ራድሄ ማ

23 መጋቢት 2025, 07:36 EAT

ተሻሽሏል 23 መጋቢት 2025, 07:36 EAT

ተዓምራትን እንደምትሠራ ትናገራለች። አማኞችዋም አምላክ እንደሆነች ያምናሉ።

ራድሄ ማ በሕንድ አወዛጋቢ በሆነው እና ቁጥራቸው ከጨመረው “አማልክት” መሆናቸውን ከሚገልጹ ጥቂት ሴቶች አንዷ ናት።

ብዙ ተከታዮች አሏት። ቢቢሲ ይህን የእምነት እና የፍርሀት ዓለም ለመግለጥ ፈቃድ አግኝቷል።

የሉዊ ቩተን እና የጉቺ ቦርሳዎችን የያዙ ሴቶች፤ በወርቅ እና በአልማዝ ባጌጡ ባሕላዊ አልባሳት ከራዴ ማ ጋር ለማሳለፍ እኩለ ሌሊት ላይ መሰባሰብ ጀመሩ።

ቀላል ልብሶችን ወይም ረዥም ስብከት አትወድም።

ይህ ደግሞ ከብዙ ‘ቅዱሳን’ የሚለያት ሲሆን ራሷን “ተዓምረኛዋ እናት” ብላ ትጠራለች።

“ተአምራቶች ዋጋ ይሰጣቸዋል። ካልሆነ ግን ማንም ሰው ገንዘብ አይሰጥም።ተዓምራት በእነርሱ ላይ ይከናወናል።ሥራቸው ሲጠናቀቅ ገንዘብ ይለግሳሉ” ትላለች ራድሄ ማ።

ልጅ የሌላቸውን ጥንዶችን በሕፃናት እንዴት እንደባረከቻቸው፤ ሴት ልጆችን ብቻ የሚወልዱ ባለትዳሮች ወንድ ልጅ እንዲወልዱ እንደረዳቻቸው፤ የታመሙትን እንደተፈወሱ፣ እየከሰሩ ያሉ ንግዶች እንዴት እንዳተረፉ በስፋት ይነገራል።

የመለኮታዊ ኃይሎች አሉኝ የምትለው ራድሄ ማ ብቻ አይደለችም። ሕንድ ‘አምላክ’ የሚባሉ ብዙ ሰዎች አሏት። ቁጥራቸው በትክክል ባይታወቅም በየዓመቱ እየበዙ የመጡ ይመስላል።

አንዳንዶቹ በሙስና አልፎ ተርፎም በጾታዊ ጥቃት ተከስሰዋል።

ራድሄ ማ ጥንቆላ ሠርታለች እና በሕንድ ሕገ-ወጥ የሆነውን የጥሎሽ ክፍያዎች እንዲፈጸሙ ረድታለች የሚል ውንጀላ ገጥሟታል።

ጉዳዩን ፖሊስ ከመረመረ በኋላ ክሱ ውድቅ ተደርጓል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን እነዚህን አማልክቶች ለማየት ይጎርፋሉ። ባለፈው ዓመት በአንድ ስፍራ በተፈጠረ መረጋገጥ ከ120 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ራድሄ ማ

የሕንድ ፀረ-አጉል እምነት ድርጅት ኃላፊ ፕሮፌሰር ሽያም ማናቭ “አብዛኞቹ ሕንዶች ያደጉት በአምልኮ፣ በአርምሞ ወይም በጸሎት መለኮታዊ ኃይል ሊገኝ እንደሚችል በሚያምኑ ቤተሰቦች ውስጥ ነው።

እነሱን የሚያገኙ ደግሞ ተዓምራትን ማድረግ ይችላሉ ብለው ያምናሉ” ብለዋል።

“እንዲህ ያለው ሰው አምላክን የሚመስል ወይም አማላክት እንደሆነ ይቆጠራል።”

