
ተሟገት ኑሮና ብልኃቱ አልሳካ ያለው የጉርስና የመጠለያ ነገር
ቀን: March 16, 2025
በገነት ዓለሙ
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት የጠያቂ መብዛትንና የሸቀጥ ማነስን አድምጦ ዋጋ ለመተኮስ የሚፈጥን፣ ለአቅርቦት መብዛትና ለፍላጎት መቀነስ ግን ጆሮ የሌለው፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መውደቅ እንኳ ከቅጠላ ሊገታው ያልቻለ ዓይን አውጣ ነው፡፡ የዋጋ አቀጣጠሉ ደግሞ ያው በደርግ ዘመን እንደለመደው ባለሁለት አቅጣጫ ነው፡፡ መሸጫ ተመን ከፍ በማድረግና የሚሸጠውን ነገር መጠን/ሚዛን፣ ጥራት ወይም ውፍረት በመቀነስ፡፡
ከሚገዙ/ከሚሸጡ ነገሮች የብዙዎች ጭንቅ የሆኑት የመሠረታዊ ፍላጎት አቅርቦቶች ናቸው፡፡ ከመሠረታዊ ፍላጎት ውስጥ ልብስ አሮጌ በማሳደስም ሆነ በመግዛት የሚሸፈን ‹‹ትርፍ ነገር›› ሆኗል፡፡ የልጅ ትምህርት ቤትም ጊዜ ይሰጣል፡፡ ዕድሜ ሲደርስ እንደምንም አንድ የደንብ ልብስ ገዝቶ መንግሥት ትምህርት ቤት መስደድ ነው፡፡ ሕክምናም ከአገረ ሰብ መድኃኒት፣ ከጠበልና ከመሳሰለው ካለፈ ያው ጤና ጣቢያ እንዳደረገ ይኮናል፡፡ ሞት አንደኛውን ከመጣም ግልግል ነው፡፡
እነ ስልክና ኢንተርኔት አየር የመተንፈስ ያህል የመሠረታዊ ኑሮ አካል ሆነዋል፡፡ ባደጉት አገሮች መኪናም የመሠረታዊ ፍላጎት አካል ተደርጓል የሚል ወሬ ‹‹የሰካራሞች›› ወሬ ነው፡፡ ለእኛ መሠረታዊ የሆኑት ጉርስና መጠለያ ናቸው፡፡ ጉርስ ሲባልም የእነ ለስላሳ ወይም የእነ ቢራና ወይን ውኃ መሆንን፣ የእነ ፍራፍሬን ደህና ከብልሹ መሆንን፣ የሥጋን ደህና ከሞራና ከአጥንት ጋር መሆንን አይጨምርም፡፡ እነዚህ ‹‹ቅንጦቶች›› ናቸው፡፡ የብዙኃኑ ጉርስ ጉዳይ ሆድን የሚያታልል ነገር ማሟላት ነው፡፡ መጠለያም ሲባል መኝታ ቤት ምንትስ ያለበት መኖሪያ ሳይሆን የትም ይዋል፣ አንገት ማስገቢያ ማግኘት ሆኗል፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ የሚለፋው እነዚህን ለማቃናት ነው፡፡
ተለፍቶስ መቼ በዋዛ የሚሟሉ ሆነው! ከገቢ የሚፈጥነው ዋጋቸው በየት አስችሎ!! በፈረንጆቹ አገር የኢኮኖሚ ቀውስ እስካልረበሸ ድረስ፣ የጡረታ መውጫችን ጊዜ ይነስልን ሠልፍ የሚወጣበት ጥያቄ ነው፡፡ እኛ አገር ትግሉ ጡረታ ላለመውጣት፣ ያውም ገና ሥራ ሲጀመር ዕድሜ ከመቀነስ አንስቶ፡፡ ያን ያህል ሙጭጭ የተባለለት ደመወዝ ከቀለብ አልፎ ለእርጅና ዘመን የሚሆን ጥሪት ሊተርፈው ይቅርና ቀለብ በአግባቡ ለመሸፈንም የማያስችል