ማኅበራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ችግር ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

የማነ ብርሃኑ

ቀን: March 16, 2025

በቅዱስ ጳውሎስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ እየተሰጠ የሚገኘው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ‹‹አለ›› ሊባል በማይቻልበትና በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም አበራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኩላሊት ሕመምና ንቅለ ተከላ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ሆኖም በቅዱስ ጳውሎስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ በመሰጠት ላይ የሚገኘው የንቅለ ተከላ ሕክምና በሚፈለገው ልክ ነው ለማለት አያስደፍርም ብለዋል፡፡

‹‹የኩላሊት ሕመምና ሕክምናውን የሚፈልገው ሰው ቁጥር ጨምሯል፡፡ ንቅለ ተከላው ግን አለ የሚባልበት ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ቆሟል ለማለትም የሚቸግር ነው፤›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከባለሙያ እጥረት፣ ከመድኃኒት አቅርቦትና ከሕክምና ግብዓት ችግሮች ጋር በተያያዘ ምክንያት አጥጋቢ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ቢንያም ገለጻ፣ በሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና መሰጠት ከጀመረ ከ2000 ዓ.ም. አንስቶ ከ170 የማይበልጡ ሕሙማን ብቻ አገልግሎቱን አግኝተዋል፡፡ ይህም ከበሽታው ስፋትና ከሕሙማኑ ቁጥር አንፃር ሲታይ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌና የኩላሊት ስፔሻሊስት ሐኪም የወንደሰን ታደሰ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ በኩላሊት ሕመም ዲያሌሲስ የሚያደርጉና ንቅለ ተከላ ያከናወኑ ሰዎች ቁጥር ከአምስት ሺሕ አይበልጥም፡፡ ይህም ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ላለው አገር እየተሰጠ የሚገኘው አገልግሎት በቂ ላለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ለኩላሊት ሕሙማን እየተሰጠ የሚገኘው የዲያሌሲስና የንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎት አነስተኛ መሆን፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅምና ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆን እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

‹‹በአንድ ወር ውስጥ በቁጥር ከሦስት የማይበልጡ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ቢደረግ ነው፡፡ ይህም አገልግሎቱ በሚፈለገው መጠን እየተሰጠ ነው ለማለት አያስችልም፤›› የሚሉት የኢትዮጵያ ኪድኒ ኬር ሥራ አስፈጻሚ እሴተ ጌታቸው (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እንደ እሴተ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና እየተሰጠ የሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ነው፡፡ ሕክምናው በአንድ ተቋም ብቻ መሰጠቱ፣ የሕክምና ባለሙያ እጥረት፣ የመድኃኒት አቅርቦትና የግብዓት ችግር ሕክምናው በተፈለገው ደረጃ ላይ እንዳይገኝ ምክንያት ሆነዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሐኪም፣ የኩላሊት ሰብ ስፔሻሊስትና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል ዳይሬክተር ፀጋዬ ብርሃኑ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና በሆስፒታሉ መስጠት ከጀመረ ከመስከረም 20009 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ለ172 ሕሙማን የተሳካ የኩላሊት የንቅለ ተከላ ሕክምና ተደርጓል፡፡

‹‹ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት የሕክምና ባለሙያ እጥረት የለበትም፣ የመድኃኒት አቅርቦትና የግብዓት ችግር አልፎ አልፎ ያጋጥማል፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ሆኖ በሁለት ሳምንት ለአንድ ወይም ሁለት የኩላሊት ሕሙማን የንቅለ ተከላ ሕክምና በመደረግ ላይ ነው በማለት ከላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት የሙያ አጋሮቻቸው የተለየ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በውጭ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ያደረጉ 572 የሚሆኑ ሕሙማን በሆስፒታሉ ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውን፣ ሕሙማኑን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ሆስፒታሉ ባለው አቅም ጥረት እያደረገ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን አሟልተው፣ የንቅለ ተከላ ሕክማና ለማድረግ የሚጠባበቁ ከ40 በላይ ሕሙማን አሉ፤›› የሚሉት ፀጋዬ (ዶ/ር)፣ ሆስፒታሉ ያለበትን የመድኃኒት አቅርቦትና የግብዓት ችግር በመቅረፍ ሕሙማኑ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በመሥራት ላይ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