ምንም እንኳን እንደዚህ ባሉ ሃሳቦች የሚጠመዱት ድሃዎች፣ ያልተማሩ እና ክፉ ናቸው የሚል ሰፊ ግንዛቤ ቢኖርም ራድሄ ማ ከሃብታም ቤተሰቦች በመጡ እና በከፍተኛ ደረጃ በተማሩ ሰዎች ዘንድ ትከበራለች።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ የሆነው እና በትምህርት ዙሪያ የሚያማክር ተቋም ያለው ፑሽፒንደር ብሃቲያ፣ ራድሄ ማ ዘንድ ለመግባት ሠልፍ ይዟል።

“ሥጋ የለበሰ አማልክት” እከተላለሁ ብሎ አስቦ እንደማያውቅ ይናጋል።

“‘በእርግጥ አምላክ በሰው መልክ ይመጣልን? እውነት ይሆን? ሕይወትህን ሊለውጡ በሚችሉ መንገዶች ትባርክሃለች? እነዚህ ተዓምራት የሚባሉት እንዴት ይሳካሉ?’ የሚሉ ጥያቄዎች መጀመሪያ ላይ ነበሩኝ” ይላል።

ባቲያ በቤተሰቡ ውስጥ ከደረሰ አሳዛኝ አደጋ በኋላ ከራዴ ማ ጋር ተገናኘ።

ምንም እንኳን አንዳንዶች በወቅቱ ለጥቃት የተጋለጠ ነበር ቢሉም እሱ ግን በትክክል እንደምታስብለት ተሰምቶታል።

“መጀመርያ ሳያት ባላት ጸጋ ማርካኝ ነበር። ሰዋዊ የሆነ ማንነቷን ስትመለከቱ ወዲያውኑ ከእርሷ ጋር ትስስር ትፈጥራላችሁ” ብሏል።

ፑሽፒንደር ባቲያ

በወርቃማ እና በቀይ ክፍል ውስጥ ያሉት ታዳሚዎች

ራዴህ ማ የምትመራው ጉባኤ በጣም ተፈላጊ ነው። አንድ ምሽት ደልሂ ውስጥ በሚገኝ የግል መኖርያ ቤት አንድ ጉባኤ አዘጋጅታ ነበር።

በመቶዎች ከሚቆጠሩት ምዕመናን መካከል ለጉባኤው ሲሉ በተለየ በረራ የመጡ የታዋቂ ነጋዴዎች እና የፖሊስ መኮንኖች ቤተሰቦች ይገኙባቸዋል።

ጋዜጠኛ ሆኖ ለመታዘብም መጀመሪያ ምርቃትዋን ማግኘት ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ ረዥም ወረፋ መጠበቅ ግድ ነው። ከዚያም እንዴት መጸለይ እንደሚያስፈልግ እና በትክክል ካልተፈጸመ በቤተሰብ የሚደርስ ጉዳት እንዳለ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።

በዚያ የራድሄ ማ ተወዳጅ ቀለሞች ቀይ እና ወርቃማ ክፍል ውስጥ በዓይኖቿ ሁሉንም ነገር ታዝዛለች።

አንድ ጊዜ ፈገግ፣ ሌላ ጊዜ ቆጣ ስትል ይታያል። ቁጣዋ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ ደቀ መዝሙሯ የተጋባ ይመስላል።

ሴትዮዋ ወለሉ ላይ መንከባለል ስትጀምር ክፍሉ ፀጥ አለ ።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የራድሄ ማ ተከታዮች ይቅርታ እንድታደርግ ከለመኗት በኋላ፣ ታዋቂ የሆነ የቦሊውድ ዘፈን ተከፍቶ መደነስ ጀመረች።