ነው፡፡ በሺሕ ብሮች ደመወዝ ቀለብ መሸፈን ብሎ ነገር አስቂኝ ሆኗል፡፡ የዛሬን ኑሮ ‹‹ግማሽ ረሃብ›› እንኳ የሚመጥነው ቃል መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ የጡረታ ዋስትና ነገርማ አይነሳ፡፡ ድሮም አልነበረም፣ አሁንም የለም፡፡ ያለው ‹‹አበል›› ነው፡፡ የዱሮው አበል በአሥራ ምናምን ብርም ቤተሰብ ያስተዳድር ነበር፡፡ ዛሬ ሺሕ ብሮች እንኳ ቤት ሳይደርሱ ገና መንገዳገድ ጀምረዋል፡፡ የጡረታ ሐሳብ ዛሬ በልጅና በቤተ ዘመድ ላይ አይጣል ነገር፣ የዞረበት ዘበናይነትና ጨካኙ ኑሮ የትስስብ ገመዶቻችንን እየበጣጠሳቸው ነው፡፡
ከዘመድና ከመንግሥት በላይ፣ ዛሬ ባለ ትንሽ ግቢ የመኖሪያ ቤት ቅርስ ያለው የፀደቀ ነው፡፡ በከተማ ውስጥ የቤት ባለቤት መሆን ማለት የመተዳደሪያ ዋስትና ማግኘት ማለት ሆኗል፡፡ ያችን እየሸነሸነ፣ እያውተፈተፈም በኪራይዋ ኑሮን ማሸነፍ ይቻል ነበር፡፡ አሁን ግን እሱም በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ተረት እየሆነ ነው፡፡ ቤት የለሽ ከተሜ ግን ከጡረታ በፊትም ሆነ በኋላ ለጉርስ ያለበት ትግል አይጣል ነው፡፡ ከአንድ የበለጠ ሥራ መሥራት ወይም የቤተሰብ አባላትን ባተሌነት ማበራከት ግድ ይለዋል፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ ሲታገሉ ደግሞ የቀዳዳዎቹ መጥበብ ሳያንስ የመሰናክሎቹ አስቸጋሪነት፡፡ በፊት በአዲስ አበባ መንገዶች ዳር ወጥቶ ትንሽ ነገር ለመሥራት የእግረኛ መንገዶች ጥበትና የአካባቢ የደኅንነት ሥጋት ምቀኛ እየሆነ መባረር ነበር፡፡ አሁን ግን የመንገድ ዳር ሥራ አይሞከርም፡፡ እንደምንም እየተሠራ የኑሮን ዕዳ መወጣት ቢቻል እንኳ የከተማ አፍርሶ ግንባታ የሚፈጥረው መናጋት ሌላ ራስ ምታት ነው፡፡
ከሥራም ሥራ ግን አለ፡፡ የቆሎ ተማሪን የመደጎሚያና ሥለት የማድረሻ መንገድ ከመሆን ዝቅ ቢል፣ ሰርቆ ከመብላት የሚመረጥ የዕጦት መወጫ የነበረው የቀድሞው ልመና፣ የቆመበት የሃይማኖተኛነትና የጨዋነት ማማ በደርግ ጊዜ ከተደረመሰና መስረቅን የብልህና የአዋቂ ሥራ ያደረገ (ልጄን ፊናንስነት ወይ ዕርዳታ ማስተባበሪያ አስቀጥርልኝ ብሎ ለፈጣሪ እስከመሳል ያበቃ) ዘመን ከመጣ ጀምሮ፣ ስርቆት በየትኛውም እርከን የሚካሄድ አንድ ሁነኛ የኑሮ ማሸነፊያ ዘዴ መሆኑ እንደቀጠለ ነው፡፡ ልመናም ለገጠሬም ሆነ ለከተሜ ቋሚና የትርፍ ጊዜ የገቢ ማግኛ አማራጭ ሆኖ ማገልገል ከያዘ ውሎ አድሯል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ዘንድ የዘለቀው በወሲብ ንግድ መጊያጌጥም መጊያጊያጥም፣ ዕጦትን የመወጣት ትግሉ ምን ያህል እንደከፋ የሚያሳይ ነው፡፡
