
ከ 8 ሰአት በፊት
በትግራይ ክልል በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው ክፍፍል ተባብሶ በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ ያሳለፍነው ሳምንት በደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ወገን በሚደግፏቸው የትግራይ ኃይል አባላት በመታገዝ የአስተዳደር ተቋማትን መቆጣጠሩ ሲገለጽ ቆይቷል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ “ማኅተም ከነጠቀ አካል” ጋር እንዳይደራደር ጠይቀዋል።
በዚህ ውዝግብ መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት አንደኛው የህወሓት ክንፍ “የአገሪቱ ተቀናቃኝ ከሆኑ የውጭ ኃይሎች” ጋር ግንኙነት እና ትብብር አለው ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ከሷል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ውጥረት እንዳለ ሆኖ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚለው ስጋትም እንዳንዣበበ ይገኛል።
ቢቢሲ የሁለቱ ወገኖች ክፍፍል ወዴት ሊያመራ ይችላል? የከፌደራል መንግሥት በኩል ጣልቃ በመግባት የሚፈታ ችግር ነው? በሚሉና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ተንታኙን አደም ካሴ (ዶ/ር) አስተያየት ጠይቋል።
የፌደራል መንግሥት ሚና
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ጋር በክልሉ ስላለው ሁኔታ ለዲፕሎማቶች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት” አንደኛው የህወሓት ክንፍ የአገሪቱ ተቀናቃኝ ከሆኑ የውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እና ትብብር አለው” ብለዋል።
ሚኒስትሩ ይህንን እና ሌሎችንም ክሶች በህወሓት አንደኛው ወገን ላይ ባቀረቡበት ጊዜ ግንኙነቱ ከየትኛው የውጭ ኃይል ጋር እየተደረገ መሆኑን በስም አልጠቀሱም።
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት በተባባሰበት ባለፉት ወራት በድርጅቱ ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፂዮን የሚመራው የህወሓት ወገን ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እያደረገ መሆኑን ተጠቅሶ በተደጋጋሚ ሲከሰስ ቆይቷል።
አቶ ጌታቸውም አንዳንድ የህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እያደረጉ ነው ሲሉ መክሰሳቸው ይታወቃል።
በዶ/ር ደብረፂዮን የሚመራው ቡድን ግን እየቀረበበት ያለውን ይህንን ክስ በተደጋጋሚ እያስተባበለ ይገኛል።
በትግራይ ክልል የተከሰተውን ውጥረት በተመለከተ ማዕከላዊው መንግሥት በይፋ መግለጫ ሲሰጥ የባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን፣ መንግሥታቸው በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አመለክተው፤ አንደኛው የህወሓት ክንፍ “ጊዜያዊውን መንግሥት በግልጽ ኃይል ተጠቅሞ ለመናድ እየሞከረ ነው” ነው ብለዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ የፌደራል መንግሥት ስለሚኖረው ሚና የተጠየቁት የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር አደም “የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ያለውን የኃይል ሚዛን፣ የሕዝብ ድጋፍና ድርጅታዊ አቅም አይቶ የህወሓት የሚለውን ሰው ቢተካ የተሻለ ይመስለኛል። አሁን ባለው ሁኔታ ህወሓት ተመልሶ አቶ ጌታቸውን ይቀበላል የሚል እምነት የለኝም” ብለዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ “ወደ ድርድር ይገባሉ” ብለው እንደማያምኑም አክለዋል።
የፓርቲና የመንግሥት መሪ የተለያየ የሚሆንበት አሠራር በአገሪቱ ፖለቲካ ባህል “ያልተለመደ” መሆኑን እንደ አንድ ምክንያት የፖለቲካ ተንታኙ ይጠቅሳሉ።
“የፓርቲና የመንግሥት መሪ የተለያየ የነበረው በትግራይ ብቻ ነው። ይሄንን በኢትዮጵያ አለመድነውም። በሁለቱ መካከል የሚኖር የሐሳብ መለያየት፣ አለመስማማት፣ አለመዋደድ ወይም የግል ፀብም ከፍተኛ ችግር ያመጣል” ይላሉ።
“በህወሓት መሪና በመንግሥት መሪ መካከል ልዩነት ካለ አሁንም ችግር መምጣቱ አይቀርም። ምክንያቱም እንደ ፖለቲካ ባህል ያለመድነው ነው” ሲሉም አክለዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከ ምርጫ ድረስ የሚቆይ ከሆነ የፓርቲውና የመንግሥት አስተዳዳሪው አንድ ቢሆኑ የተሻለ እንደሚሆን ተንታኙ ይናገራሉ።
- አቶ ጌታቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ማህተም ከነጠቀ አካል” ጋር እንዳይደራደሩ ጠየቁ13 መጋቢት 2025
- “በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ11 መጋቢት 2025