ሁሉም ነገር ወደነበረበት መመለሱን የሚያሳይ ምልክት መሆኑ ነው። ምዕመናኑ እንደገና በወረፋ መንቀሳቀስ ጀመሩ።

የራድሃ ማ ክፍል

ከ’አማልክት’ እንደ አንዱ መሆን

የራድሃ ማ ታሪክ የሚጀምረው ከሰሜናዊ ሕንድ ፑንጃብ ግዛት ነው።

ስሟ ሱክዊንደር ካውር ይባል ነበር። መካከለኛ ደረጃ ካለው ቤተሰብ የተገኘች ናት።

በአንድ መምህር ትምህርት ከተሰጣት በኋላ መለኮታዊ ኃይል እንዳገኘች ትናገራለች።

“ልጆች ፓይለት ወይም ዶክተር መሆን እንደሚፈልጉት ሁሉ ደራድሄ ማ-ጂ ሁሌም ‘እኔ ማን ነኝ?’ ትል ነበር። አባታችን ወደ አንድ ታዋቂ መምህር ወሰዳት። እሱም በሰው አምሳል ያለች አምላክ መሆኗን አወጀ” ስትል የራዴ ማ እህት ራጂንደር ካውር ትናገራለች።

እህቷ በራዴ ማ ስም ባለ አንድ ክፍል ቤተመቅደስን የምታስተዳድር ሲሆን የራዴ ማ ባል፣ ሞሃን ሲንግ ባህር ማዶ ሠርቶ ባጠራቀመው ገንዘብ የተገነባ ነው።

“አባ” ብለን እንጠራዋለን። እሷ እናታችን ናት። ስለዚህ እሱ አባት ነው ” ትላለች ካውር።

20 ዓመት ሲሆናት እና ባለቤቷ ባህር ማዶ በነበረበት ወቅት፤ ራዴ ማ ሁለቱን ልጆቿን ለእህቷ ትታ በምዕመኖቿ ቤት መኖር ጀመረች። አብዛኞቹ ምዕመኖቿ ነጋዴዎች ነበሩ።

ከከተማ ከተማ ስትዘዋወር ቆይታ የሕንድ የንግድ ዋና ከተማ ሙምባይ ስትደርስ ከአስር ዓመት በላይ በአንድ ነጋዴ ቤት አረፈች። በመጨረሻም ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ተመልሳለች።

ለዓመታት ያስተናገዷት እና በዚህ ምክንያት በልጽገናል የሚሉት ምዕመናን አክራሪ ተከታዮቿ ናቸው።

ራዴ ማ አሁን የምትኖረው በሁለት ልጆቿ በተገነቡት ትልቅ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው። ልጆቿ የስኬታማ ነጋዴዎችን ልጆች አግብተዋል። ብዙ ጊዜ ግን እዛ አትኖርም።

የራድሃ ማ መኖሪያ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

“በመጀመሪያ ከእኛ ጋር እየኖረች አልነበረም። በእሷ ሻራን [መጠለያ] ከክሪፓ [ፀጋዋ] ጋር በመኖራችን ተባርከናል” ስትል ጉባኤውን የምታስተናግደው የልጇ ሚስት የሆነችው ሜጋ ሲንግ ተናግራለች።

“በሁለተኛ ደረጃ እሷ እኛን እንደ ቤተሰብ ሳይሆን እንደ ምዕመን ነው የምታየን።”

ለራድሄ ማ የሚሰጡ ስጦታ የሚተዳደሩት በቤተሰቧ እና በምዕመናኑ ነው።

“የምታገኘው ስጦታ የሚተዳደረው በምዕመናኗ ነው። እነሱም ችግረኛ ሰዎችን የሚጠይቁትን በመለየት የገንዘብ ወይም የዓይነት ስጦታዎቹን ያከፋፍላሉ።

ራዴ ማ ከእነዚህ ፍቅረ ቁሳቁሶች በጣም ትበልጣለች” ትላለች ሜጋ ሲንግ።

ሴትየዋ ግን በሚያማምሩ ቀሚሶች እና ጌጣጌጦች ትደሰታለች።

“እንዳገባች ሴት ጥሩ ቀሚሶችን እና ቀይ ሊፕስቲክን እወዳለሁ። ሜካፕን ግን አልወድም” ትላለች ራድሄ ማ። ሆኖም ግን በጣም ብዙ ሜካፕ ትጠቀማለች።