የሚኮነውንም የማይኮነውንም እየተኮነ ከተገኘ ገቢ ውስጥ ይበልጡን ነጣቂ ሆኖ የሚያስቸግረው የቤት ኪራይ ወጪ ነው፡፡ ንጥቂያውን ለመቀነስ በትልልቅ ከተሞች አንድ ቤት ለብዙ ተከፋፍሎ፣ አንድ ክፍል ለሁለትና ከዚያ በላይ ደባል ሆኖ መያዝ፣ ከብሎኬት ቤት ወደ ጭቃ ቤት፣ ያም ሲያቅት ወደ ልሙጥ ቆርቆሮ ቤት መውረድ ሁሉ የወፍራም ኪራይ ሸክምን የማቅለል መላዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን አልተቻሉም፡፡ ለዚህ ዓይነቱም ኑሮ የአከራይ ክልከላ ሌላ ፈተና ነው (እጅግ በባሰበት ድህነት ውስጥ፣ በደርግ እስር ቤቶች የታየው ዓይነት የፈረቃና የ‹‹ስክ›› መኝታ ዘዴ ተግባራዊ የሚደረግበት የሌሊት አስተዳደር በአዲስ አበባ ውስጥ ሳይኖር አይቀርም)፡፡
በልቶ የማደሩ ብልኃት ምኑን ከምኑ አድርጌ ላስፈጨው/ላበራክተው የሚል ራሱን የቻለ አበሳ ሆኖ ሳለ፣ የመብራትና የውኃ መቋረጥ የተገኘችውን አዘምማዶ ለመብላት እንኳ እየከለከለና ተሯሩጦ ሥራ የመሥሪያ ጊዜን እየተሻማ ቆሽት ያሳርራል፡፡ መብራቱ እንደ ቀድሞው በፈረቃ ሆኖ እንደ አመሉ እንዳይያዝ ዝብርቅርቅ ነው፡፡ ተዘባርቆም በቀን አንዴ (በአዲስ አበባ ልምድ) ሳይጠፋ አይውል፡፡ የንፋስና የዝናብ ሰበብ ከተገኘ ወዲያው እልም፡፡ የተጀመረና በኤሌክትሪክ የሚካሄድ የመተዳደሪያ ሥራ በተዘዋዋሪ የጉርስ ማግኛ ምንጭ መታጓጎል፡፡ በወር ውስጥ አከታትሎ ወይ አዘባርቆ በጨለማ ቢያንስ ሦስት አራት ቀን ማሳደርም የማይቀር ነው፡፡ ውኃው በፊናው እንኳን በተራ ቀን በበዓል ቀን እንኳ ለመቋረጥ የማያፍር ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ታዲያ ሥርዓቱ ‹‹የሚቆረቆርላት›› የሴት ልጅ አበሳ! አብሲት የገባበት ሊጥ ይዞ መብራት ወዳልጠፋበት ዘመድና ወዳጅ መብረሩ! ያ ካልተሳካለት ሊጋገር የተዘጋጀን ወይም ተጀምሮ የነበረ ሊጥን እንዳይኮመጥጥ አጎባግቦ፣ ሌላ ዓይነት የሆድ መሙያ ዘዴ ፍለጋ ውስጥ መግባቱ! መብራት ጠፍቶ ባደረበት አካባቢ የግዥ ዳቦ ለማግኘት ስደቱ! መብራት ያለው ወፍጮ ቤት ፍለጋው! ውኃ ሲጠፋ ባለ 20/25 ሊትር ጄሪካን ይዞ ውኃ ፍለጋ መንጦልጦሉ! ቢገኝ እንደ ዱሮ በተሸካሚ ላስመጣ አይባል ዋጋው ውድ! ራስ አዘሎና አንጠልጥሎ ወገብ መቁረጥ ግድ፡፡ አዲስ አበባን በሚያህል ከተማ የውኃ ችግር ‹‹ተቀረፈ›› ከተባለም በኋላ አሁንም እንዳለ አለ፡፡ ሲገኝም ከመንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ ይሁን ከውኃ ሕክምናው ክትትል ማነስ፣ ሌሊትና ማለዳ ላይ ድፍርስ ሆኖ እያረፈደ ሲሄድ ‹‹የሚጠራ›› ውኃም ያጋጥማል፡፡ ካላፈላሁ አላምንም ብሎ ለመጠንቀቅ ሲሞከር የኑሮ ጣጣ ፈንጣጣው ጥንቃቄውን ቅንጦት አድርጎ ያስጥላል፡፡
ታች ያለው ሰው ምኑን ከምኑ አድርጎ እየበላ ቆሞ እንደሚሄድ መገመት እንደ እንቆቅልሽ ከብዷል፡፡ የመንግሥት የቁጥር ስታትስቲክስ ድህነት መረጋጋቱን ይናገራል፡፡ የአዲስ አበባ ሕይወታዊ ስታትስቲክስ ደግሞ ሌላ ያወራል፡፡ ድሮ የደሃ የምግብ ባህል ውስጥ የነበረው ነጭ ሽንኩርት አድራሻውን ቀይሯል፡፡ ክረምት ሲመጣ የአዲስ አበባን መንገዶች ያቆሽሽ የነበረው የበቆሎ እሸት ዛሬ የትና የት የቀነሰው ሰው ንቆት ሳይሆን በቆሎ ሰው ንቆ ነው፡፡ የቆሎና የንፍሮ አጠፋፍም እንደዚያው ነው፡፡ ዱሮ ለልጆች አንዳንድ ዳቦ በ10/20 ሳንቲም የሚገዛበት ዘመን አልፎ ያንኑ ዳቦ በአሥር ብር ገዝቶ ለቁርስ ማካፈል ከተቻለ ተመስገን ነው፡፡ አዋቂ ራሱ አንድ ዳቦ ለምሳ በልቶ በዚያ ላይ ሁለት ብርጭቆ ውኃ በመጠጣት የሚጠግብበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ በደርግ ጊዜ ለእኔ ብጤ ወይ ለውሻ ምግብ ኮንትራት ይሰጥ የነበር የሆቴል ምግብ ትራፊ ዛሬ የአከፋፋይና የቸርቻሪ ሥራ ክፍፍል ወጥቶለት በተለያየ መጠን ለሰው የሚሸጥ ሆኗል፡፡ ይህ ጉድ ያኔ ደርግ በታላቁ ቤተ መንግሥት እስር ቤት ውስጥ የቅልብ ጠባቂ ጦር ትራፊ ለፖለቲካ እስረኞች ያበላበት ግፍ ላይ መሳለቅ የማያስችል እውነታ ነው፡፡
የአገር ውስጥ ምርት የገበያ ትስስር ተሞክሮለት ገበያው ማንሳት ሲያቅተው ልማቱ እንዳይከስር ሲባል የውጭ ገበያ እስከማፈላለግ ድረስ ይኬዳል፡፡ የውስጥ ገበያው ለምን ማንሳት እንዳቃተው ምክንያቱን ፈልጎ ለመፍታት ሲሞክር ግን አይታይም፡፡ ወደ ፍራፍሬ መሸጫ መደብሮች ቢኬድ ገዥ አጥቶ እንደተሰቀለና እንደተደቀነ የሚበላሽ ፍራፍሬ ብዙ ነው፡፡ ወደ ጉልቶች ቢኬድ እግሩ ውኃ ውስጥ ተዘፍዝፎ እያደረ፣ ቀንም ውኃ እየተርከፈከፈበት ተሸጦ አላልቅ እያለ ለቆሼ ገንዳ የሚዳረግ ቆስጣና ጎመን ቀላል አይደለም፡፡ እየጠወለገ የሚጣል ድንች፣ ቃሪያና ሎሚ እንደዚያው ትንሽ አይደለም፡፡ ችግር የሆነው ምርቱ ከሕዝቡ ፍላጎት (አምሮት) በላይ ተትረፍርፎ ነው ወይስ የመሸጫ ዋጋው ንረት የጥያቆቱን (ለመግዛት የሚችለውን ፈላጊ) ቁጥር አውርዶት? ይህ ታች ወለል ላይ የሚታይ እውነታ በጊዜ መፍትሔ ካልተፈለገለት ነገ በመግዛት አቅም ማነስ ምክንያት ገበያ ውስጥ የሚፈጠረውን ቀውስ ይጠቁማል፡፡ ያ ቀውስ ደግሞ አንሺ ላጣ ምርት የውጭ ገበያ በመፈለግ ብቻ የሚፈታ አይሆንም፡፡ ገዝቶ ለመኖር አቅም የማጣት ምሬት ብሎ ብሎ የሚፈጥረው ቁጣ በቀላሉ የሚመለስ አይሆንም፡፡
