
18 መጋቢት 2025, 07:09 EAT
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የየመን ሁቲዎች በዓለም አቀፍ የመርከብ መስመሮች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ኢራን “የከፋ” እርምጃ እንደሚጠብቃት አስጠነቀቁ።
የኢራን አመራር “በሁቲዎች ለሚተኮሰው እያንዳንዱን ሚሳዔል” ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብለዋል።
በኢራን የሚደገፉት አማፂያኑ በሁለት ቀናት ብቻ ሦስት ጊዜ የአሜሪካ አውሮፕላን ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተናግረዋል።
እሁድ ዕለት አሜሪካ በየመን ከባድ የአየር ድብደባ ከፈጸመች በኋላ፣ የሁቲ አማፂያን የአሜሪካ አየር ኃይል ንብረት የሆነው እና በቀይ ባሕር ላይ የሚገኘውን አውሮፕላን ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
ፔንታጎን ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ የተደረገ ትልቁ የአየር ጥቃት ባለው የአየር ጥቃት ከቅዳሜ ጀምሮ በየመን 30 ዒላማዎችን መደብደቡን ገልጿል።
ትራምፕ ሰኞ ዕለት በትሩዝ የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ “ከአሁን ጀምሮ ከሁቲዎች የሚተኮሰው እያንዳንዱ ሚሳዔል ከኢራን ጦር እና አመራር የተተኮሰ እንደሆነ አድርገን ነው የምናየው ብለዋል።
“እናም ኢራን ተጠያቂ ትሆናለች፤ ምላሹንም ይቀበላሉ፤ ምላሹም አስከፊ ይሆናል!”
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ኢራንን ለቡድኑ የገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ እና የመረጃ ድጋፍ ታደርጋለች በማለት ቢከስሷትም፣ቴህራን ግን አስተባብላለች።
የኢራን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑክ ሰኞ ዕለት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በፃፉት ደብዳቤ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት በየመን ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የጣሰ መሆኑን በመግለጽ አገራቸው በቀጠናው ውስጥ ምንም አይነት አለመረጋጋትን የሚፈጥር ተግባር እንደሌላት ገልጸዋል።
- አሜሪካ በየመን በፈጸመችው አዲስ ጥቃት 53 ሰዎች መሞታቸውን የሁቲ አማፂያን ገለፁ17 መጋቢት 2025
- በቀይ ባህር ላይ መርከቦችን እያጠቁ ያሉት የየመን ሁቲ አማጽያን እነማን ናቸው?22 ታህሳስ 2023
- ፍጥጫ ከሁቲዎች ጋር፡ የየመን አማፂያን ምዕራባውያንን ለመገዳደር ምን ያህል አቅም አላቸው?6 የካቲት 2024
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
አምባሳደር አሚር ሰኢድ ኢራቫኒ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ “መሰረተ ቢስ ክስ” ሰንዝራለች ሲሉ ማጣጣላቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የፔንታጎን ባለስልጣናት ሰኞ ዕለት በሰጡት አጭር መግለጫ አሜሪካ በየመን ላይ ያደረሰችው ጥቃት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከተፈቀደው ጥቃት በተለየ ሰፊ ዒላማ ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።
ሌተና ጄኔራል አሌክስ ግሪንኬዊች እንደተናገሩት የሁቲ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ባለሙያዎች በዒላማው ውስጥ ከተካተቱት መካከል ናቸው።
አክለውም “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ምንም ዓይነት ተጨባጭ መረጃ የለም” ብለዋል።
ዋሽንግተን በበኩሏ ከሟቾቹ መካከል አንዳንድ ቁልፍ የሁቲ ሰዎች እንደሚገኙበት ተናግራለች፤ ቡድኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አልሰጠም።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሴን ፓርኔል፣ ዩናይትድ ስቴትስ በአገሪቱ የሥርዓት ለውጥ አትፈልግም ብለዋል።
አክለውም “ይህ ዘመቻ ጥቃት የመፈፀም አቅማቸውን ለመቀነስ እና በቀጠናው የመርከብ መስመሮችን ክፍት ለማድረግ እንዲሁም አገራችንን ለመጠበቅ የሚደረግ ነው” ብለዋል።
እሁድ ጠዋት ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ የምትገኘው ዩኤስኤስ ሃሪ ኤስ ትሩማን (USS Harry S Truman) የተሰኘች የአሜሪካ አውሮፕላን ጫኝ መርከብ ላይ ያነጣጠረ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን አስወነጭፈዋል።
የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላኖች ወደ 11 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትተው መጣላቸውን አንድ የአገሪቱ ባለስልጣን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ አክለውም ሁቲዎች ከዩኤስኤስ ሃሪ ኤስ ትሩማን አጭር ርቀት ላይ የወደቀ ባለስቲክ ሚሳኤል አስወንጭፈው እንደነበር ገልፀዋል።
ቢቢሲ የአማፂ ቡድኑ አድርሼዋለሁ ስላለው ሌላ ጥቃት ፔንታጎንን የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
ሰኞ ዕለት የፔንታጎን ባለስልጣናት የሁቲ አማፂያን፣ መርከብ ላይ ያነጣጠረ ሚሳዔል ቢተኩሱም ከዒላማው 160 ኪሎ ሜትር ርቆ መውደቁን ተናግረው ውጤታማ አልነበረም ሲሉ አስተባብለዋል።
ሁቲዎች በየመን አል ጁፍ እና ሁዳይዳህ አካባቢዎች አሜሪካ በፈጸመችው የአየር ጥቃት አምስት ሕጻናትን ጨምሮ 53 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።
ቢቢሲ የሟቾቹን ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
አሜሪካ ቅዳሜ እና እሁድ በቡድኑ ላይ ተጨማሪ የአየር ድብደባ ፈጽማለች።
ሁቲዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የጣለችውን እገዳ እስክታነሳ ድረስ በቀይ ባሕር ላይ በሚጓጓዙ መርከቦች ላይ ማነጣጠራቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሁቲዎች በእስራኤል እና ሃማስ መካከል በሚደረገው ጦርነት ፍልስጤማውያንን በመደገፍ የቆሙ መሆናቸውን የሚገልፁ ሲሆን፣ ምንም እንኳ እውነት ባይሆንም ዒላማ የሚያደርጉት ከእስራኤል፣ ከአሜሪካ ወይም ከእንግሊዝ ጋር የተገናኙ መርከቦችን ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።
እስራኤልን እንደ ጠላት የሚቆጥረው እና በኢራን የሚደገፈው አማፂ ቡድኑ፣ ሰነዓን እና የየመንን ሰሜናዊ ምዕራብ ይቆጣጠራል።
አማፂ ቡድኑ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የአገሪቱ መንግሥት አይደለም።