“ሁሌም ለሚስታችሁ የሚስማማ ልብስ ትገዛላችሁ።ሕያዋን አምላክስ ምን ያንሳታል? አንድ በማግኘታችን ተባርከናል። እሷን በማገልገላችን ተባርከናል” ስትል ሜጋ ሲንግ ተናግራለች።

እ.ኤ.አ. በ2020 ራድሄ ማ የተወዳዳሪዎችን ቤት ለመባረክ በቢግ ብራዘር የሕንድ የቲቪ ትርዒት ላይ ታየች፣ መለያዋ የሆነውን ቀይ ቀሚስ ለብሳ እና ወርቃማ ባለሦስት ጫፍ ዘንግ ይዛለች።

አሁን ያላት ትክክለኛ ምስል እና ምዕመናኑ ከሚያሳዩት ፎቶግራፎች ጋር በእጅጉ ይቃረናል።

ሳንቶሽ ኩማሪ የራዴህ ማን ምስሎች በቤቷ ውስጥ በሚገኝ ቤተ መቅደስ ውስጥ አስቀምጣለች።

የእምነቷ ምንጭ ባሏ በልብ ሕመም ምክንያት ሆስፒታል በነበረበት ወቅት፣ ከበሽታው ማገገሙን በመናገር፣ በወቅቱ ካገኘችው በረከት የሚመነጭ መሆኑን ትናገራለች።

“ከአፍዋ ደም ወጣ። እርሱን ከንፈሬን ቀብታኝ ‘ምንም መጥፎ ነገር አይፈጠርም ባልሽ ይድናል’ አለችኝ።”

በርካታ ተከታዮቿ የራድሄ ማ ምላስ በደም እንደሚለወስ፣ ይህም ደግሞ የመለኮታዊ ኃይል ውጤት ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ኩማሪ 500 ከሚሆኑ እና ባሎቻቸው በመሞቱ ምክንያት በወር ከ11 እስከ 22 ዶላር ከሚሰጣቸው መካከል ናቸው።

ሌሎች ከእጇ ጡረታቸውን የሚቀበሉ ሰዎችም የግለሰቧን የተዓምራት ታሪኮች በጥንቃቄ ይናገራሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ቃላታቸው በጥንቃቄ የተሞላ ነው።

የራድሃ ማ ፎቶ

ፍርሃቶች

“ስለ እሷ ምንም ማለት አንችልም፤ ምክንያቱም እኛን ሊጎዳ ይችላል።መብራት ካላበራሁላት ጉዳት ይደርስብኛል። እታመማለሁ” ስትል ሰርጄት ካውር ገልጻለች።

ያላትን ኃይል በማመንም ካውር በየቀኑ ሳታስተጓጉል ለራዴህ መብራት ታበራለች።

ፕሮፌሰር ማናቭ ግን ይህንን አንድ ደቀ መዝሙር የአምላኩን በረከት እንዳያጣ በመፍራት የሚደረገው ነው ይላሉ።

“አንዳንድ ትንበያዎች ዕውን ስለሚሆኑ አማልክቷ እንዳደረገችው ይቆጠራል። ስህተት ሲፈጠር ግን ተወቃሽ አትሆንም። ፀሎት ባለማድረግ፣ እምነት በማጣት ወይም በዕድለ ቢስነት ራስን ተወቃሽ ማድርግ ይመረጣል” ሲሉ ተናግረዋል።

በራዴ ማ ዝግጅቶች ላይ ከተገኙት ጥቂት ሰዎች ብቻ ተዓምራትን የማድረግ ኃይሏን እንደማያምኑ በግልጽ ይናገራሉ።

አንድ ግለሰብ እነዚህን ተዓምሮች “ምናባዊ ታሪኮች” ብሎ ጠርቷቸዋል።

ሌላ ግለሰብ ደግሞ ሜካፑን እና ውድ አልባሳቱን ጠቁሞ መለኮታዊ አለመሆኑን እና ምንም ዓይነት ተዓምር አይቶ እንደማያውቅ ተናግሯል።