የቤት ኪራይ ዋጋ አዲስ አበባ ውስጥ ለአንድ ደህና ክፍል እጅግ በትንሹ ከአሥር ሺሕ ብር አያንስም፡፡ እሳት የተባለ ኮንዲሚኒየም ስቱዲዮ በአሥራ አምስት ሺሕ ብር ድረስም ይከራያል፡፡ ወዶም ሆነ ተገዶ ቅናሽ ፍለጋ ሰው ወደ ከተማ ጠርዝ እየዘመተ ነው፡፡ ይህም ያቃተው ካገባ በኋላ እንደገና ወደ ወላጆቹ እየተመለሰ ለኪራይ ያሏትን ቤት መሻማት ይዟል፡፡ በዚህ ላይ ከዚህ ሁሉ ስቃይ ይገላግላል የተባለለት የጋራ ቤት ግንባታ ጉዳይ ሕልም ሆኖ የብዙዎችን ተስፋ ንዷል፡፡ በአንድ ወቅት ፕሮጀክቱ ራሱ የአመለካከትና የትልም ችግር እንዳለበት ሥራው የሚመለከታቸው የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰዎች መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ የሕዝብ መሬት እንደ መንግሥት የግል ንብረት ከመቆጠሩ የተነሳ መንግሥት በነፃ መሬት መስጠቱ እንደ ትልቅ ድጎማ (ውለታ) ሲነገርም ተሰምቷል፡፡ መንግሥት ምድር ላይ ያለውን ትፍግፍግ በተለያየ የቤት ደረጃ ልዘርዝረው የሚል ንድፍ እንደሌለው የሚያጋልጥ ነው፡፡
ሌላው በተስፋፋ ትምህርት የታጀበ የሥራ አጥነት ችግር አለና እንደ ቀድሞው ልጄ ተምሮ ከችግር ያወጣኛል ብሎ ተስፋ ማድረግ የለም፡፡ ዛሬ ተምሮ መመረቅና ሥራ ማግኘት በጣም የተለያዩ ነገሮች ሆነዋል፡፡ በየዓመቱ በከፍተኛና በመለስተኛ ሙያ የሚመረቀውን ወጣት የሚያነሳ የሥራ ፈጠራና የሥራ መስፋፋት የሚፈለገውን ያህል አለመኖር፣ የመንግሥትንም የሥራ ተስፋ ሆኖ የመዝለቅና ወጣቱን ከተቃውሞ የማራቅ ብልጠት አደጋ ውስጥ የከተተ ነው፡፡ በግልና በቡድን ሥራ ፈጥሮ እንጀራ ማግኘት የግድ ከተማሩት ሙያ ጋር አልገጥም ሲል የብስጭት ምንጭ ይሆናል፡፡ ብድር አግኝቶ በሆነ የሥራ መስክ ሠርቶ የመኖር ዕድልም ቢሆን መነሻ ገንዘብንና አሳማኝ የሥራ ዕቅድ ማቅረብን ይጠይቃል፡፡ መነሻ ገንዘብ በማስገኘት በኩል መድኅን ናቸው የሚባሉ ሥራዎች ሁሉን ምሩቅ ሥራ አጥ የሚማርኩ አይሆኑም፡፡ በዚያ ላይ ከተለያየ አቅጣጫ የመጣ ሥራ አጥ ሁሉ የሚገባበት እንደመሆኑ ሁሉንም አይሸፍንም፡፡ በሥራ ገንዘብ ቋጥሮ ወደ ሥራ ፈጣሪነት መሸጋገር ብልህነትን፣ ልባምነትንና ወኔን የሚፈትን