
16 መጋቢት 2025, 07:30 EAT
ሁሉ መልካም ነው ብለው በአውሮፕላን ተሳፍረው ከሚያቀኑ መንገደኞች መካከል አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሕይወታቸው በበረራ ወቅት ቢያልፍ ምን ይደረጋል?
“አገልግሎት ከመስጠት፣ ወደ ሕይወት አድን እንዲሁም የአስከሬን ሠራተኛ እንሆናለን። በበረራ ላይ ለሞተው ተሳፋሪ መደረግ ያለበትን እና ሌሎች ተሳፋሪውን የማረጋጋት ሥራ እንሠራለን” በማለት ከአስር ዓመት በላይ በበረራ ሠራተኛነት የሠራው ጄይ ሮበርትስ ይናገራል።
አክሎም “ለ300 ተሳፋሪዎች ቁርስ ወይም እራት ማቅረብ ይኖርብናል። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን” ይላል።
ጄይ በአውሮፓ ታላላቅ አየር መንገዶች የካቢን ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በኤምሬትስ አየር መንገድ በበረራ ሠራተኝነት አገልግሏል።
እንደሌሎች የአውሮፕላን ሠራተኞች፣ የተሳፋሪዎች ሞት በበረራ ቢያጋጥም ምን መደረግ እንደሚኖርበት ሥልጠና ወስዷል። ሆኖም እንደ ዕድል ሆኖ በእነዚህ ዓመታት ሞት የገጠመው በአንድ በረራ ላይ ብቻ ነው።
“በአውሮፕላን በረራዎች ላይ ሞት መከሰት በጣም ያልተለመደ ነው። ምናልባት ሞት የሚያጋጥመው ረዘም ያለ በረራ ያላቸው፤ ለረጅም ጊዜ አለመንቀሳቀሳቸው ድንገት አካላዊ ተጽእኖ አድርሶ ከሆነ ነው። አንዳንድ የበረራ ሠራተኞች በሙሉ የሙያ ዘመናቸው ሞት ላያጋጥማቸው ይችላል” ሲል ጄይ ያስረዳል።
በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲሲን በአውሮፓውያኑ 2013 ባተመው ጥናት በበረራ ላይ ሞት “አልፎ አልፎ” የሚያጋጥም ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
ጥናቱ ከአውሮፓውያኑ 2008 – 2010 ከአምስት አየር መንገዶች ወደ ሕክምና ተቋማት የተደረጉ የአደጋ ጊዜ ጥሪዎችን ዳስሷል።
በበረራ ወቅት ድንገተኛ ህመም ካጋጠማቸው መንገደኞች መካከል 0.3 በመቶዎቹ ያህሉ ሕይወታቸው ማለፉን በጥናቱ ላይ አካቷል።
ባለፈው ወር አውስትራሊያውያን ባል እና ሚስት ከሜልበርን ወደ ዶሃ እየበረሩ በነበረበት ወቅት አንዲት ሴት ሕይወቷ በማለፉ አጠገቧ ለመቀመጥ ተገድደው ነበር።
በዚህም የተነሳ በረራቸውም ምን ያህል አሰቃቂ እንደነበር ተናግረዋል።

የበረራ ሠራተኞች አስከሬኗን በብርድ ልብስ ከሸፈኑት በኋላ፤ ቀሪውን አራት ሰዓታት በረራ ከባልየው ሚቸል ሪንግ አጠገብ እንዳስቀመጧት ጥንዶቹ ተናግረዋል።
ወደ ሌላ ወንበር ለማዛወርም በበረራ ሠራተኞቹ እንዳልተጠየቀም እኚሁ ጥንዶች ተናግረዋል።
ጥንዶቹን ያሳፈረው የኳታር አየር መንገድ ተገቢ መመሪያዎችን መከተሉን ገልጾ “ይህ ክስተት ችግር ወይም ጭንቀት ለፈጠረባቸው” ይቅርታን ጠይቋል።
ቢቢሲ በበረራ ወቅት ተሳፋሪዎች ቢሞቱ ምን እንደሚደረግ፣ አስከሬን የሚቀመጥበት መመሪያዎችን በተመለከተ የበረራ ሠራተኞችን እና የአቪዬሽን ባለሙያዎችን አናግሯል።
የበረራ ሠራተኞች በራሳቸው አንድ ሰው ሞቷል ብለው ማረጋገጫ መስጠት አይችሉም።
ይህ መከናወን ያለበት በሕክምና ባለሙያዎች ነው። አንዳንድ ጊዜ በበረራ ላይ የሕክምና ባለሙያዎች ተሳፋሪዎች ሊሆኑ ስለሚችሉ ማረጋገጫ መስጠቱ ወዲያውኑ ይከናወናል።