- የኢትዮጵያ መንግሥት አንደኛው የህወሓት ክንፍ ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አለው ሲል ከሰሰ14 መጋቢት 2025
የፌደራል መንግሥቱ “ህወሓት የሚለውን ሰው ተቀብሎ ቢሾም ይሻላል” የሚሉት ዶ/ር አደም፣ ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ፌደራል መንግሥት ላይ ትግራይ ያላት ውክልና እና ከአማራ ክልል ጋር ያለውን የድንበር ግጭት [የግዛት ይገባኛል] በተመለከተም ስምምነት ላይ መድረስ የሚቻልበት መንገድ ቢፈጠር ሲሉ ይመክራሉ።
ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በህወሓት ተገድዶ ወይም እጁን ተጠምዝዞ ይሄን አደረገ” መባል ስለማይፈልጉ ከላይ የዘረዘሯቸው ምክረ ሐሳቦች እውን የመሆን ዕድላቸው ጠባብ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ይህንን ማድረግ እንደ ፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላሉ ሌሎች ተቀናቃኞች “ጥሩ መልዕክት” የማያስተላልፍና “የመሸነፍ” ስሜት የሚፈጥር ስለሆነ እንደማይሳካም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ህወሓትና የጊዜያዊ አስተዳደሩም ሊቀበሉት እንደማይችሉ ዶ/ር አደም አያይዘው ያነሳሉ።
በሁለቱም ወገኖች መካከል ያለው መወቃቀስ እንዳለ ሆኖ የፌደራል መንግሥቱም በጀት እየላከ መሠረታዊ እንቅስቃሴ ባለበት ሊቀጥል የሚችልበት ዕድል እንዳለ ይናገራሉ።
“ህወሓት በቆየ ቁጥር የኃይል እርምጃ ወደመውሰድ ነው የሚጠጋው። አሁን ጫና ውስጥ ናቸው። ሕዝቡም ፍርሃት ውስጥ ነው። ፍርሃቱን ለማቀዝቀዝና የራሳቸውን እውቅና ለማጠናከር በተለይ ከአማራ ክልል ጋር ያሉ ቦታዎችን [ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ክልል ስር እንዲጠቃለሉ የተደረጉ] በጉልበት ለመያዝ ሊሞክሩ ይችላሉ። የባሰ የዐቢይን መንግሥት የሚፈታተን ነው የሚሆነው።”
ሌላው ሊፈጠር ይችላል ብለው የፖለቲካ ተንታኙ የሚያስቀምጡት ሁኔታ በፌደራል መንግሥት በኩል የሚወሰድ እርምጃ ቢኖር ነው። የፌደራል መንግሥቱ በጀት ላለመላክ ወይም እቃ እንዳይገባ ለማገድ ቢወስን “የህወሓት ኃይል እንደ ወልቃይት [ምዕራብ ትግራይ] ያሉ ቦታዎችን በተወሰነ ደረጃ የመያዝ ዕድሉ ሰፊ ይመስለኛል” ይላሉ።
በትግራይ ክልል አስተዳደር ሥር የቆየው ምዕራብ ትግራይ በ2013 ዓ.ም. የጀመረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል እንዲጠቃለል ተደርጎ ወልቃይት ጠገዴ በሚል የክልሉ አንድ አካል ሆኖ ይገኛል።
በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ሆኖም በክልሉ ያሉት የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል አለመውጣታቸው እንዲሁም በክልሉ በሚፈጸሙ ጥሰቶችም ስማቸው ሲጠቀስ ይሰማል።
ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ክልል ስር ተጠቅለው የተቋቋሙ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እንደሚፈርሱ እና ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ ከዚህ ቀደም ቢነገርም፤ በተለይም ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች በከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ባደረጓቸው ሰልፎች አሰምተዋል።
ችግሩ ሳይፈታ በቆየ ቁጥር በሁሉም ወገኖች በኩል ምን ሊፈጠር ይችላል? የሚለው ፍርሃት ነገሮችን ሊያባብስ እንደሚችል ጠቅሰው “በቶሎ ካልተፈታ አደገኛ ይሆናል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ሌላው አማራጭ የፌደራል መንግሥት “የጉልበት አማራጭ” የሚከተልበት ነው። ይሄ ከሆነ “የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ላይ ብቻ የመጣ ሳይሆን፣ ህወሓት ከተሸነፈ ወደ እነሱም እንደሚመጣ በመፍራት ጦርነቱን በቀጥታም በተዘዋዋሪም መቀላቀሉ አይቀሬ ነው” ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ሳይገባም ነገሮች እየተንከባለሉ ቆይተው በህወሓትና በኤርትራ መንግሥት ወደ ጦርነት ሊገባ የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችልም አያይዘው ያነሳሉ።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ የሆኑት ሌተናንት ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል “በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” በማለት ባለፈው ሳምንት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ጦርነት የሚነሳ ከሆነ ከአገር ውስጥና ከውጭም የተለያዩ ኃይሎችን የሚያሳትፍ እንዲሁም ዳፋው ለቀጠናው የሚተርፍ እንደሚሆን የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ ቆይተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት በአዲጉዶም ከተማ እና በመቀለ አንዳንድ አካባቢዎች የትግራይ ኃይል አዛዦች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ በርካቶች መቁሰላቸው ተዘግቧል።
