በርካታ ግዙፍ የአየር መንገዶች የምሽት በረራ ላይ የተጣለው ገደብ መነሳቱን ተከትሎ በረራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል
የምስሉ መግለጫ,በርካታ ግዙፍ የአየር መንገዶች የምሽት በረራ ላይ የተጣለው ገደብ መነሳቱን ተከትሎ በረራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል

ከ 4 ሰአት በፊት

በዩናይትድ ኪንግደም ግዙፉ የሆነው ሂትሮው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በረራ መጀመሩን እና ቅዳሜ ዕለት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገለፀ።

አየር ማረፊያው አቅራቢያ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የተቀሰቀሰን እሳት ተከትሎ በተከሰተው መብራት መቋረጥ አርብ ዕለት ሙሉ ቀን ተዘግቶ ውሏል።

በዚህ የተነሳ ወደ 200,000 መንገደኞች መጉላላታቸው የተገለፀ ሲሆን፣ አርብ ዕለት ሙሉ በሙሉ በረራ ተቋርጦ ውሏል።

ወደ አየር ማረፍያው ይመጡ የነበሩ አውሮፕላኖችም በአውሮፓ ወደሚገኙ ሌሎች አየር ማረፊያዎች እንዲሄዱ ተደርጓል።

የአየር ማረፊያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ቶማስ ዎልድቢ በረራቸው ለተስተጓጎለ መንገደኞች ይቅርታ ጠይቀው፣ መስተጓጉሉም “አየር ማረፍያችን ከሚችለው በላይ ግዙፍ ነበር” እና ራሱን “መቶ በመቶ” ከዚህ መከላከል አልቻለም ብለዋል።

የአገሪቱ ፖሊስ እሳቱ የተፈጠረው በሌላ አጠራጣሪ ነገር ነው ብሎ እንደማያምን አስታውቋል።

ፖሊስ በተጨማሪም ምርመራው በ “ኤሌክትሪክ ማከፋፈያ መሳሪያዎች” ላይ ያተኩራል ብሏል።

የብሪቲሽ አየር መንገድ ስምንቱ የረዥም ርቀት በረራዎቹ አርብ አመሻሽ ላይ ከሂትሮው ለቅቀው እንዲወጡ መደረጉን እና “ደንበኞቻቸው ይህንን በአስቸኳይ እንዲያውቁ እያደረገ” መሆኑን አስታውቋል።

መጨናነቅን ለማቃለል በምሽት በረራዎች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳም ለጊዜው መነሳቱን የትራንስፖርት ክፍሉ አስታውቋል።

ተሳፋሪዎች ለአዳዲስ የበረራ መረጃዎች አየር መንገዶቻቸውን እንዲያነጋግሩ ምክር ሰጥተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የብሪቲሽ ኤርዌይስ ፣ ኤር ካናዳ እና ዩናይትድ ኤርላየንስን ጨምሮ ወደ ሂትሮው የሚደረጉ እና ከሂትሮው የሚነሱ በረራዎቻቸውን እንደገና እንደሚጀምሩ በርካታ አየር መንገዶች አስታውቀዋል ።

የአየር ማረፊያው ቃል አቀባይ እንዳሉት የመጀመሪያዎቹ በረራዎች “ወደ አውሮፓ ሌሎች አየር ማረፊያዎች እንዲሄዱ የተደረጉ መንገደኞች ወደ ሂትሮው መመለስ . . . ” ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል።

ሚስተር ዎልድቢ “ይህ በጣም ከባድ የሆነ ክስተት መሆኑን ላሳስብ እወዳለሁ። ትንሽ እሳት አይደለም።

“መካከለኛ መጠን ካለው ከተማ ጋር እኩል የሆነ ኃይል አጥተናል እናም የመጠባበቂያ ስርዓታችን በሚፈለገው መጠን እየሰራ የነበረ ቢሆንም አየር ማረፊያውን ሙሉ በሙሉ ለማንቀሳቀስ አቅም አልነበረውም።”

