ለሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተሠሩ ሥራዎች ዙሪያ የፓናል ውይይት ተካሂዷ

ማኅበራዊ ትስስራዊ ሥራ የሚጠይቀው የሴቶች ተጠቃሚነት

ምሕረት ሞገስ

ቀን: March 16, 2025

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማጠናከር ከዓለም አቀፍ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ ሕጎች ወጥተው የተለያዩ ሥራዎች ቢሠሩም፣ አሁንም በዓለም የሴቶች ተጠቃሚነት አናሳ ነው፡፡

ትስስራዊ ሥራ የሚጠይቀው የሴቶች ተጠቃሚነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ችግሩ ደግሞ በተለይ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ባላቸው አገሮች ይበረታል፡፡ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 በየዓመቱ በታወሰ ጊዜም፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጀምሮ በየአገሩ እስካሉ የሴቶች ተቋማት በሴቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዕልባት ያገኙ ዘንድ ይነሳል፡፡

በሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችም ቀኑን ታሳቢ አድርገው መንግሥታት የሴቶችን አጠቃላይ ተጠቃሚነት ያረጋግጡ ዘንድ ይወተውታሉ፡፡ ከታች ጀምሮ በሚሠሩት ሥራ የሚያጋጥማቸውን ከትምህር፣ ከጤና፣ ከመሠረተ ልማት፣ ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ ተጠቃሚነት አንፃር ያዩዋቸው ችግሮች በፖሊሲ ተደግፈው ይፈቱ ዘንድ ፖሊሲ እንዲወጣ፣ እንዲሻሻል፣ ሕጎች እንዲሻሻሉና ተግባራዊ እንዲሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

በኢትዮጵያ ደረጃም ከችግሩ ግዙፍነት የተነሳ የሴቶች ችግርና ሰቆቃ አሁንም ያላባራ ቢሆንም፣ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያደርጉት ጥረት መሻሻሎች ታይተዋል፡፡

የዘንድሮውን ማርች 8 አስመልክቶ ስትራቴጂክ ኢንሺየቲቭ ፎር ውመን ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ (ሲሃ ኔትወርክ)፣ ሴቶችን የከበቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም፣ በዘርፉ በሚሠሩ ተቋማትና መንግሥት ትብብር ለተሠሩ ሥራዎች እውቅና ለመስጠት መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በመድረኩ በሴት ድርጅቶችና በመንግሥት ትብብር የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሠሩ ሥራዎች ዙሪያ የፓናል ውይይት ተሳታፊ የነበሩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ነጭቴ ፍላቴ እንዳሉት፣ ሴቶች ፈተናን አልፈው ስኬታማ እንዲሆኑ ሕጎች መሠረታዊ በመሆናቸው የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመቀበልና የአገር ውስጥ ሕጎችን በማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

በሴቶች ላይ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት አሁንም በርካታ ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማንኛውንም ዓይነት መድልኦ ለማስወገድ እ.ኤ.አ. በ1979 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተደረሰው ዓለም አቀፍ ስምምነትና ኢትዮጵያም ተቀብላ ያፀደቀችው በሴቶች ላይ የሚደርስ አድልኦና ማንኛውም ዓይነት በደል Convention on the Elimination all Forms of Discrimination Against Women (CEDAW) ስምምነት መቀበሏን፣ በአገር ውስጥ ያሉ ሕጎችን ማሻሻሏንና እንዲሻሻሉ እየሰራች መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተሠሩ ሥራዎች የቤተሰብ ሕጉን ማሻሻል አንዱ መሆኑን በመግለጽም፣ ከዚህ የሴቶችና የመኖሪያ ቦታን በጋራ የመምረጥ መብት፣ የጋብቻ ዕድሜን ከ15 ዓመት ወደ 18 ዓመት መሻሻልን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሌሎችም በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የተካተቱት በወንጀል ሕግ እንዲዳኙ ማድረግ ከተሠሩ ሥራዎች እንደሚጠቀሱም አክለዋል፡፡

ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጎ እንዲፀድቅ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በፓርላማ በ1987 ዓ.ም. ከነበረበት ሁለት በመቶ ወደ 41.9 በመቶ ማደጉን፣ በሕግ አውጪውና አስፈጻሚው 35 በመቶ ሴቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ነጭቴ፣ ሴቶችን በኃላፊነት ደረጃ ለማምጣትና የፖለቲካ ተሳትፎዋቸውን ለማጉላት ሲፈለግ በአብዛኛው የሚነሳው ለዚህ ደረጃ የሚሆኑ ተተኪ ሴቶች አለመኖራቸው በመሆኑ፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከ8,500 በላይ ሴቶችን ቀጣይ አመራር ለማድረግ የማብቃት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በቀዳሚነት የሚነሳው የሴቶች የመሬት ባለቤትነትና የመወሰን መብት አለመኖር ቢሆንም፣ ይህ ተሻሽሎ ሴት በጋብቻ ስትኖር አብራ እንድትወስን፣ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንዲኖራትና በዚህም 60 በመቶ ሴቶች የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘታቸው ተነስቷል፡፡

የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በብድርና ቁጠባ ተጠቃሚ መሆናቸውን፣ የሴቶች ሞት መቀነስ፣ በጤና ጣቢያ የመውለድ ሁኔታ መጨመርን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም የሰላም፣ የፀጥታ፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማት መጠናከር እንዳለባቸ፣  ለዚህ ሲባል በየተቋማቱ ሪፎርም ሲሠራ ሴቶች ያሉበት ሁኔታ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከየሎው ሙቭመንት፣ ከመራሂት፣ ከአርቲክል 35፣ ከቤዛ ፎር ኮሙዩኒቲ ቤዝድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን የተወከሉ ፓናሊስቶች በተወያዩበት መድረክ፣ እነሱን ጨምሮ በርካታ በሴት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች የሴቶችን መብት ለማስከበርና ተጠቃሚ ለማድረግ ቢሠሩም፣ መልካም የሚባሉ ሕጎች ቢኖሩም በትግበራው ላይ ማኅበረሰቡ ወደ ኋላ መቅረቱ ተነስቷል፡፡

