የሕጻናት ወሲባዊ ጥቃትን የሚከላከሉት ባለሙያዎች

18 መጋቢት 2025, 07:02 EAT

ማቤል ቤት ውስጥ አያት ናት። ጊዜዋን ከልጅ ልጆቿ ጋር በማሳለፍ የምትደሰት ምርጥ አያት።

ሥራ ቦታዋ ስደርስ ግን ኢንተርኔት ላይ በጣም “አስጸያፊ” የሕፃናት ወሲባዊ ጥቃትን ለመመልከት ትገደዳለች።

የፖሊስ እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ምሥሎቹን እንዲያነሱ ለማገዝ ከሚሠራ እና ፈቃድ ካላቸው ጥቂት ድርጅቶች ለአንዱ ትሠራለች።

የኢንተርኔት ዋች ፋውንዴሽን (አይደብሊውኤፍ) ይባላል። ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ ምሥሎች ከድረ-ገጾች ላይ እንዲነሱ አድርጓል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚዘጋጁ ተመሳሳይ ምሥሎች ቁጥርም አድጓል። የእነዚህ ምሥሎች ቁጥር በአምስት እጥፍ ገደማ ጨምሯል።

የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ማቤል የምትመለከታቸው ምሥሎች “ይዘት በጣም አሰቃቂ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ መዘጋጀትም አልነበረባቸውም ነበር” ትላለች።

“ተጠቂዎቹ ሕጻናት በመሆናቸው ከችግሩ ነጻ መሆን አይቻልም። በጣም አስጸያፊ ነው።”

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ማቤል (ስሟ ተቀይሯል) አንዳንድ በጣም የከባድ እና አሰቃቂ ምሥሎች አጋልጣለች። ቤተሰቧ የዕለት ሚናዋን ለመወጣቷ ትልቅ ምክንያት እንደሆነ ተናግራለች።

ከሰሜን ዌልስ የመጣችው ማቤል ራሷን “አስጨናቂ” ብላ ትገልጻለች። ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ መጥፎ ምሥሎችን የሚያጋሩ የወንጀል ቡድኖችን ማጋለጥ እንደምትወድ ትናገራለች።

የፋውንዴሽኑ ባለሙያዎች ከወንጀለኛ ቡድኖች እና ሥራቸውን ከሚቃወሙ ሰዎች እንዲጠበቁ እንዲሁም ደኅንነት እንዲሰማቸው ማንነታቸው እንዳይገለጽ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል።

“ጠዋት ወደ ቢሮ ስትገባ፣ ቀኑን ሙሉ መልካም ነገር የምትሠራበት እና መጥፎ ሰዎችን የምታናድድበት ብዙ ሥራ የለም። እኔ ግን ሁለቱንም አግኝቻለሁ” ብላለች ማቤል።

“ምሥሉን ሳነሳ መጥፎ ሰዎች እነዚያን ምሥሎች እንዳይደርሱባቸው እየተከላከልኩ ነው።”

“ልጆች እና የልጅ ልጆች ስላሉኝ ለእነሱ ደኅንነቱ የተጠበቀ ኢንተርኔትን ማቅረብ ብቻ ነው የምፈልገው።”

“ሰፋ ባለ መልኩ ካየነው በዓለም ዙሪያ ካሉ የሕግ አስከባሪዎች ጋር በመተባበር ምርመራ እንዲያደርጉ እና ወንበዴዎችን ለማጥፋት እንሠራለን።”

መቀመጫውን ካምብሪጅ ያደረገው አይደብሊውኤፍ በይነ መረብ ላይ የሕጻናት ጥቃት ይዘትን ለመከታተል ፈቃድ ካላቸው ሦስት ድርጅቶች አንዱ ነው።

ባለፈው ዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ ምሥሎችን እና ቪዲዮዎችን ሊይዙ የሚችሉ 291 ሺህ 270 ድረ-ገጾችን እንዲያነሱ ረድቷል።

ዘንድሮ ካለፈው በአምስት እጥፍ የሚበልጥ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጁ የሕጻናት ወሲባዊ ጥቃት ምሥሎችን ማውረዱን ፋውንዴሽኑ አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት 51 የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ ወደ 245 ከፍ ብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ባለፈው ወር በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጁ ምሥሎችን ችግር ለመፍታት አራት አዳዲስ ሕጎችን አውጥቷል።

