
16 መጋቢት 2025, 09:54 EAT
ኢራን የአገሪቱን እስላማዊ ሕግ የሚጻረሩ አለባበሶች የሚከተሉ ሴቶችን ለመቆጣጠር ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና መተግበሪያዎች እየተጠቀመች መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።
የተመድ መርማሪዎች እንዳሉት፣ የኢራን የደኅንነት ሠራተኞች “በመንግሥት የሚደገፍ ሥርዓት አልበኝነት” እየተከተሉ ነው።
ዜጎች ልዩ የስልክ መተግበሪያዎች በመጠቀም የአለባበስ ሕግ ያልተከተሉ ሴቶች ላይ ጥቆማ እንዲሰጡ እየተደረገ ነው።
ድሮንና የደኅንነት ካሜራ በመጠቀም በቴህራንና ደቡብ ኢራን ሂጃብ ያላደረጉ ሴቶችን ለመለየትም መንግሥት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ሕጉን የተጻረሩ ወይም የተቃወሙ ሴቶች ይታሰራሉ፤ ይደበደባሉ፤ በፖሊስ ይዞታ ሥር ሳሉም ይደፈራሉ።
በኢራን ምርመራ ያደረገው ቡድን (Independent International Fact-Finding Mission on the Islamic Republic of Iran) ግኝቱን ይፋ ያደረገው እአአ በ2022 ማሳ አሚኒ በፖሊስ ይዞታ ሥር ሳለች ከሞተች በኋላ ነው።
ፖሊስ ያደረሰባት “አካላዊ ጥቃት” ለሞት እንደዳረጋት መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል።
የ22 ዓመቷ ማሳ በኢራን የሞራል ፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባታል።
ሞቷ በመላው ኢራን ሕዝባዊ ቁጣ አስነስቷል። መንግሥት “በልብ ድካም” መሞቷን ገልጿል።
እስራትና እንግልት ሳይፈሩ በርካታ ኢራናውያን ተቃውሟቸው በአደባባይ ማሰማታቸው ይታወሳል።
“ተቃውሞው ከተነሳ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ በኢራን ሴቶች በሥርዓቱ የሚደርስባቸው መድልዎ እንደቀጠለ ነው። በተለይም ከአስገዳጅ የሂጃብ ሕግ ጋር በተያያዘ መላው ሕይወታቸው በቁጥጥር ውስጥ ነው” ይላል ሪፖርቱ።
መንግሥት ጉዳዩን “የዜግነት ኃላፊነት” በማስመሰል ሴቶች ለሂጃብ ሕግ ተገዢ እንዲሆኑ “ሥርዓት አልበኛ” የሆነ አሠራር መተግበሩ በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
- የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የደቡብ አፍሪካው አምባሳደር “በአሜሪካ ተቀባይነት የላቸውም” አሉ16 መጋቢት 2025
- ዶናልድ ትራምፕ በጦርነት ጊዜ የሚታወጅ ሕግ ተጠቅመው ስደተኞችን እንዳያባርሩ እገዳ ተጣለባቸው16 መጋቢት 2025
- የኢላን መስክ መንኩራኩር ለ9 ወራት ሕዋ ላይ የቆዩትን የጠፈር ተመራማሪዎች ለመመለስ ተላከ16 መጋቢት 2025
በቴህራን ባለው አሚርካቢር ዩኒቨርስቲ ሴቶች ሂጃብ መልበሳቸውን ለመለየት ፊታቸውን የሚያነብ የፌሻል ሬኮግኒሽን መሣሪያ መገጠሙ ተገልጿል።
በኢራን ዋና አውራ ጎዳናዎች የደኅንነት ካሜራዎች ተገጥመዋል። ሂጃብ ያላደረጉ ሴቶችን ለመለየትም ይውላሉ።
‘ናዛር’ የተባለ መተግበሪያ በመጠቀም የኢራን ፖሊስ ሕዝብ ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ምርመራው ይጠቁማል። ይህም ታክሲ ውስጥ፣ ባስ ውስጥ፣ ባቡር ውስጥና አምቡላንስ ውስጥም ሳይቀር የሚደረግ ክትትል ነው።
“የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች የሂጃብ ሕግ ተጥሷል ብለው ሲያስቡ ያሉበትን ቦታና ሰዓት እንዲሁም የመኪና ታርጋ ማስገባት ይችላሉ። በዚህ መንገድ ፖሊስ ይጠራል” ይላል ሪፖርቱ።
በዚህ ወቅት ለመኪናው ባለቤት የጽሑፍ መልዕክት ይላካል። መልዕክቱ ችላ ከተባለ ተሽከርካሪው እንዲቆም ይደረጋል።
የተመድ መርማሪዎች 300 ተጎጂዎችና የዓይን እማኞች አነጋግረዋል።
የኢራንን የሕግ ሥርዓትም ፈትሸዋል። የሕግ ሥርዓቱ ገለልተኛ አይደለም ብለዋል።
ተጎጂዎች አካላዊ ስቃይ እንደተፈጸመባቸውና ቤተሰቦቻቸው ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሳቸውም ገልጸዋል።
በሦስት ልጆችና ሦስት አዳጊ ተቃዋሚዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ መፈጸሙንና ራሳቸውን አጥፍተዋል መባሉን ሪፖርቱ ያሳያል።
በፖሊስ ይዞታ ሥር ወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈጸምም ተጠቁሟል። ሴቶች ክፉኛ እንደሚደበደቡና በቡድን እንደሚደፈሩም ሪፖርቱ ይገልጻል።
ሪፖርቱ ከቀናት በኋላ ለተመድ የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ይቀርባል።