ነውና ፈተናውን ማለፍ የሚያቅተው ይኖራል፡፡ በየዓመቱ የሚፈጠረውን ሥራ አጥ በተወሰነ ዘርፍ ውስጥ የማስተናገድ መርሐ ግብር ነባሮቹን ቦታ ማስለቀቅ ይጠይቃል፡፡ ቦታ ማስለቀቁ ቢሳካ እንኳ ሥራው ሄዶ ሄዶ ቅልብጭ ይላልና አዛላቂ ማስተናገጃ አይሆንም፡፡ ልማቱ በየዘርፉ ብዙ ዓይነት የሥራ ቀዳዳዎች ትርጉም ባለው ደረጃ ካልፈጠረ በቀር፣ የሚጠራቀመው የወጣት ሥራ አጥነት ከእነመዘዙ እጅግ አስፈሪ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ሥራ አጥነትና መሠረታዊ ፍላጎት ያረረበት የኑሮ ክብደት አንድ ላይ የሚያፈነዱት ድንገተኛ ቁጣ የማሰላሰያ ጊዜ አይኖረውም፡፡
መሠረታዊ ፍላጎት ስሙ እንደሚገልጸው ታገሱን የማይባልበት ነው፡፡ የዛሬዎቹ ገዥዎች ሕዝብ ማቆሚያ ካጣው አበሳው ይልቅ ዘላቂ ልማትን አብልጦ ታግሶናል እያሉ ራሳቸውን ከሚያታልሉ፣ የገዥነት መንግሥታዊ ቆይታ በሕዝብ መዳፍ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት ነበርን ብለው ቢያስቡ ለሁሉም ይበጃል፡፡ ‹‹ሁለተኛ ዲግሪ ያለው አስጠኚ›› የሚል ማስታወቂያ በየሠፈሩ ከሚለጥፈው ወጣት ምሩቅ እስከ ታች ከልታማው ድረስ ያለ ሥራ አጥነትን የሚሰለቅጥ የሥራ መስፋፋትን በማምጣት አጠቃላይ መፍትሔ ውስጥ፣ አንደኛ የውኃና የመብራት መቋረጥ የሚፈጥረውን አብግንነት ትርጉም ባለው ደረጃ በቶሎ ማቅለል፡፡ ሁለተኛ የቤትና የምግብ ውድነትን ለሚያረግቡ ጊዜያዊና ሽግግራዊ መላዎች እንክባከቤ ማድረግ፡፡ ለምሳሌ፣
- የመሬት ፍትሐዊ አጠቃቀም ለእያንዳንዱ ቤት ፈላጊ ቤት የመሥሪያ ቦታ ግድ ማደል ወይም የጋራ ቤት ባለቤት ማድረግ አይደለም፡፡ ይኼኛው መብት በመግዛት አቅም የሚጨበጥ እንደመሆኑ የመጠለያ መብት ዋና ማሟያ መንገድ ኪራይ ቤት ነውና ከአብዛኛው አቅም ጋር የተግባባ የቤት ኪራይ ዕድል እንዲፈጠር ማድረግ ግዴታ ነው፡፡ በገንዘብ አቅም ልክ የሚከራዩት ቤት ማጣት ሊያስጠይቅ የሚገባ የመብት መጓደል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ፖሊሲንና አሠራርን ማተካከል፣ አንድ ክፍልም ለመሥራት ከፈቃድም አልፎ ፕላን አሠሩ የሚባለውን ግን በጉቦ የሚነደለውን ደንብ አቃንቶ፣ ሲሆን በፍጥነትና በቀላል ዋጋ የሚሠራ የቤት ቴክኖሎጂ አዘጋጅቶ ባለግቢዎች የኪራይ ቤቶች እንዲሠሩ ማበረታታት፡፡ ከዚሁ ጋር ከተወሰነ ተመን በታች የሆኑ የኪራይ ዋጋዎችን ከግብር ነፃ ማድረግ፡፡
