March 16, 2025

ርዕሰ አንቀጽ

ከአንዱ ግጭት ወደ ሌላው የሚደረገውን ጥድፊያ በቅጡ ማስቆም ባለመቻሉ አሁንም በኢትዮጵያ ምድር አደጋ እያንዣበበ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ተገቶ የሰላም ጭላንጭል መታየት ቢጀምርም፣ አሁን በትግራይ ኃይሎች መካከል በተነሳ እሰጥ አገባ ምክንያት ወደ ደም መፋሰስ የሚያስገባ እንቅስቃሴ እየተስተዋለ  ነው፡፡ በሕወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው ክፍፍል ሳቢያ ለወራት በቃላት ጦርነት ውስጥ የከረመው የትግራይ ክልል፣ አሁን ደግሞ ወደ ለየለት ትርምስ ውስጥ የሚያስገባው አደገኛ ክስተት እየተፈጠረ ነው፡፡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ጣልቃ መግባትና ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ከበቂ በላይ ምክንያት እንዳለው፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት የተሳተፉት የፌዴራል መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በክልሉ ያለው ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱንና የስምምነቱ መፍረስ የሚያስከትለውን አደጋ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው ማሳሰባቸው የችግሩን ክብደት ያሳያል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ተገቶ፣ ለዘለቄታዊ ሰላም ጥርጊያውን የሚያመቻቹ ሥራዎች በወጉ ሳይከናወኑ በትግራይ ክልል ከፍተኛ አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ ችግሮች በስፋት እየታዩ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በሕወሓት ጉባዔ ማድረግና አለማድረግ የተነሳው ውዝግብ ከድርጅቱ ውስጣዊ ችግርነት አልፎ፣ በወታደራዊ አዛዦች ላይ የዕገዳ ውሳኔ ሲተላለፍ ብዙዎችን ሥጋት ውስጥ ከቶ ነበር፡፡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተኩስ የታጀቡ የአስተዳደር መዋቅሮችን መቆጣጠር መጀመርም ሥጋቱን አባብሷል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት እንዳሉት የፕሪቶሪያ ስምምነት እየፈረሰ ክልሉ የማይወጣው ችግር ውስጥ እየገባ ይመስላል፡፡  የተለመደው የሴራ ፖለቲካ እየቀደመ ለንግግርና ለድርድር ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ፣ ጉልበት መፈታተሽ ውስጥ እየተገባ የሕዝብ መከራና ሥቃይ ተባብሶ እንደሚቀጥል አያጠራጥርም፡፡ አሁን እየታየ ያለውም በሥጋት የተወጠረ አየር የሚያመለክተው የፖለቲከኞቹ አለመግባባት ወደ ፀጥታ ኃይሉ ሊያመራ እንደሚችል ነው፡፡

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደሩን በሚመሩትና በተቃራኒ በቆሙት ኃይሎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በብዙዎች ዘንድ ከሥልጣን ጋር በተያያዘ እንደሆነ መላምት ቢያሳድርም፣ ከበስተጀርባው የውጭ ኃይሎች እንዳሉበት ሲጠረጠር ደግሞ ያስደነግጣል፡፡ በክልሉ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር አጋጥሟል መባሉ ምን እየተካሄደ ነው ያሰኛል፡፡ ፖለቲከኞቹ በውጭ ኃይሎች ግፊትና ድጋፍ በፕሪቶሪያ ስምምነት አውዳሚው ጦርነት መቆሙ፣ መከራና ሥቃይ ውስጥ ለነበረው ሕዝብ ዕፎይታ መፍጠሩ የተሰማቸው አይመስሉም፡፡ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት በቅደም ተከተልና በስክነት አስፈላጊዎቹ ተግባራት እንዲከናወኑ በማድረግ ያጠላውን ሥጋት መግፈፍ ሲገባቸው፣ ለንፁኃን ዕልቂትና ለንብረት ውድመት የሚዳርገው ጦርነት እንደገና እንዲቀሰቀስ ምቹ መደላድል ሲፈጥሩ እንደማየት የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡ በንግግርና በድርድር ሊፈታ የሚችል አለመግባባትን በማጦዝ ወደ ጦርነት ነጋሪት ጉሰማ መግባት ሊያበቃ የግድ ይላል፡፡