በሂትሮው የኃይል ስርዓት ውስጥ ክፍተት ነበር ብለው ያምኑ አንደሆን ተጠይቀው “ይህን ማለት ይችላል፤ ግን እንዲህ ግዙፍ ለሆነ አደጋ የሚሆን መጠባበቅያ አልነበረም፤ ራሳችንንን መቶ በመቶ መከላከል አልቻልንም፤ ይህ ከእርሱ አንዱ ነው።

“ምንም እንኳ ምንም ዓይነት ሰው ጉዳት ባይደርስበትም፤ ለአየር መንገዳችን ከሚችለው በላይ ግዙፍ ነው።ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ዎልድቢ በመቀጠልም አየር ማረፊያው ቅዳሜ “መቶ በመቶ ወደ ስራ” ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ሂትሮው የዩኬ ትልቁ የአቪዬሽን ማዕከል ሲሆን በየቀኑ ወደ 1,300 የሚያህሉ የአውሮፕላን በረራዎችን ያስተናግዳል።

ባለፈው ዓመት ብቻ 83.9 ሚሊዮን መንገደኞች በተርሚናሎቹ ማስተናገዱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ሃይዲ አሌክሳንደር የየአየር ማረፍያው ኃላፊዎች ” የአደጋ ጊዜ እቅዳቸውን በፍጥነት መተግበር ጀምረዋል እና ከድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሰጭዎቻችን እና ከአየር መንገዱ ኦፕሬተሮች ጋር በቅርበት ሠርተዋል፤ ምትክ የኃይል አቅርቦቶች አሏቸው፤ በናፍታ የሚሰሩ ጄኔሬተሮች ያሏቸው ቢሆንም በዚህ አጋጣሚ አንዳቸውም ሊሰሩ አልቻሉም።

ምክንያቱም ይህ የመጠባበቂያ አቅርቦት በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ያሉትን ወሳኝ ቁልፍ ስርዓቶች ለመጠበቅ እንጂ ለአውሮፕላን ማረፊያው በሙሉ ኃይል ለመስጠት አልተደራጀም” ብለዋል።

አሌክሳንደር አክለውም ከኢነርጂ ሚኒስትር፣ ከአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር እና ከአየር ማረፍያው ኃላፊዎች ጋር “ወደ አየር ማረፊያው ከተዘረጋው ሥርዓት ልንማራቸው የሚገቡን ነገሮችን መኖራቸውን ለማረጋገጥ” በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢነርጂ ተቆጣጣሪው ኦፍጌም (Ofgem) ቀደም ሲል “የዚህን ክስተት መንስዔ ለመረዳት እና ምን ትምህርት መውሰድ እንደሚቻል” ግምገማ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

አደጋው በተፈጠረበት ወቅት ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እየመጡ የነበሩ 120 አውሮፕላኖች አቅጣጫውን ለመቀየር ወይም ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል።

የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት በስፍራው የተጠራው በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ሐሙስ ከሌሊቱ አምስት ተኩል ገደማ ሲሆን ከጣቢያው ከፍተኛ የእሳት ነበልባል ሲቀጣጠል እንዲሁም ጭስ ሲወጣ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተጋሩ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።

እሳቱን ለመቆጣጠር 10 የእሳት አደጋ መከላከያ መኪኖች እና ወደ 70 የሚጠጉ የእሳት አደጋ ሠራተኞች መሰማራታቸው ተግለጿል።

በምዕራብ ለንደን ሃይስ የሚገኘው ማከፋፈያ ጣቢያ የተቀሰቀው የእሳት ቃጠሎ ከ65,000 በላይ ቤቶች መብራት አልባ አድርጓል።

በተጨማሪም 150 ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ ተደርገዋል።

እሳቱ ባስከተለው የመብራት መቋረጥ ምክንያት ከ16 ሺህ 300 በላይ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ማጣታቸውን የስኮትላንድ እና የደቡባዊ ቀጠና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ድርጅት በኤክስ ገጹ አስታውቋል።