ካለበለዚያ ግን የሞት ማረጋገጫ የሚሰጠው አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ነው።
አብዛኞቹ አየር መንገዶች አንድ ተሳፋሪ ሕይወቱ አልፏል ብለው ካመኑ ምን መደረግ አለበት ለሚለው የዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) መመሪያዎችን ይከተላሉ።
ሆኖም ፖሊሲዎቹ እንደ አየር መንገዶቹ በተወሰነ መልኩ ይለያያሉ።
- አየር ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ሊያደርግዎ የሚችሉ 8 ምክንያቶች5 ጥር 2025
- በአሁኑ ወቅት የአውሮፕላን አደጋዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ በብዛት እየተከሰቱ ነው?25 የካቲት 2025
- ልብሳችን ወልቆ ተፈትሸናል ሲሉ ኳታር አየር መንገድን የከሰሱ ሴቶች መዝገብ ውድቅ ሆነ11 ሚያዚያ 2024

“አስከሬን ባዶ ወንበር ላይ ይቀመጣል”
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በበረራ ወቅት ተሳፋሪዎች ድንገተኛ ህመም ቢያጋጥማቸው የበረራ ሠራተኞች የመጀመሪያ እርዳታን ይሰጣሉ። እንዲሁም በአውሮፕላኑ ውስጥ የተሳፈሩ የሕክምና ባለሙያዎች ካሉ እርዳታ ይጠይቃሉ።
በተጨማሪም የአውሮፕላኑ አብራሪ መሬት ላይ ካሉ የድንገተኛ ሐኪሞች መመሪያዎችን ለማግኘት የመገናኛ ሥርዓቶችን እንደሚጠቀም የቀድሞ አብራሪ እና በባኪንግሃምሻየር ኒው ዪኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ማርኮ ቻን ያስረዳሉ።
አስፈላጊ ከሆነም ካፒቴኑ በአስቸኳይ የበረራ አቅጣጫውን ሊቀይር ይችላል።
ሆኖም ተሳፋሪን ሁልጊዜም ማዳን አይቻልም።
በዕይታ መመሪያ መሠረት ተሳፋሪው ሞቷል ተብሎ ከታሰበ፣ የሰውዬውን ዓይን መክደን እንዲሁም አስከሬኑ የሬሳ መያዣ ካለ በዚያ ውስጥ መከተት አለበት።
ካለበለዚያ አስከሬኑ እስከ አንገቱ ድረስ በብርድ ልብስ ሊሸፈን ይገባል።
አውሮፕላኖች ያላቸው ቦታ ውስን ነው።
በዚህም የተነሳ ሌሎች ተሳፋሪዎችን ሳይረብሹ እና የአውሮፕላኑን ደኅንነት አደጋ ውስጥ ሳይከቱ አስከሬኖችን ለማስቀመጥ ተስማሚ ቦታ ማግኘት ፈታኝ ነው።
በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር መመሪያ መሠረት አስከሬኑ ከተቻለ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ርቆ ወደሚገኝ ወንበር ወይም ወደ ሌላ የአውሮፕላኑ ክፍል መወሰድ አለበት።
ነገር ግን አውሮፕላኑ ከሞላ ተሳፋሪው ከመሞቱ በፊት ተቀምጦበት ወደነበረው ስፍራ ይመለሳል።
ለአጭር በረራዎች የሚያገለግሉ አነስተኛ አውሮፕላኖች በአብዛኛው አስከሬኖችን ለማስቀመጥ በቂ ቦታ የላቸውም።
እናም በእነዚህ አውሮፕላኖች ሞቶች ሲከሰቱ “ተሳፋሪዎችን ከተፈጠረው ነገር ለመከላከል” ቦታ እንደሌላቸው በኮቬንትሪ ዩኒቨርስሪ በአቪዬሽን አስተዳደር ተባባሪ ፕሮፌሰር ኢቫን ስቲቨንሰን ይናገራሉ።
በእነዚህ አውሮፕላኖች ላይ ያለው ቦታ “በጣም የተገደበ ነው። በእንደነዚህ ዓይነት አውሮፕላኖች ውስጥ አንድ ሰው ሕይወቱ ካለፈ ተቀምጦበት በነበረበት ወንበር ላይ አስከሬኑን ማስቀመጥ አስፈላጊ መሆኑ አይቀርም” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
