
16 መጋቢት 2025, 08:56 EAT
የአሜሪካ ፌዴራል ዳኛ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጦርነት ወቅት የሚታወጅ ሕግ ተጠቅመው ስደተኞች በገፍ እንዳያባርሩ አገዱ።
227 ዓመታት የሆነው ሕግ አሜሪካ ጦርነት ውስጥ ስትገባ ብቻ የሚታወጅ ነው ተብሏል።
ትራምፕ ቅዳሜ ባወጡት መመሪያ ከቬንዙዌላ የመጡ ስደተኞች ትሬን ዴ አራጉዋ የተባለው የወንበዴ ቡድን አባላት አሜሪካ ላይ “ያልተለመደ ጦርነት ከፍተዋል” በማለት ኤሊየን ኢነሚስ የተሰኘውን የ1798 ሕግ ጠቅሰው እንደሚያባሯቸው ተናግረው ነበር።
ነገር ግን የፌዴራሉ ዳኛ ጄምስ ቦአስበርግ ቅዳሜ አመሻሹን የትራምፕን ውሳኔ ለሚቀጥሉት 14 ቀናት ማገዳቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ዳኛው ውሳኔያቸውን ባሳወቁበት ወቅት አውሮፕላኖች የተባረሩ ስደተኞች ጭነው እየሄዱ መሆናቸውን ሰምተው እንዲመለሱ ማዘዛቸውን ዋሺንግተን ፖስት ዘግቧል።
ትራምፕ ያጣቀሱት ሕግ አሜሪካ በጦርነት ወቅት የሀገር ደኅንነትን ስጋት ላይ ይጥላሉ ብላ የምታስባቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አውላ ከሀገር የምታስወጣበት ነው።
- የትግራይ ክልል ቀውስ፡ ከፕሪቶሪያ ወዲህ መቼ ምን ተከሰተ?15 መጋቢት 2025
- አሜሪካ በሁቲ አማጺያን ላይ “የሰላ እና ጠንካራ” የአየር ጥቃት ፈጸመች16 መጋቢት 2025
- የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የደቡብ አፍሪካው አምባሳደር “በአሜሪካ ተቀባይነት የላቸውም” አሉ16 መጋቢት 2025
ይህ ሕግ ለመጨረሻ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓናዊያንን ለማባረር ነበር።
ትራምፕ ይህ አወዛጋቢ ሕግ ተጠቅመው ስደተኞችን በገፍ እንደሚያባርሩ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል ገብተው ነበር።
አሜሪካን ሲቪል ሊበርቲስ ዩኒየን የተባለው ማኅበር እና ሌሎች የመብት ተሟጋች ተቋማት ትራምፕ ትዕዛዝ ከማስተላለፋቸው በፊት ውሳኔውን ተቃውመው ክስ መሥርተዋል።
የፌዴራል ዳኛው፤ ትራምፕ ያሳለፉት ውሳኔ ትክክለኛ መሠረት የሌለው ነው ማለታቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ አስነብቧል።
አንድ ጠበቃ ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት ሶስት አውሮፕላኖች ቬንዙዌላዊያንን ጭነው እየተጓዙ ነበር። ቢቢሲ በግሉ ይህን ማጣራት አልቻለም።
ጉዳዩ አስፈላጊ የሚባሉ የሕግ ሒደቶችን አልፎ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊደርስ ይችላል።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ሕገ-ወጥ ስደተኞች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ እና የሸቀጦችን ዋጋ እንደሚያወርዱ ዝተዋል። ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ የአሜሪካ የስደተኞች ሥርዓት ላይ ብዙ ለውጦችን አካሂደዋል።
የመብት ተሟጋቾችና የሕግ ባለሙያዎች አሜሪካ ኤሊየን ኢነሚስ የተባለውን ሕግ መጠቀም የምትችለው በግልፅ ከሌላ ሀገር ጋር ጦርነት ውስጥ ስትገባ ነው ይላሉ።
በአሜሪካ ሕገ-መንግሥት መሠረት ጦርነት ማወጅ የሚችለው ኮንግረሱ ብቻ ነው።
በትራምፕ ትዕዛዝ መሠረት ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ የሆነ ሁሉም የቬንዙዌላ ዜጎች “በቁጥጥር ሥር ውለው መጤ ጠላት ተብለው” ይባረራሉ።
ትራምፕ ትዕዛዙን ሲያወጡ አንድ ግለሰብ የአመፀኛ ቡድን አባል ስለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለ የሚለውን አላብራሩም።