
18 መጋቢት 2025, 07:14 EAT
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን የሰላም ስምምነት ዙርያ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ያደርጉታል ተብሎ በጉጉት ከሚጠበቀው የስልክ ውይይት በፊት “በበርካታ ነጥቦች” ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናገሩ።
ትራምፕ ማክሰኞ ጠዋት ከፑቲን ጋር እንደሚነጋገሩ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ለጥፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ምንም እንኳን “ብዙ ሊሰራባቸው የሚገቡ” የስምምነቱ አካላት ይቀራሉ ብለዋል።
“እያንዳንዱ ሳምንት ከሁለቱም ወገኖች 2,500 ወታደር ይቀጥፋል፤ እናም አሁኑኑ ማብቃት አለበት። ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የሚደረገውን የስልክ ውይይት በጣም በጉጉት እጠባበቃለሁ” ሲሉ ጽፈዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ለጋዜጠኞች “የሠላም ስምምነት ላይ፣ የተቁስ አቁም ላይ መድረስ እንችል እንደሆን፣ሠላም ማምጣት እንችል እንደሆነ እናያለን፣ እናም ደግሞ ይህንን ማድረግ የምንችል ይመስለኛል” ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሰኞ ምሽት ባደረጉት ንግግር ፑቲንን ጦርነቱን አራዝሟል ሲሉ ከስሰዋል።
“ይህ ምክረ ሃሳብ ከረዥም ጊዜ በፊት ተግባራዊ ሊሆን ይችል ነበር” ያሉት ሚኒስትሩ፣ “በጦርነት ውስጥ እያንዳንዱ ቀን የሰው ሕይወት ማለት ነው” ብለዋል።
በትራምፕ አስተዳደር ወገን እስካሁን ድረስ የተኩስ አቁም ውይይቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ወጥነት የሌላቸው መረጃዎች ነበሩ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጅዳ ከዩክሬን ባለስልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ እንደተናገሩት ውይይቱ “ጠቅለል ባለ መልኩ የድርድር ሂደት ምን እንደሚመስል” ላይ የተደረገ እንጂ “ነጥብ በነጥብ ” የተደረገ አልነበረም ብለዋል።
ሞስኮ ውስጥ ሐሙስ ዕለት ከፑቲን ጋር የተገናኙት የዩናይትድ ስቴትስ ተወካይ ስቲቭ ዊትኮፍም በጉዳዩ ላይ ቁጥብ መረጃ ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ፑቲን ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጉ ከሆነ እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዜሌንክሲ የተኩስ አቁም ሃሳብ ላይ በመስማማት ያሳዩትን “ድፍረት” አድንቀው ሩሲያም ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ ጠይቀዋል።
“ሞት በቃ። በቂ ሕይወት ጠፍቷል። በቂ ውድመት ደርሷል። አፈ ሙዞች ዝም ማለት አለባቸው” ሲሉ ማክሮን በኤክስ ገጻቸው ልጥፍ ላይ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ፣ ፑቲን “ሙሉ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መስማማት አለባቸው” ብለዋል ።
ዩናይትድ ኪንግደም እና አጋሮቿ ሩሲያ “ያለ ማወላወል” እንድትደራደር ለማስገደድ የሚረዱ “ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ካርዶች” አሉን ሲሉ አስጠንቅቋል።
- ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት ዙርያ ከፑቲን ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናገሩ15 መጋቢት 2025
- ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች12 መጋቢት 2025
- የንግድ ጦርነት፡ ትራምፕ በርካታ የዓለም ሀገራት ላይ ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስታወቁ13 መጋቢት 2025
ዋይት ሐውስ ትራምፕ እና ፑቲን ከሚያደርጉት የስልክ ውይይት አስቀድሞ የዩክሬን ሰላም “እንደ አሁኑ ቀርቦ አያውቅም” ሲል ተስፋውን ገልጿል።
የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ትናንት ለጋዜጠኞች፣ ትራምፕ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ ናቸው ብለዋል።
ንግግሮቹ ምን ሊሸፍኑ እንደሚችሉ ሲያብራሩም “በሩሲያና በዩክሬን ድንበር ላይ የሚገኝ የኃይል ማመንጫ አለ፤ በጉዳዩ ላይ ከዩክሬናውያን ጋር መወያየት ይኖርብናል፤ እናም ነገ ከፑቲን ጋር በሚያደርጉት የስልክ ውይይት ላይ ያነሱታል” ሲሉ ተናግረዋል።
የኃይል ማመንጫው በአውሮፓ ትልቁ የሆነው ዛፖሪዛዚሃ (Zaporizhzhia) የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ሊሆን ይችላል።
እአአ ከመጋቢት 2022 ጀምሮ በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን፣ በአካባቢው በሚደረገው ጦርነት የተነሳ የኒውክሌር አደጋ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል።
እሁድ ዕለት የተኩስ አቁም ድርድሩ ምን አይነት ነጥቦችን ታሳቢ እንደሚያደርግ የተጠየቁት ትራምፕ “ስለ መሬት እንነጋገራለን፤ ስለ ኃይል ማመንጫዎች እንነጋገራለን . . . አንዳንድ ሀብቶችን በመከፋፈል ላይ ንግግር ጀምረናል” ብለዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሁለቱ መሪዎቹ ስለሚወያዩበት ጉዳይ ተጠይቀው “ይህን በጭራሽ አናደርግም” በማለት ዝርዝር ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ፑቲን ቀደም ሲል የተኩስ አቁም ስምምነትን እንደሚደግፉ ተናግረው፣ ሠላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችንም ዘርዝረው ነበር።
ለውይይቱ እንቅፋት ሆኖ የነበረው አንዱ በዩክሬን ቁጥጥር ስር የነበረው የሩሲያ ኩርስክ ግዛት ሲሆን ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ የዩክሬን ጦር የተወሰኑ ግዛቶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሩሲያ ዳግም በቁጥጥሯ ስር ለማዋል ጥረት ያደረገች ሲሆን፣ ፑቲን ኩርስክን መልሰን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረናል ብለዋል።
በተጨማሪም የተኩስ አቁም ስምምነቱ በምሥራቅ ጦር ግንባር ላይ እንዴት ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚደረግበት በመጥቀስ በርካታ ነጥቦችን አንስተዋል፤ ከእነዚያም መካከል በግዛቶቹ የኔቶ ወታደሮችን እንዳይገቡ የሚለው ይገኝበታል።
ባለፈው ሳምንት ሊደረግ ስለታሰበው የሠላም ድርድር በዩክሬን እና በአሜሪካ ተወካዮች መካከል በሳዑዲ አረቢያ ውይይት ተደርጓል።
የሁለቱ አገራት ተወካዮች ለሰዓታት በዝግ ከተወያዩ በኋላ ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ሀሳብ ላይ መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ማክሰኞ ዕለት የተገናኙት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን እና አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ አገራቶቹ ለዩክሬን የሚያደርጉትን “የማያወላውል” ድጋፍ እንደሚቀጥሉ እና ከሩሲያ ስለ ሠላም “ግልጽ አቋም” እንደሚፈልጉ አሳስበዋል።