
ከ 7 ሰአት በፊት
ከአፍሪካ አህጉር ለዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ አገራትን ለመለየት የሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ ከወራት በኋላ በዚህ ሳምንት ቀጥሎ ይከናወናል።
በዚህ ሳምንት የሚደረጉት ጨዋታዎች የአገራት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ይሆናሉ።
ምድባቸውን በበላይነት አሸንፈው የሚያጠናቅቁ ዘጠኝ አገራት ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ በሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ጥሩ ነጥብ ያሰባሰቡ አራት አገራት ደግሞ በጥሎ ማለፍ ቀሪዋን አንድ ቦታ ለማግኘት የሚፎካከሩ ይሆናል።
ካለፉት የማጣሪያ ጨዋታዎች በኋላ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ቱኒዝያ አሰልጣኝ ቀይረዋል።
ለመሆኑ በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ምን ይጠበቃል?
ነጥብ መጣል ዋጋ ያስከፍላል
ውጤት ለማግኘት ጫና ካላባቸው የአፍሪካ ኃያላን አገራት መካከል ናይጄሪያ ተጠቃሽ ናት።
በምድብ ሦስት አንድም ጨዋታ ሳታሸንፍ በአራት ነጥብ ሩዋንዳን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የቀድሞው የማሊ አሰልጣኝ ኤሪክ ቼሌ ጫና ውስጥ የገባውን ብሔራዊ ቡድን ለማሰልጠን ተስማምተዋል።
ኪጋሊ ላይ ሩዋንዳን ከገጠሙ በኋላ በሜዳቸው ደግሞ ዚምባብዌን ያስተናግዳሉ።
“እግር ኳስ በጫና የታጀበ ነው” ብለዋል አሰልጣኝ ኤሪክ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ሲገልጹ።
“ጊዜ የአሰልጣኞች ጠላት ነው ብዬ ባምንም በተጫዋቾቼ እተማመናለሁ” ብለዋል።
የቡድኑ አጥቂ ቪክተር ኦሲሜህ በበኩሉ የ2022ቱ የኳታር የዓለም ዋንጫ ላይ አለመሳተፋቸው እሱን እና የቡድብ ጓደኞቹን ወደ ዓለም ዋንጫ ለመጓዝ “ከፍተና መነሳሳት” አላቸው።
ማሊን ለስኬት ለማብቃት ያለሙት ሴንትፊት
ማሊም በአዲሱ አሰልጣኝ ቶም ሴንትፊት መሪነት ምድቡን በአራት ነጥብ በልጧቸው ከሚመራው ኮሞሮስ ጋር ይጫወታሉ።
“ጥሩ ቦታ ላይ ባንገኝም ጎበዝ ተጫዋቾች አሉኝ” ሲሉ ሴንትፌት ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግረዋል።
“ታሪክ ለመጻፍ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለዋል።
በምድቡ የምትገኘው ጋናም ከቻድ እና ከማዳጋስካር ትጫወታለች።
የቴራንጋ አንበሶቹ እና በአስደናቂ ጉዞ ላይ የሚገኙት ሱዳኖች
ሴኔጋል ፓፕ ቲያውን በአሰልጣኝነት ሾማለች።አሰልጣኙ በምክትልነት ሲያገለግሉት የነበሩትን አሊዩ ሲሴን ነው የተኩት።
ሴኔጋል ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች አንድም ጨዋታ ያልተሸነፈች ሲሆን የቀድሞው አጥቂ አል ሃጂ ዲኡፍ በቡድኑ አሰልጣኝ መተካካት መደነቁን አልሸሸገም።
“ኢለዩ እዚህ በነበረበት ወቅት፣ ፓፕም እዚህ ስለነበር ጥሩ ሽግግር ነው” ብሏል ዲዩፍ።
“የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን እንደ ቤተሰብ ነው።ጥሩ ስብስብም አለን። አብረን ሠርተን አብረን እንደሰታለን።”
ምድቡን በአስደናቂ ጉዞ ላይ የምትገኘው ሱዳን ስትመራ፤ ሴኔጋል በሁለት ነጥብ ርቃ ትገኛለች።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ሲገናኙ ሴኔጋል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወጡትን ኒኮላስ ጃክሰንን እና ኢሊማን ንዳዬን በጉዳት አታሰልፍም።
ጨዋታው በሊቢያዋ ቤንጋዚ ከተማ እንዲካሄድ መርሃ ግብር ወጥቶለታል።
የሱዳኑ አሰልጣኝ ክዋሲ አፒያህ የጀመሩትን ድንቅ ጉዞ ያስቀጥሉ ይሆን?

ኢትዮጵያ እና ምድቡን በበላይነት የምትመራው ግብጽ
ግብጽ ምድብ አንድን በአራት ነጥብ ልዩነት ስትመራ ሦስት ነጥብ ብቻ ያላት ኢትዮጵያ ከምድቡ ግርጌ በአንድ ከፍ ብላ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ አገሩ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ስታድርግ የነበረችውን የመጨረሻዎቹን ጨዋታዎች እንዲያርፍ ቢደረግም ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ጨዋታ እንደሚሰለፍ ይጠበቃል።
ግብጽ በቀጣይ ከሴራሊዮን ጋር ስትጫወት ኢትዮጵያ ደግሞ ጂቡቲን ትገጥማለች።
በምድቡ ካሉት እንደ ግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ ቢሳው እና ሴራሊዮን ካሉ አገራት እና እስካሁን ካሰባሰበችው ነጥቦች አንጻር ኢትዮጵያ ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ ከባድ ፈተና ይጠብቃታል።
የኮንጎ መቀጣት ጥያቄዎችን ፈጥሯል
በምድብ አምስት የምትገኘው ሞሮኮ ሁሉንም የማጣሪያ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለች ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ሆናለች።
ምድቡ ትንሽ ውስብስብ ይመስላል።
ኤርትራ ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ ራሷን ስታገል፤ ኮንጎ ብራዛቪል ደግሞ በአገሪቱ እግር ኳስ ማህበር ውስጥ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብቷል በሚል በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ተቋም ፊፋ እገዳ ተጥሎባታል።
ኮንጎ ከታንዛንያ እና ዛምቢያ ጋር ያላት ጨዋታ ተሰርዟል።
ፊፋ የጣለባት እገዳ ቢነሳ እንኳን እነዚህን ጨዋታዎች በድጋሚ ለማከናውን ባለው መርሃ ግብር የተነሳ ከባድ ሊሆን ይችላል።
በምድቡ ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ቡድን በምን መስፈርት በጥሎ ማለፍ ሊሳተፍ ይችላል የሚለውን ፊፋ እና ካፍ የሚወስኑት ይሆናል።
ኮንጎ ብራዛቪል ሙሉ ለሙሉ ከውድድሩ ውጭ ከሆነች ደግሞ እያንዳንዱ ጨዋታ ውስብስብ ይሆናል።