አንጸባራቂ ማዕድን

ከ 5 ሰአት በፊት

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ “አገራችንን አንሸጥም” በማለት ዩክሬን ያላትን ሰፊ የማዕድን ክምችት ለአሜሪካ እንድትሰጥ ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።

ዩክሬን እጅግ በጣም ብዙ እና ወሳኝ ማዕድናት አሏት። አብዛኛዎቹ የሚገኙት ግን በሩሲያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ባሉ ቦታዎች ነው።

ትራምፕ፣ አሜሪካ በጦርነቱ ለዩክሬን በምትሰጠው ድጋፍ ምትክ ማዕድናቱ ሊሰጧት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ትራምፕ የካቲት 10 ለፎክስ ኒውስ ጋዜጠኛ ብሬት ባይነር እንደተናገሩት ከሆነ “500 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው እንደምንፈልግ (ለዩክሬን) ነግሬያለሁ።”

የዜለንስኪ ምላሽ ግን “ይህ ከባድ ውይይት አይደለም። አገራችንን መሸጥ አልችልም” የሚል ነበር።

በትራምፕ የቀረበው ሀሳብ ማዕድናቱ ለአሜሪካ ያላቸውን ጠቀሜታ አሳይቷል።

ማዕድናቱ ለምን ዓላማ ያገለግላሉ? ለአሜሪካስ ምን ይጠቅማሉ?

በማዕድን የበለጸገው የዶኔስክ እና ሉሃንስክ አካባቢ

ብርቅዬ ማዕድናት ምንድን ናቸው?

“ብርቅዬ ማዕድናት” በዘመናዊው ቴክኖሎጂ እና ኢንዱስትሪ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የ 17 ተመሳሳይ የኬሚካል ንጥረ ነገሮች የጋራ ቃል ነው።

እነዚህ ንጥረ ነገሮች ስማርት ስልኮችን፣ ኮምፒውተሮችን፣ የህክምና መሳሪያዎች እና ሌሎችንም ለማምረት ወሳኝ የሚባሉ ናቸው።

እነዚህም ስካንዲየም (Sc)፣ ይትሪየም (Y )፣ ላንታነም (La )፣ ሴሪየም (Ce)፣ ፕራሲዮድሚየም (Pr )፣ ኒዮዲሚየም (Nd )፣ ፕሮምቲየም (Pm )፣ ሳምሪየም (Sm)፣ ዩሮፒየም (Eu)፣ ጋዶሊኒየም (Gd)፣ ቴርቢየም (Tb)፣ ዳይስፕሮሲየም ( Dy )፣ ሆሊየም (Ho)፣ ኤርምየም ( Er ) ፣ ቱሊየም (Tm) እና ሉተቲየም (Lu ) ናቸው።

ማዕድኖቹ “ብርቅዬ” በመባል የሚታወቁት ንጹህ ሆነው ማግኘት በጣም ባለመለመዱ ነው። አንዳንዶቹ በመላው ዓለም ይገኛሉ።

ብርቅዬ ማዕድናቱ እንደ ቶሪየም እና ዩራኒየም ካሉ ራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ። በዚህ ምክንያትም ለመለየት ብዙ መርዛማ ኬሚካሎችን ይፈልጋል። ይህም የማውጣቱ ሂደት አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ እና ውድ ያደርገዋል።

ሊቲየም

ዩክሬን የትኞቹ ማዕድናት አሏት?

ዩክሬን በአውሮፓ ኅብረት “ወሳኝ ጥሬ እቃዎች” ተብለው ከተገለጹ 30 ንጥረ ነገሮች ውስጥ 21 ያህሉ ያሏት ሲሆን ይህም 5% የሚሆነው የዓለም ክምችት የሚይዝ ነው።

እነዚህ ንጥረ ነገሮች በአብዛኛዎቹ በደቡባዊ የዩክሬን ክሪስታል ሺልድ በዋነኛነትም በአዞቭ ባህር ስር ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ እነዚህ ግዛቶች በአሁኑ ጊዜ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ናቸው።

እንደ ፎርብስ ዩክሬን ገለጻ ከሆነ 70 በመቶ ያህሉ በዶኔስክ፣ በዲንፕሮፐትሮቭስኪ እና ሉሃንስክ ግዛቶች የሚገኙ ናቸው። አብዛኛዎቹ እነዚህ ቦታዎች ደግሞ በሩስያ ቁጥጥር ስር ናቸው።

ብርቅ ከሚባሉት በተጨማሪ ዩክሬን በጣም ወሳኝ የሚባሉትን እንደ ሊቲየም ያሉ ማዕድናትም አሏት።

እንደ የዩክሬን መንግሥት ከሆነ አገሪቱ ወደ 450 ሺህ ቶን የሚጠጋ የሊቲየም ክምችት አላት። ማውጣት ለመጀመር እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ወደ ተግባር አልተገባም።

ሩሲያ ቢያንስ ሁለት የሊቲየም ክምችቶችን ተቆጣጥራለች።

በኪሮቮራድ ክልል የሚገኘው የሊቲየም ማዕድን ክምችት በዩክሬን ቁጥጥር ስር ነው።

ዶናልድ ትራምፕ

ትራምፕ እነዚህን ማዕድናት ለምን ፈለጉ?

