሓት ባደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ በስድስት ተቃውሞ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ፡፡ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪነት ይህ በቂ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግሥቱ ግን አልፈልግም ቀይሩ፣ ወጣትና ምሁር ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መርጣችሁ አድርጉ ስላለ አልተስማማንም፡፡ በወቅቱ አንፈልግም ጣልቃ አትግቡብን ማለት የምንችልበት አቅም አልነበረንም፡፡ በጀት ለመፍቀድም ሆነ ለሌላ የፖለቲካ ውይይት ለመጀመር ጊዜያዊ አስተዳደር በቶሎ ይመሥረት ይባል ስለነበርና ያለንበት ሁኔታም ለመከራከር የሚያስችል ስላልነበር፣ በውስጣችን ብዙ ተሟግተን አራት ሰዎች ድጋሚ መረጥን፡፡ በስተመጨረሻ 18 ለ17 በሆነ ድምፅ ጌታቸው ረዳ ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ፡፡ ጌታቸው ረዳ የማዕከላዊ ኮሚቴ ብቻ ሳይሆን የሥራ አስፈጻሚ አባል ጭምር ስለነበር ምርጫችንን ፌዴራል አይቀበለውም የሚል ግምት ቢኖረንም ብልፅግና ግን በሙሉ ድምፅ ተቀብዬዋለሁ ነበር ያለን፡፡ አቶ ጌታቸው ፕሬዚዳንት ከሆነ በኋላ ግን ወዲያው ስህተት መፈጸም ውስጥ ገባ፡፡ ለብቻው መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ሕወሓት ለረዥም ጊዜ የገነባውን የጋራ አመራር ባህላችንን አፍርሶ በአጭር ጊዜ በደብዳቤ ብቻ በግሉ ሰዎችን ማባረርና ማስፈራራት ጀመረ፡፡ አካሄዱ እየተበላሸ ሲመጣ በመጨረሻ ግምገማ እናድርግ ተብሎ ረዥም ጊዜ የወሰደ ግምገማ ተደረገ፡፡ ሂስና ግለ ሂስ አደረግን፡፡ መስመር የሳቱ ሰዎችን ኮሚቴ ተቋቁሞ ክትትል እንዲደረግም ወሰንን፡፡ ለብልፅግና የሚሰልሉ በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃ የሚያሰራጩ ሰዎች ነበሩ የገጠሙን፡፡ ድርጅቱ ከመንገዱ እንዲወጣ የሚፈልጉ ኃይሎችን አግኝተናል፤›› ነው ያሉት፡፡

ይህን መሳይ ይዘት ያለው የሕወሓት አመራሯ የፈትለወርቅ ንግግር ደግሞ አቶ ጌታቸው ከሰሞኑ ከሰጡት መግለጫ ጋር ፍፁም የሚቃረን ሲሆን ነው የሚታየው፡፡ በዚህ ሁኔታ ፌዴራል መንግሥቱ ገብቶበትም ቢሆን የሕወሓት መከፋፈል በቀላሉ ይፈታ ይሆን ወይ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ እየተነሳበት ነው፡፡ የትግራይ ክልልን የከበበው ከሕወሓት መከፋፈል የጀመረው ፍትጊያና ሽኩቻ ተባብሶ ወደ ቀጣናዊ ጦርነት ይሸጋገራል ወይስ በቶሎ በሰላም ይረግባል የሚለው ጉዳይ አሁን የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የእንግሊዝ፣ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በኢትዮጵያ መቀመጫቸውን ያደረጉ 25 አገሮች ኤምባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ የትግራይ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ሐሙስ ዕለት ይፋ አድርገዋል። በማግሥቱ ዓርብ ደግሞ አቶ ጌታቸውና የፌደራል መንግሥቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ባሉበት ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር ውይይት ስለመደረጉ ተዘግቧል። ጌዲዮን (ዶ/ር) የሕወሓት ቡድን የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዳይተገበር እንቅፋት መሆኑን ለተለያዩ አገሮች ተወካዮችና ዲፕሎማቶች ስለመናገራቸውም ተዘግቧል። የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲተገበር ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ያግዝ ማለታቸውም ነው በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተዘገበው።

የአፍሪካ ኅብረትም በበኩሉ፣ የትግራይን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ኅብረቱ የሚመለከታቸው ሰላም ስምምነቱ ባለቤቶች በዓለም አደባባይ የፈረሙት ስምምነት እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርቧል፡፡ ኅብረቱ ንግግር እንዲደረግ እሠራለሁም ብሏል፡፡