የአደጋ ጊዜ መውጫን የሚከለክል ከሆነ፣ ባዶ ቢሆንም በዚያ ስፍራ አስከሬኖችን ማስቀመጥ አይቻልም። በረጅም በረራዎች ወቅት በሠራተኞች ማረፊያ አስከሬኖች መቀመጥ እንደማይችሉ ጄይ ያስረዳል።
አውሮፕላኖች ባላቸው ጠባብ ስፍራ የተነሳ አስከሬኖች ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ማዛወር ከባድ እንደሆነም ጄይ ይገልጻል።
በኳታር አየር መንገድ ላይም የተፈጠረው ይህ ነው። የሞተውን ተሳፋሪ ከተቀመጠበት ስፍራ ማዛወር እንዳልተቻለ ተገልጿል።
በበረራ ወቅት ድንገተኛ ህመም ከገጠመ የተሳፋሪውን ሕይወት ለማዳን አንድ አውሮፕላን፣ የበረራውን አቅጣጫውን ሊቀይር ይችላል።
ነገር ግን ቀድሞውኑ ሞቷል ተብሎ ከታሰበ አቅጣጫ እንደማይቀየር የበረራ ሠራተኞች እና የአቪዬሽን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የአውሮፕላኑ ካፒቴን የተሳፋሪውን ሞት በተቻለ ፍጥነት ለአየር መንገዱ የኦፕሬሽን ማዕከል እና የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ያሳውቃል።
አውሮፕላኑ ሲያርፍም የአካባቢው ባለሥልጣናት በአየር ማረፊያው ደርሰው እንደሚቀበሉት ፕሮፌሰር ስቲቨንሰን ይናገራሉ።
ተሳፋሪው ብቻውን እየተጓዘ ከነበረ የአካባቢው ባለሥልጣናት ወይም የአየር መንገዱ ተወካዮች የሟቹን ቤተሰቦች ያነጋግራሉ።

“በመታጠቢያ ቤቴ አለቀስኩ”
በበረራ ሠራተኝነት ለአስር ዓመታት የሠራችው አሊ መርፊ የአንድ ተሳፋሪ ሞት ገጥሟታል።
ከአክራ ጋና ወደ ለንደን ብቻውን ሲጓዝ የነበረ ተሳፋሪ በተቀመጠበት ወንበር ላይ ራሱን ሳተ።
አጠገቡ ተቀምጠው የነበሩ ተሳፋሪ ይህንኑ ለበረራ ሠራተኞች መናገራቸውን ተከትሎም ተሳፋሪው እስትንፋስ እና የልብ ምት እንደሌለው ተረዱ።
የበረራ ሠራተኞቹ ለተሳፋሪ ድንገተኛ እርዳታ ለመስጠት ወደ መተላላፊያው ወሰዱት።
አሊ እና ሌሎች የበረራ ሠራተኞች ለ40 ደቂቃዎች ያህል ያለ እረፍት የመጀመሪያ የነፍስ አድን እርዳታ ሰጡት።
ካፒቴኑም የበረራውን አቅጣጫ በመቀየር ወደ ፈረንሳይዋ ከተማ ሊዮን አቀና።
አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ የሕክምና ባለሙዎች ራሱን የሳተውን ተሳፋሪ ይዘውት ሄዱ።
ሆኖም ተሳፋሪው ሕይወቱ ማለፉን ባለሙያዎቹ አረጋገጡ።
“በመጨረሻው እስትንፋሱ ወቅት አቀፍኩት። ሌላ ሰው ይህንን ቢያደርግለት ይመርጥ ይሆናል። የነበርኩት ግን እኔ ብቻ ነኝ” ትላለች።
አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ መንገደኞች በፀጥታ እና በድንጋጤ ተውጠው ነበር ትላለች።
ተሳፋሪ ሕይወቱ ሲያልፍ መመልከት ለአሊ አሳዛኝ ነገር ነበር።
“ቤት ሄጄ መታጠቢያ ቤት ገብቼ አለቀስኩ። የተሳፋሪውን እስትንፋስ ከሳምንት በኋላም ጠረኑም ይሰማኝ ነበር፤ አሰቃቂ ነው” ብላለች።
በበረራ ወቅት ተሳፋሪ ከሞተ፣ የበረራ ሠራተኞች የማማከር ሕክምናን ጨምሮ ከሥራ እረፍት እንዲወስዱ በማድረግ እርዳታ እንደሚደረግላቸው ጄይ ይናገራል።
“እኛ ዶክተሮች፣ ነርሶች አይደለንም። ምን ማድረግ እንዳለብን ብንሰለጥንም ብዙ የሚያጋጥመን ስላልሆነ ከባድ ነው” ይላል ጄይ።