- ሕዝብ ከሚበረክቱባቸው አደባባዮች፣ ከመጓጓዣ መናኸሪያዎች፣ ከጉልቶችና ከሌሎች ኢመደበኛ ንግዶች ጋር ተጎዳኝተው የሚመጡ ቀላል የምግብ (የሳምቡሳ፣ የአምባሻ፣ የእርጥብ፣ ወዘተ) ንግዶች ንፅህናና ጤናማነታቸው ባልተጓደለበት ሁኔታ ሳይሳቀቁ ግን በተጠያቂነት አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታና የሥራ ቦታ ማመቻቸት፡፡
- በአዲስ አበባ ልምድ ላይ እንወሰንና እንደ ዘመኑ ኑሮ ሰዎች ባነሰ ዋጋ ምሳና ራት የሚያገኙባቸው ሥፍራዎች ነበሩ፡፡ መርካቶ አካባቢ፣ አራት ኪሎ፣ ወዘተ፡፡ ዛሬም ባለው የኑሮ ውድነት ደረጃ የፆም በየዓይነቱ በ100 እና በ150 ብር የሚሸጡ ባለአንድና ባለሁለት አነስተኛ ክፍል ምግብ ቤቶች ቁጥራቸው ቢቀንስም መኖራቸው አልቀረም፡፡ እንዲህ ያሉትን ውለታ የመሥራት ያህል የሚፈይዱ ምግብ ቤቶችን ጤናማነትን ከማስተማመን በስተቀር፣ ይህንን ደረጃ አላሟላችሁም ወይም ቦታው ለልማት ይፈለጋል ከሚል ጉንተላና ማስፈራሪያ መጠበቅና ከግብር ጋር የተያያዘ ማበረታቻ መስጠት፡፡
- ዳቦን በተመለከተ ብዙ ፈላጊ ያለው ትንንሹ ዳቦ ነው፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባ እንደሚታየው የዚህ ዓይነቱን ዳቦ እንደ ተፈላጊነቱ በማብዛት ፈንታ በቀን ሁለት ጊዜ ጨርሶ ከዚያ በኋላ ያለውን ጊዜ ሰሊጥ ብጤና ቄንጣ ቄንጥ ያለውን ዳቦ ወፈር ባለ ዋጋ ማጣሪያ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በተለይ ከመጓጓዣ ችግር ጋር ታግሎ ከሥራ የሚመለስ ሠራተኛ የሚወድቀው የዚህ ዓይነት ገፈፋ ላይ ነው፡፡ ወቀሳ ሲበዛባቸው ቢበዛ የሚያደርጉት ለውጥ የትንንሽ ዳቦ መገኛውን ሰዓት ከቀን ላይ ቀንሰው ወደ ሥራ መውጫ ጊዜ ማስጠጋት ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱን የተዛባ አነጋገድና የዳቦን ጥራትም ሆነ ሚዛን በየጉራንጉር ሁሉ እየገቡ መቆጣጠርና ማቃናት ባይቻልም፣ በቅርንጫፎች አማካይነት ሰፊ አቅርቦት ሊፈጥሩ የሚችሉ ጥቂት ትልልቅ ተዋንያን እንዲደራጁ በማድረግ እነሱን መቆጣጠር፡፡ የእነሱ ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ አቅርቦት ትንንሾቹን እንዲገራ አድርጎ ማቻቻል አንድ መፍትሔ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ተከፍተው እየተዘጉ ያሉ ትልልቅ ዳቦ ቤቶች ጉዳይ ቢታሰብበት ይሻላል፡፡ ዳቦ ሲጠፋ የሚከተለው ጥሩ ነገር አይደለምና፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