የአየር ጥቃት

16 መጋቢት 2025, 08:24 EAT

አሜሪካ “የሰላ እና ጠንካራ” ያለችውን የአየር ጥቃት በየመን የሁቲ አማጺያን ላይ ፈጸመች።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት አማጺያኑ በቀይ ባሕር መርከቦች ላይ ላደረሱት ጥቃት ምላሽ የአየር ጥቃቱ ተፈጽሟል።

በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው “በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን በአሜሪካ መርከብ ላይ ሚሳዔል ተኩሰው ወታደሮቻችንንና አጋሮቻችንን ዒላማ አድርገዋል። የባሕር ላይ ዝርፊያቸው፣ ነውጠኛነታቸውና የሽብር ድርጊታቸው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ አሳጥቷል። የብዙዎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ ከቷል” ብለዋል።

በሁቲ የሚመራው የጤና ሚኒስትር ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸውንና ዘጠኝ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል።

ከጋዛ ጦርነት መጀመር በኋላ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረስ የጀመረው ቡድኑ ለአሜሪካ የአየር ጥቃት ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።

በሰንአ እና በሰሜናዊቷ ግዛት ሳዳ ተከታታይ የአየር ጥቃት ድምጽ ሲሰማ እንደነበር ተገልጿል።

እስራኤል ጠላት ናት የሚለው አማጺ ቡድኑ ሰንአንና የየመንን ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ይቆጣጠራል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ያልተረጋገጡ ምሥሎች ወታደራዊ መቀመጫ አካባቢ ከፍተኛ የፍንዳታ ጭስ ያሳያሉ።

የሁቲ አማጺያን አሜሪካና ዩኬ በሰንአ ነዋሪዎች ላይ የተቃጣ “ክፉኛ” ጥቃት ፈጽመዋል ብለዋል።

አሜሪካ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ዩኬ አልተሳተፈችም።

ከዚህ ቀደም ግን ለአሜሪካ ጥቃት ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች።

ትራምፕ ግባቸውን ለመምታት “ከፍተኛ አቅም” እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባስ አርጋቺ የአሜሪካ መንግሥት “የኢራንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚቆጣጠርበት አንዳችም ኃይልና አቅም የለውም። የኢራንን ሕዝብ መግደል አቁሙ። የእስራኤልን የዘር ጭፍጨፋና ሽብር መደገፍ አቁሙ” ብለዋል።

ሁቲዎች እስራኤልን በመንቀፍ የእስራኤል፣ አሜሪካና ዩኬ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።

ሁለት መርከብ ሲያሰጥሙ አንድ መርከብ ደግሞ ተቆጣጥረው የተወሰኑ የመርከብ ሠራተኞች ገድለዋል።

ምዕራባውን ቀይ ባሕር ላይ መርከብ የሚጠብቅ ኃይል ቢያሰማሩም የአማጺያኑን ጥቃት ማስቆም አልተቻለም።

እስራኤልም ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ በሁቲዎች ላይ ጥቃት ስትፈጽም ነበር።

ከዓለም የባሕር ንግድ ወደ 15% በሚያልፍበት ቀይ ባሕር መርከብ ማሳለፍ ያቆሙ ተቋማት ነበሩ።

መንገድ በመቀየራቸው ምክንያት ጉዞ ላይ የሚያሳልፉት ጊዜም ጨምሯል።

ትራምፕ ሁቲዎችን “ከተግባራችሁ ካልተቆጠባችሁ ከዚህ ቀደም አይታችሁ በማታውቁት ሁኔታ አካባቢውን ገሃነም እናደርገዋለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሁቲዎች በምላሹ “ይህ ጥቃት እንዲሁ የሚታለፍ አይሆንም። የታጠቀው የየመን ኃይል የተባባሰውን ግጭት ከዚህም በላይ እንዲባባስ ያደርጋል” ብለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም ከሁቲዎች ጀርባ ያለችውን ኢራንን ማስጠንቀቃቸውን ተናግረዋል።

እአአ ከኅዳር 2023 እስከ ጥቅምት 2024 ሁቲዎች 190 ጥቃቶች በቀይ ባሕር ላይ ሰንዝረዋል።