ሴቶች ከአካላዊ እስከ በይነመረብ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፡፡ በተለይ በአገሪቱ በሚታዩ ግጭቶች ሴቶች ለከፋ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃትና ጉዳት ተጋልጠዋል፡፡ በሰላም ግንባታ በሚደረጉ ድርድሮች የበለጠ ተጠቂ ከመሆናቸውም አንፃር ተሳታፊ መሆን ቢጠበቅባቸውም፣ እድሉን አያገኙም፡፡ በሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ከታች ጀምሮ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ይቆሙ ዘንድ ቢወተውቱም፣ የተቻላቸውን ቢሠሩም ዛሬም ሴቷ ከጥቃት አላመለጠችም፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በየቦታው ተበጣጥሰው በሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ተሳስረውና ተናበው በአንድ ድምፅ መቆም አለባቸው፡፡

የመድረኩ አዘጋጅ የስትራቴጂክ ኢንሽየቲቭ ፎር ውሜን ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ (ሲሃ ኔትወርክ) የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዝምድና አበበ ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ ተባብሮና ተቀናጅቶ መሥራት በተለይ አሁን ላይ ወሳኝ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ሴቶች ይለፉሉ፣ ይሠራሉ፣ ነገር ግን ሥራቸው ቦታ አይሰጠውም፣ እንደተሠራም አይቆጠርም፣ ለሴቶች በሴቶች ድርጅቶችም ሆነ በመንግሥት የሚሠሩ ሥራዎች ቅብብሎሽ ናቸው ያሉት ዝምድና፣ ችግሮች ቢኖሩም በዚያ ችግር ውስጥ ተሆኖ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራና ለውጥ እየታየ መሆኑን፣ ነገር ግን የሚቀሩ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሴቶች አገር ግንባታ ላይ የሠሩት ሥራና አስተዋጽኦ ጎልቶ እንዳይወጣ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የሴቶችን አስተዋጽኦ የሚደብቅ ሥርዓት ስላለ ነው፡፡ ሴቶችም እንደ አንድ ተደራጅተን ይኼ ነው ችግራችን ብለን በአንድ ድምፅ አለመናገራችን ነው፡፡ የተማረች ያልተማረች፣ የከተማ፣ የገጠር፣ የአካል ጉዳት ያላትና የሌላት፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላትና የሌላት፣ የቤት ውስጥ ሠራተኛ የሆነች ሴት አለች፡፡ በዚህ ብንለያየም ፆታ አንድ ያደርገናል፡፡ በፆታ ተኮር ጥቃቶች የምናልፍባቸው ልምዶች ደግሞ አንድ ያደርጉናል፡፡ ለዚህ አንድ ድምፅና አንድ ሆነን መምጣት አለብን›› ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የዩኒቨርሲቲ ንቅናቄዎችና ሌሎችም አንደ አንድ ጥምረት ሆነው እየመጡ መሆኑ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ብዙ ጊዜ አንድ ላይ ሆኖ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ተደጋግፎና ተማምኖ የመንቀሳቀስ ችግር የሚታይ በመሆኑ ይህንን መቅረፍ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

‹‹አንድ ላይ ካልመጣንና ካልታገልን ማሸነፍ አንችልም›› ያሉት ዝምድና፣ እንደቤተሰብ ሆኖ፣ ልዩነትን አክብሮ፣ ጥቃት ሲደርስ አብሮ በመቆም የእህትማማችነትን ስሜት ማዳበር እንደሚገባም መክረዋል፡፡

እንደ ዝምድና፣ የተሠሩ ሥራዎችን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ነገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተፈጠሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየች አይደለችም፡፡ ሴቶች የሚደበቁበትና የሚሳቀቁበት ግጭት በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ይስተዋላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአውሮፓና በአሜሪካ ጭምር ጽንፍ የያዙ ንቅናቄዎች ወይም የመንግሥት መዋቅሮች እየተበራከቱ ነው፡፡ የሴቶችን መብቶች የሚቃወሙ አጃንዳዎች የያዙ የተለያዩ ፈጻሚዎች ብቅ እያሉ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ለሴቶች መብት የተሠሩ ሥራዎች ወደኋላ የሚጎተቱበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ ጦርነቶችና የሴቶችን  የመጎዳት መጠን የሚያበራክቱ ችንሮችም መጥተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የድጋፍ መቋረጥም ይካተታል፡፡

በመሆኑም እንደ ሴት መብት ተሟጋች፣ እንደ ሴት ንቅናቄና ወትዋቾች ምን መደረግ አለበት ተብሎ ያሉትን የድርጊት መርሐ ግብሮች ማየትና መገምገም፣ ለዚህ ደግሞ አንድ ላይ መምጣትና መወያየት፣ በተለይ ግጭትን በአንድ ላይ ሆኖ መቃወም፣ ለመቃወም ደግሞ የአንዷን ሴት ጥቃት የእኔም ነው ብሎ ማየት፣ ግልጽነትን ማስፈርና፣ ከመንግሥት ጋር በቅርበት መሥራትን ማዳበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አንዳቸው ሌላቸውን ደጋፊ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች መብት ላይ የመጣውን ማዕበል ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥን ለመቋቋም አብሮ መሥራት፣ ጦርነት ነገ ሳይሆን ዛሬ መቆም አለበት ማለት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