እንደሚታወቀው ቀደም ሲል በጦርነቱ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች አልቀዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለረሃብና ለመፈናቀል ተዳርገዋል፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፣ የተደፈሩና ለከፍተኛ ሥነ ልቦና ጉዳት የተዳረጉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ አሁንም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆነው የዕርዳታ ያለህ የሚሉ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ቋፍ ውስጥ እየገቡ ነው በሚባልበት በዚህ ጊዜ የትግራይ ሕዝብ ከደረሰበት መከራና ሥቃይ ሳያገግም ተመልሶ ሌላ ዙር ጦርነት ሲያንዣብበት፣ በግራም ሆነ በቀኝ የተሠለፉት የፖለቲካ ተዋንያንም ሆኑ ሌሎች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ ነገር ግን በሕዝብ ስም የሚነገድበት የፖለቲካ ቁማር መቆም አለበት፡፡ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ሰላምና ዕፎይታ ለሚያስፈልገው ሕዝብ የቦምብና የጥይት እሩምታ ለመደገስ መቅበዝበዝ መዘዙ የከፋ እንደሆነ ይታወቅ፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያሉ ጦርነቶች ቆመው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የሚረዱ ተግባራት ላይ እንዲተኮር፣ በትግራይ ክልል በፕሪቶሪያ ስምምነት የተገታው ጦርነት እንደ ምሳሌ ሆኖ እንዲያገለግል፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ግድያዎችና ዕገታዎችን ጨምሮ ነውረኛ ድርጊቶች በፍጥነት መላ እንዲበጅላቸው ርብርብ መደረግ ሲኖርበት ለሌላ ዙር ፍጅት ዝግጅት ማድረግ ጤነኝነት አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የግጭት መናኸሪያ ከሆኑ አካባቢዎች በተጨማሪ በመላ አገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰላም ናፍቋቸዋል፡፡ በሰላም ዕጦት ምክንያት ከሚደርሱ ዕልቂቶችና ውድመቶች በተጨማሪ፣ በኑሮ ውድነት ሳቢያ የሚሊዮኖች ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላ ዙር ጦርነት ለማካሄድ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አቅም የላትም፡፡ እንኳንስ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ያሉ ዜጎች፣ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው ሥፍራዎች የሚኖሩ ጭምር የኑሮ ውድነቱን መቌቌም ተስኗቸዋል፡፡

ኢትዮጵያን እያደር ከድጡ ወደ ማጡ የሚገፏት አደገኛ ድርጊቶች ሲበራከቱ ሊከተል የሚችለው መዘዝ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በቅርብ ርቀት ላይ ያሉ አገሮች ማለትም ሱዳን፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያና ሌሎችም በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ ሥርዓተ አልበኝነቶች ነው የማይወጡት ቀውስ ውስጥ የገቡት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩነቶችን በሥርዓት ፈር አስይዞ ለንግግርና ለድርድር ዓውድ መፍጠር አቅቶ በየቦታው ውጊያ፣ ዕልቂት፣ ውድመት፣ ማፈናቀል፣ ዘረፋ፣ ዕገታና የጭካኔ ግድያ ተበራክተዋል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ በመውጣት ሁሉን አቀፍ ንግግርና ድርድር ለማድረግ የሚያግዙ መድረኮች ማመቻቸት ይገባል፡፡ አሁን በተያዘው ሁኔታ የሚቀጠል ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ለአካባቢው ጭምር እጅግ አደገኛ ጥፋት የሚያስከትል ጦርነት ውስጥ እንደምትገባ አለመገንዘብ ውጤቱ ከባድ ኪሳራ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ጦርነት የሚወስዱ መንገዶች በፍጥነት ይዘጋጉ!