አቶ ጌታቸውም የመንግሥትን መዋቅር አፍርሰዋል በሚል አራት የሠራዊት አዛዦችን ማገዳቸው አይዘነጋም።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥት በክልሉ ጣልቃ መግባትን ጨምሮ “የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ” በቂ ምክንያት እንዳለው መናገሩም ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ግን የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባ በይፋ አለመጠየቃቸውን ተናግረዋል።
“በካቢኔ ደረጃ ተሰብስብን የፌደራል መንግሥቱ ወደ ትግራይ ይግባ ብለን አልጠየቅንም፤ መጠየቅም አያስፈልገንም” ብለዋል።
የትግራይ ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ በበኩሉ “በራሳችን አቅም ሊፈቱ የሚችሉ የውስጥ እና የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ሦስተኛ ወገን መጋበዝ አሳፋሪ ነው” በማለት በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።
“በዚህ ረገድ የትኛውም የኃይል እንቅስቃሴ ችግሩ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲሸጋገር እና እንዲባባስ ያደርጋል” ያለው መግለጫው “ሕዝቡም ደስተኛ እንደማይሆን” መግለጫው አክሎ ገልጿል።

ለምን ፖለቲካዊ መፍትሔ አልተገኘም?
አቶ ጌታቸው ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ በክልሉ “መፈንቅለ መንግሥት” እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረው፣ ይህንን ድርጊት የሚያከናውኑ አካላት የርዕሰ መስተዳደርነት ሥልጣንንን ለመቀበል ከፌደራል መንግሥት ጋር “ድርድር ለማድረግ” ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ይችላሉ የሚል ግምታቸውን ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው፤ “ምርጫ ቦርድ ‘አላውቅህም፤ ያደረከውን ጉባኤ አልቀበልም’ ብሎት ግን ምርጫ ቦርድ ‘ያልከኝን አልቀበልም፤ ስለዚህ ምርጫ አድርጌያለሁ’ ብሎ፤ የወረዳ ማኅተም፣ የቀበሌ ማኅተም አሁን የከተሞች ከንቲባዎችን ማኅተም እየለቀመ የሚውል ኃይል፤ ኮስተር ብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ‘ልደራደር ነው’ ብሎ ይመጣል” ሲሉ ተደምጠዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው መካረር ወደ ዓመት ገደማ እየተንከባለለ ሲመጣ ከፌደራል መንግሥት በኩል ምንም አለመባሉን በተመለከተ የፖለቲካ ተንታኞች ጥያቄ ያነሳሉ።
ዶ/ር አደም እንደሚሉት፣ በጉዳዩ ጣልቃ ባለመግባት “ህወሓትን ማሳጣት” ይፈለጋል።
“ድርድር ቢደረግ እንኳን፣ ክብሩና ውስጣዊ ጥንካሬው ከላላ ድርጅት ጋር ነው የሚሆነው። ይሄንን ቢያንስ ቢያንስ ዐቢይ ይጠላዋል ብዬ አላስብም” ሲሉ ያስረዳሉ።
“መጀመሪያ ላይ ህወሓት የሚፈልገውን ሰው አልሾምም ያለበት ምክንያት ግልጽ ነበር” በማለትም ያክላሉ።
አብዛኞቹ ነገሮች “ከሕግ ውጪ” እየተከሰቱ መሆኑ ጉዳዮን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለመመልከት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አያይዘው ያነሳሉ።
“ሕግ መከበር አለበት። ሥርዓቱ እስከሚገነባ ድረስ ግን ሕጉ በተወሰነ ደረጃ ወደጎን መባል ሊኖርበት ይገባል” የሚሉት ዶ/ር አደም የምርጫ ሕጉ መሻሻልን እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ።
ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ በመጠናቀቁ ለሦስት ወራት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መታገዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጮ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።
ህወሓት በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበ ጊዜ አንስቶ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ፣ መተዳደሪያ ደንቡን ማጽደቅ እና አመራሮችን መምረጥ ቢኖርበትም “ይህንን ባለማክበሩ” ዕግዱ እንደተጣለበት የካቲት ላይ ተገልጿል።
“አሁን ባለንበት ሁኔታ ስምምነት እያደረጉ ስምምነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ወደ ሕግ መቀየር ነው። ካልሆነ ግን እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ አካላትንም ለወደፊት ቅቡልናቸውን የሚያሳጣ ይሆናል” ሲሉ ዶ/ር አደም ያስረዳሉ።