ታምሲን ማክኔሊ

ይዘቱ ማየት ለታምሲን ማክኔሊ እና ለ30 የሥራ ባልደረቦቿ፣ ቀላል የሚባል ባይሆንም ሥራቸው ልጆችን ለመጠበቅ እንደሚረዳ ታውቃለች።

“ለውጥ እናመጣለን። ለዚህም ነው የምሠራው” ስትል የቡድን መሪዋ ተናግራለች።

“ሰኞ ጧት ስገባ ከሁለት ሺህ የሚበልጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደዚህ ዓይነት ምሥሎች እንዳጋጠማቸው ሪፖርት አድርገውልናል። በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሪፖርቶችን እናገኛለን።”

“ሁሉም ሰው ይህ ችግር መሆኑን እንደሚያምን ተስፋ አደርጋለሁ። እንዳይከሰት ለማድረግም የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ።”

“ሥራው ባይኖር እመኛለሁ። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን በይነ መረብ ላይ ክፍተቶች እስካሉ ድረስ እንደ እኔ ያሉ ሥራዎች ያስፈልጉ ይሆናል።”

“ስለሥራዬ ስነግራቸው ብዙዎች ይህ ሥራ ስለመኖሩም ለማመን ይቸገራሉ። ቀጥለው ደግሞ ለምን ይህን ሥራ ትሠሪያለሽ? ይላሉ።”

እነማቤል በየጊዜው የስነልቦና ድጋፍ ያገኛሉ

ብዙ የቴክኖሎጂ ድርጅት ሠራተኞች ሥራው የአእምሮ ጤንነታችንን ጎድቷል በሚል ጉዳዩን ወደ ሕግ መርተውታል። ፋውንዴሽኑ ግን ሥራውን “ወርቅ” ነው ብሏል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሠራተኞች በየወሩ በአስገዳጅነት የምክር አገልግሎት፣ ሳምንታዊ የቡድን ስብሰባዎች እና መደበኛ የደኅንነት ድጋፍ ያገኛሉ።

“ከመደበኛዎቹ ድጋፎች ጎን ለጎን ኢ-መደበኛ ባልሆነ መልኩ ፑልን ጨምሮ የተለያዩ የመዝናኛ አማራጮች ተዘጋጅተውልናል” ብላለች ማቤል።

“እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ሁላችንንም እዚህ እንድንቆይ ረድተውናል።”

አይደብሊውኤፍ

አይደብሊውኤፍ የግል ስልኮችን ቢሮ ውስጥ መጠቀምን በጥብቅ ይከለክላል። ማንኛውም የሥራ ኢሜይሎችም እንዳይወጡ የሚያረጋግጥ ጥብቅ መመሪያዎች አሉት።

ማነን (ስሟ የተቀየረ) ለድርጅቱ ለመሥራት ማመልከቻ ብታስገባም መሥራት እንደምትችል ግን እርግጠኛ አልነበረችም።

በሃያዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው እና ከደቡብ ዌልስ የመጣችው ማነን “አስፈሪ ፊልሞችን ማየት እንኳን አልወድም። ስለዚህ ሥራውን መሥራት እንደምችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ አልነበርኩም” ስትል ተናግራለች።

“ነገር ግን የሚሰጠው ድጋፍ በጣም ጠንካራ እና ሰፊ በመሆኑ የሚያረጋጋ ነው።”

“በሁሉም መልኩ ኢንተርኔትን የተሻለ ቦታ እያደረጉት ነው። በየቀኑ ይህን መሰል ትልቅ ሥራ የሚከናወንባቸው ብዙ ሥራዎች አሉ ብዬ አላስብም።”

ማነን

ዩኒቨርሲቲ እያለች ሥነ ልሳን አጥንታለች። ይህም በኢንተርኔት ቋንቋ ዙሪያ እንድትማር ስላገዛት ለፋውንዴሽኑ ሥራ ያላትን ፍላጎት ጨምሮታል።

“ወንጀለኞች የራሳቸው ማኅበረሰብ ያላቸው ናቸው ብሎ መግለጽ ይቻላል። የራሳቸውን ቋንቋ ወይም ምልክት በመጠቀም ለመደበቅ ይሞክራሉ” ብላለች ማነን።

“በዩኒቨርስቲ የተማርኩትን ተግባራዊ በማድረግ እና በገሃዱ ዓለም በመተግበር የልጆች ወሲባዊ ጥቃት ምሥሎችን መፈለግ እና ማኅበረሰቡን መርዳት በእውነት አስደሳች ነው” ትላለች።