በአሜሪካ በኩል ብርቅዬ እና ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን ምርት ለመቆጣጠር ያለው ፍላጎት የሚመነጨው በአሁኑ ጊዜ የዓለምን አቅርቦት ከምትቆጣጠረው ከቻይና ጋር ባለው ውድድር ምክንያት ነው።

ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ቻይና ብርቅዬ ማዕድናትን በማውጣትና በማቀነባበር ግንባር ቀደም ሆናለች።

ከ60 እስከ 70 በመቶ የዓለምን ምርት እና 90 በመቶ የሚሆነውን የማቀነባበር አቅምን ትሸፍናለች።

ከብሔራዊ ደህንነት እና ከኢኮኖሚ አንፃር አሜሪካ በዚህ ጉዳይ በቻይና ላይ ያላት ጥገኝነት ለትራምፕ አስተዳደር አሳሳቢ ሊሆን ይችላል።

ከኤሌክትሪክ መኪናዎች እስከ ወታደራዊ መሳሪያዎች ያሉትን የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች ለመሥራት እነዚህ ቁሳቁሶች በጣም አስፈላጊ ናቸው።

ሻንጋይ ቻይና የሚገኘው የቴስላ ማምረቻ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ሁኔታው ሲታይ ተቃርኖ ይመስላል።

ትራምፕ የታዳሽ ኃይልን ሚደግፉ ፖሊሲዎችን በማስቀረት የነዳጅ ምርት እንዲስፋፋ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ወደ ታዳሽ ኃይል ለሚደረገው ሽግግር ቁልፍ የሆኑትን ወሳኝ ማዕድናት ከየትኛውም ቦታ ማግኘትን ይፈልጋሉ።

እንዲህ ያሉት ማዕድናት ለኤሌክትሮኒክስ፣ ለወታደራዊ እና ለመርከብ መሳሪያዎች ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ሠራሽ አስተውሎ የመረጃ ማዕከሎችን ለመገንባት ወሳኝ ናቸው።

ትራምፕ የሠው ሰራሽ አስተውሎት መሠረተ ልማትን በአገራቸው ለማስፋፋት ትልቅ ግፊት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆኑ በዋናነት እንደመዳብ፣ ሲሊከን፣ ፓላዲየም እና ብርቅዬ ማዕድናትን አቅርቦት ይጠይቃል።

ወሳኝ የሆኑ ማዕድናት አቅርቦት ማሽቆልቆል በመጀመሩ ምክንያት ለዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይል ዕድገት መቀዛቀዝ ዋና መንስኤ አንዱ ሆኗል።

ቻይናውያን ብርቅዬዎቹን ጨምሮ የወሳኝ ማዕድናት ላይ የበላይነት መያዟ በዩኤስ-ቻይና ጂኦፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ዋነኛው ምክንያት ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

ለአስርተ ዓመታት የማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን እና እውቀቶችን በማዳበሯ ምክንያት ቻይና መቶ በመቶ የተጣራ የተፈጥሮ ግራፋይት እና ዲስፕሮሲየም አቅርቦትን፣ 70 በመቶ ኮባልትን እና 60 በመቶ የሚሆነውን የተቀነባበሩ ሊቲየም እና ማንጋኒዝ ትቆጣጠራለች ሲል የዓለም አቀፉ ታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ አስታውቋል።

በተጨማሪም በዋናነት ብርቅዬ ንጥረ ነገሮችን በአፍሪካ፣ በእስያ እና በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ዋና ዋና ቦታዎች ላይ በባለቤትነት በመያዝ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲኖራት ሆኗል።

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የጦር አገልግሎት ኮሚቴ በባይደን አስተዳደር ወቅት “የቻይናን እያደገ የመጣውን የዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ለመመከት አሜሪካ የራሷን ወሳኝ እና ስትራቴጂካዊ ማዕድናት አቅርቦት ማግኘቷ አስፈላጊ ነው” ብሏል።

የትራምፕ አስተዳደር እንደ ዩክሬን እና ግሪንላንድ ያሉ ቦታዎችን ወደ አቅርቦቱ ሰንሰለት በማስገባት አዳዲስ ዘዴዎችን የሚጠቀም ይመስላል።