በደቡብ አፍሪካ ባለፈው ዓመት የጠፋች የስድስት ዓመት ህጻን

ከ 4 ሰአት በፊት

በደቡብ አፍሪካ ባለፈው ዓመት ደብዛዋ የጠፋ የስድስት ዓመት ህጻን፣ ‘አይኗ እና ቆዳዋ’ በባህል ሐኪም ይፈለግ እንደነበር በፍርድ ቤት በነበረ ምስክርነት ተገለጸ።

ጆሽሊን ስሚዝ የተሰኘችውን ህጻን ልጇን መታገት አቀነባብራለች በሚል እናቷ ኬሊ ስሚዝ እና ሌሎች ተባባሪዎቿ ክስ ቀርቦባቸዋል።

በችሎቱም ቀላ ያለችውን ህጻን ቆዳዋን የባህል ሐኪም ይፈልጉት ነበር የሚሉና ሌሎች ክሶች እየተደመጡ ይገኛሉ።

ኬሊ ስሚዝ፣ የወንድ ጓደኛዋ ጃኪን አፖሊስ እና ጓደኛቸው ስቴቨኖ ቫን ራይን በህገወጥ የሰው ዝውውር እና በእገታ የቀረበባቸውን ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ ተከራክረዋል።

ህጻኗ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ነበር ኬፕታውን አቅራቢያ ከሚገኝ መኖሪያ ቤቷ መጥፋቷ የተገለጸው። የህጻኗ ደብዛ መጥፋት በመላው አገሪቷ መነጋጋሪያ ቢሆንም እስካሁን ልትገኝ አልቻለችም።

መጀመሪያ ላይ እናቲቱ ሰማያዊ እና አረንጓዴማ ዓይን ያላትን ልጇን የወንድ ጓደኛዋ እንዲጠብቃት ከተወቻት በኋላ ጠፍታ እንደነበር ተናግራ ነበር።

በኋላ ላይ አቃብያነ ህግ ጠፍታለች በሚል በመዋሸት የስድስት ዓመቷን ታዳጊ “ሸጣታለች፣ ወይም ለውጣታለች” ሲሉ ከሰዋታል።

ችሎቱ ሶስተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል።

በችሎቱ የመጀመሪያ ሳምንት ፍርድ ቤቱ ስለ ህጻኗ አጠፋፍ ዝርዝር መረጃዎችን ሰምቷል።

እናቷ ህጻኗ መጥፋቷን ካወቀች ከስድስት ሰዓታት በኋላ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጓ ተሰምቷል።

በርካቶች ተደናግጠው ህጻኗን በሚፈልጉበት ወቅት እናቲቱ ተረጋግታ ከመታየት በተጨማሪ ከጠፋችው ልጇ ይልቅ የወንድ ጓደኛዋ የት ነው የሚለው አሳስቧት ነበር ተብሏል።

በሁለተኛው ሳምንት ችሎቱ አስደንጋጭ ዝርዝሮችን ሰምቷል።

አንድ የአካባቢ ፓስተር እንደተናገሩት ከአውሮፓውያኑ 2023 ጀምሮ የሶስት ልጆች እናት የሆነችው ኬሊ እያንዳንዱን ልጆች 1 ሺህ 100 ዶላር ለመሸጥ ትናገር ነበር ብለዋል።

በዚህን ያህል መሸጥ ካልተቻለም እስከ 275 ዶላር ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን መናገሯንም አስረድተዋል።

የህጻኗ መምህር በበኩላቸው በፍለጋው ወቅት ልጇ “በኮንቴይነር ውስጥ በመርከብ ወደ ምዕራብ አፍሪካ እያቀናች ነው” ስትል እናቲቱ መናገሯን በችሎቱ ወቅት ተናግረዋል።

የኬሊ ስሚዝ ጓደኛ እና ጎረቤት የሆኑት የአቃቤ ህግ ምስክር ሎረንቲያ ሎምባርድ አስደንጋጭ የሚባሉ መረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት በነበሩ አራት ተከታታይ ቀናት ምስክርነተቻውን የሰጡት ጎረቤት የጆሽሊን መጥፋት በደቡብ አፍሪካ ሳንጎማ ተብለው ከሚታወቁት የባህል ሐኪሞች ጋር ይገናኛል ብለዋል።.

ጓደኛዋ “አንድ የቂል ነገር አደረግኩኝ። ልጄን ለሳንጎማ ሸጥኳት” ስትል ገንዘብ ለማግኘት አማራጭ በማጣቷ ያደረገችው እንደሆነ ነግራኛለች ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

እናቲቱ ልጆቿን ለመሸጥ ማቀዷን ለሚያውቁ ዝምታቸውን ለመግዛት ገንዘብ ለመስጠት ቃል መግባቷን እኚሁ ጎረቤት በችሎቱ ላይ አስረድተዋል።

በኋላ ላይ ኬሊ ስሚዝ የልጆቿን የተወሰኑ ልብሶች በጥቁር ቦርሳ አስገብታ ይዛት ስትሄድ እንዳዩና የባህል ሐኪም ናቸው የተባሉ ሴት ጋር ሲገናኙ ጎረቤቲቱ አይቻለሁ ብለዋል።

እናት እና ልጅ ከዚህች ሴትዮ ጋር ሆነው በነጭ መኪና ተሳፍረው መሄዳቸውንም ፍርድ ቤቱ ከጎረቤቲቱ ሰምቷል።

“ህጻኗን የወሰደቻት ሴት ለዓይኗ እና ለቆዳዋ ትፈልጋት ነበር” ብለዋል ይህች ግለሰብ።

የባህል ሐኪም ለምን እንደዚህች አይነት ልጅ እንደሚፈልጉ ለፍርድ ቤቱ ግልጽ አልተደረገም።

የባህል ሐኪም ናቸው የተባሉ ግለሰብ ከኬሊ እና ከሌሎች ግለሰበች ጋር አብረው በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም መረጃ ባለመገኘቱ የግለሰቧ ክስ ውድቅ ተደርጓል።