
18 መጋቢት 2025, 07:49 EAT
የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን እያካሄደ መሆኑን ሲገልጽ፣ የሃማስ ጤና ሚኒስቴር ደግሞ በጥቃቱ 330 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ገለፀ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል የሃማስ የሆኑ “የሽብር ዒላማዎች” ላይ ማነጣጠሩን ገልጿል።
በጥቃቱ የጋዛ ሰርጥ አገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት የሃማስ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን ማሃሙድ አቡ ዋፋ መገደላቸው ተነግሯል።
እአአ ጥር 19 በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላ ይህ ከፍተኛው የአየር ድብደባ ነው ተብሏል።
የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማራዘም በተደረገው ውይይት ከስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ቀርቷል።
በርካታ ፍልስጤማውያን በረመዳን ጾም ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት በተደረገው በዚህ የአየር ድብደባ በጋዛ ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱን የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል።
እንደ ዓይን ምስክሮቹ ገለፃ ከሆነ ከ20 በላይ እስራኤል ጦር አውሮፕላኖች ተመልክተዋል።
ከዚያም አውሮፕላኖቹ በጋዛ ከተማ፣ ራፋ፣ ካን ዩኒስ ዒላማዎቻቸው ላይ ቦንብ ማዝነብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ጥቃቱ እንዲፈፀም ማክሰኞ ጠዋት ማዘዛቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ አስታውቋል።
“ይህ የሆነው ሃማስ ታጋቾቻችንን ለመልቀቅ በተደጋጋሚ እምቢተኛ በመሆኑ እንዲሁም ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት መልእክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ከአደራዳሪዎች የቀረበለትን ምክረ ሀሳብ በሙሉ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው” ብሏል።
“እስራኤል ከአሁን በኋላ በሃማስ ላይ የምትወስደውን ወታደራዊ እርምጃ አጠናክራ ትቀጥላለች” ሲልም አክሏል።
የጥቃቱ እቅድ “በሳምንት መጨረሻ ላይ በእስራኤል መከላከያ ኃይል ቀርቦ በፖለቲካ አመራሩ ተቀባይነት አግኝቷል” ብሏል።
- የሁቲ አማፂያን ጥቃት እስካልቆመ ድረስ ኢራን ‘የከፋ እርምጃ’ እንደሚጠብቃት ትራምፕ አስጠነቀቁከ 9 ሰአት በፊት
- የሊባኖሱ ሔዝቦላህ የገንዘብ ምንጩ ከየት ነው? በአደገኛ የዕጽ ዝውውር ውስጥ እጁ አለበት?14 መጋቢት 2025
- ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር ከመወያየታቸው አስቀድሞ ‘በበርካታ ነጥቦች’ ላይ መስማማታቸውን ገለፁከ 9 ሰአት በፊት
ሃማስ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች ሲል በመወንጀል ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ ሰጥቷል። አክሎም እስራኤል በጋዛ የሚገኙትን የተቀሩትን እስራኤላውያን ታጋቾች “ላልታወቀ እጣ ፈንታ” አጋልጣቸዋለች ብሏል።
ሃማስ ይህን ይበል እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ እንዲገባ ከመጠየቅ ባለፈ ጦርነቱን እንደሚቀጥል ያለው ነገር የለም።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ከእስራኤል ጋር ምክክር አድርጓል።
የመጀመሪያው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እአአ መጋቢት 1 ማብቃቱን ተከትሎ ተደራዳሪዎች ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ለመፈለግ እየሞከሩ ነበር።
አሜሪካ የመጀመሪያውን ምዕራፍ እስከ ሚያዝያ ወር አጋማሽ ድረስ እንዲራዘም፣ እንዲሁም ሃማስ ያየዛቸውን ታጋቾች እንዲለቅ፣ እስራኤል ያሰረቻቸውን ፍልስጤማውያን እንድትፈታ ሐሳብ አቅርባ ነበር።
ነገር ግን ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉ የፍልስጤም ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስራኤል እና ሃማስ በሦስተኛ ወገን በኩል ባደረጉት ድርድር ላይ የአሜሪካው ተወካይ ዊትኮፍ ባስቀመጡት የስምምነት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ አለመግባባታቸውን ተናግረዋል።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ጦርነት የጀመረው እአአ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ሲሆን ሃማስ በደቡብ እስራኤል ከ1,200 በላይ ሰዎችን ሲገድል 251 ያህሉን ደግሞ አግቶ ወስዷል።
ይህ ጥቃት የእስራኤል ወታደራዊ እርምጃን የቀሰቀሰ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከ 48,520 የሚበልጡ ሰዎችን መሞታቸውን እና አብዛኞቹ ሲቪሎች እንደሆኑ በሃማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።
1.2 ሚሊዮን የሚሆነው በጋዛ ሰርጥ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል አብዛኛው በተደጋጋሚ ተፈናቅሏል።
በግምት 70 በመቶ የሚሆኑ ሕንፃዎች ፈራርሰዋል ወይም ወድመዋል፤ የጤና አጠባበቅ፣ የውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ ሥርዓቶች ወድመዋል።
እንዲሁም በጋዛ የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድሃኒት እና የመጠለያ እጥረት ተፈጥሯል።