እንዲህም እያሉ ግን ጉባኤዋ ላይ ተገኝተዋል። “አዝናኝ” ሆና እንዳገኟት እና የቲቪ ሾው ላይ ካዩዋት በኋላ በአካል ለማየት ጓጉተው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ምርመራ በሚደረግበት ወቅት የራድሄ ማ የቀድሞ ተከታዮችን ትንቢቷ እንዳልሠራ እና እንዲያውም ጉዳት አድርሰዋል ቢሉም ማንነታቸው እንዲታወቅ አልፈለጉም።

ይህ ግን ስለ ምዕመኖቿ፣ በአምላክነቷ ላይ ስላላቸው እምነት እና ስለተገዥነታቸው ለማውቅ ጉጉት ይጨምራል።

የራድሃ ማ ልጆች እና ሚስቶቻቸው

ምን ዓይነት እምነት?

አንድ ቀን አመሻሽ ላይ ራዴ ማ መሬት ላይ የተቀመጡትን ተከታዮቿን የእንስሳት ድምጽ እንዲያወጡ ስትጠይቃቸው ያለምንም ማቅማማት አደረጉት።

እንደ ውሾች እና ጦጣዎች እንዲንቀሳቀሱ ጠየቀቻቸው፤ የተባሉትን ፈጸሙ።

የራዴህ ምራት ሜጋ ሲንግ በክፍሉ ውስጥ ስለነበረች ምን እየተከናወነ እንደሆነ ጥያቄ ቀረበላት።

ምንም የተገረመች አትመስልም።

ራዴሄ በክፍሏ ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ እንደኖረች በመግለጽ ጀመረች።

“ያላት ብቸኛ የመዝናኛ ምንጭ ይህ ብቻ ነው” ብላ ቀጠለች። “ትንሽ ቀልድ ለመጣል እንሞክራለን ወይም እንደዚህ ሁሉ ድርጊቶች በማድረግ እሷን ለማሳቅ እንሞክራለን።”

ምዕመናን ሙሉ በሙሉ እና ያለ ምንም ገደብ ማመን እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።

ራድሄ ማ ተከታዮቿን ምን ትጠይቃለች ተብሎ የተጠየቀው ፑሽፒንደር ሲንግ፣” ‘ወደ እኔ ስትመጡ ክፍት ልብ እና እምነት ይዛችሁ ኑ’ ከማለት በቀር ምንም አትልም።

ሰዎች በዚያ አስተሳሰብ ሲመጡ ተዓምራትን ስታደርግ ተመልክቻለሁ። እሷን ለመፈተን ወደዚያ ከሄድክ ግን ከዚያ በኋላ የዚያ የአማኞች ቡድን አባል እንደማትሆን አስባለሁ” ሲል መለሷል።

ተከታዮቿ የሚናገሩት በእርሷ ላይ ያላቸው እምነት ሙሉ በሙሉ እጅ መስጠትን እንደሚጠይቅ ነው።

እንደ ፕሮፌሰር ማናቭ ገለጻ ይህ ፍጹም ያለመጠራጠር ታማኝነት “አጉል እምነትንም” የሚያካትት ነው።

“ጥበብን ማግኘት የሚቻለው በአንተ መምህር ላይ የማይናወጥ እምነትን በማሳደር ብቻ እንደሆነ ተነግሮናል። እሱን የሚጠራጠር ወይም ሊፈትነው የሚሞክር ማንም ሰው እምነቱን እና በረከቱን ያጣል።”

ራድሄ ማ ተከታዮቿ አብረዋት እንደሚቆዩ ታምናለች።

አጭበርባሪ ስለሚሏት ሰዎች ምንም እንደማትጨነቅ ትናገራለች።

“ግድ የለኝም” ትላለች በፈገግታ።

ምክንያቱም ፈጣሪ ከላይ ሆኖ ይጠብቀኛል።