ስፖርት የአሥራ አንድ አገሮች ሴት አምባሳደሮች የሚሳተፉበት ቅድሚያ ለሴቶች የሩጫ ውድድር  

ደረጀ ጠገናው

ቀን: March 16, 2025

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚያከናውናቸው መርሐ ግብሮች መካከል ቅድሚያ ለሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር አንደኛው ነው፡፡ ዛሬ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በሚካሄደው ውድድር የአውሮፓን ጨምሮ ከ11 አገሮች የተውጣጡ ሴት አምባሳደሮችና በተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ድርጅቶችና ኤጀንሲዎች ኃላፊነት ላይ የሚገኙ 16 ሴቶች እንደሚሳተፉበት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

እንደ መግለጫው መነሻና መድረሻውን ቦሌ አትላስ ሆቴል በሚያደርገው ከ16,000 በላይ በሚሳተፉበት የሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ታዋቂ አትሌቶች፣ በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ተምሳሌት ሴቶች ይሳተፉበታል፡፡

‹‹ሁሉም መብት ለሁሉም ሴቶች›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ውድድሩ የሴቶችን ስኬት መዘከር፣ ለሥራዎቻቸው ዕውቅና መስጠትና ሴቶች በስፖርት ጤናማ እንዲሆኑ ማትጋት ዓላማው ማድረጉ ተነግሯል፡፡

በዘንድሮው ውድድር ላይ ኤምባሲዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ድጋፍ ለማድረግ፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉበት መሆኑም ተገልጿል፡፡