የጠፈር ተመራማሪዎች በህዋ ላይ

23 መጋቢት 2025, 07:36 EAT

በህዋ ላይ ሆነን ምድራችንን በርቀት ማየት የብዙዎች ህልም ነው።

ሆኖም የስበት ኃይል (ግራቪቲ) በሌለበት ህዋ ውስጥ መቆየት እንደሚታሰበው አይደለም።

መሬት ያላት የስበት ኃይል (ግራቪቲ) የሰው ልጅ በተለመደው ዝግመተ ለውጥ እንዲሄድ የሚያስችለው ነው። እናም የህዋ የስበት ኃይል አልባነት በሰው ልጅ ላይ ከሚፈጥረው ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ ለማገገም ዓመታት ሊወስድ ይችላል።

የጠፈር ተመራማሪዎቹ ሱኒ ዊልያምስ እና ቡች ዊልሞል ከዘጠኝ ወራት የህዋ ቆይታቸው በኋላ ተመልሰዋል።

ለስምንት ቀናት ብቻ ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ተቋም (አይኤስኤስ) የሄዱት የጠፈር ተመራማሪዎች ለዘጠኝ ወራት ወደ መሬት መመለስ ሳይችሉ ቆይተዋል።

አሁን ከዚያ ቆይታቸው ማገገም ይጀምራሉ።

“ህዋ እስካሁን ድረስ የሰው ልጅ ካጋጠመው እጅጉኑ የከፋ ከባቢ ነው። እናም ይህንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሰው ልጅ ባለበት ዝግመተ ለውጥ ገና አልደረሰበትም” የሚሉት በሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርስቲ የሰው ልጅ አካልን የሚያጠናው፣ ፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰር ዳሚያን ባይሌይ ይናገራሉ።

ወደ ህዋ መግባት የሰውን ልጅ አካል የሚቀይር ሲሆን ይህም መጀመሪያ ላይ ደስ የሚል ስሜትን ይፈጥራል።

“የመዝናናት ስሜት ይሰማል” ሲል በአውሮፓውያኑ 2015 ወደ ዓለም አቀፉ የህዋ ተቋም የሄደው የጠፈር ተመራማሪው ቲም ፒክ የሚገልጸው።

“ልብህ ቀለል ይላል። እንዲሁም ጡንቻዎችን እና አጥንቶችህም እንዲሁ ቀለል ያለ ስሜት ይሰማቸዋል።

” የስበት ኃይል ዜሮ በሆነበት በዚህ አስደናቂ ህዋ ላይ መንሳፈፍ ትጀምራለህ”

ለሳምንታት አልጋ ላይ ሆናችሁ አለመነሳትን እስቲ አስቡት ይላል።

የጡንቻ ጥንካሬ

የሰው ልጅ ጡንቻ ላይ ስንመጣ ካልተጠቀምንበት መላላት፣ መዛል ወይም መታጣት ያጋጥማል።

ቀላል ተግባራት ለምሳሌ መቆም፣ ሰውነታችን ቀጥ እንዲል ጡንቻዎችን እንጠቀማለን።

እናም እንዲህ አይነት ጡንቻን የሚጠቀሙ ተግባራት በዓለም አቀፉ ህዋ ተቋም ቀጥ ይላሉ።

ስበት ወይም ክብደት በሌለበት ስፍራ የጡንቻ ጥንካሬ የተለየ ትርጉም ይኖረዋል።

የጠፈር ተመራማሪዎች መሬት ላይ በሚወርዱበት ወቅት

የተፋጠነ እርጅና

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ከመሬት ስበት ጋር በተያያዘ ደም የሚረጩት ልብ አና የደም ስሮች ስበት በሌለበት ሁኔታ ይህንን ተግባር ማከናወን ስለሚቀንሱ ቀለል ያለ ተግባር ይኖራቸዋል።

በዚህም ምክንያት መዳከም ይጀምራሉ።

አጥንቶቻችንም እየተዳከሙና እየሳሱ ይሄዳሉ።

አሮጌውን አጥንት በሚተኩት ህዋሳት እና አዲስ በሚፈጥሩት መካከል ሚዛን (መመጣጠን) ሊኖር ይገባል።

ነገር ግን ያ መመጣጠን በዋነኝነት የሚሰራው ከስበት ኃይል ተጻራሪ ሁኔታ በመሆኑ ያ ኃይል በሌለበት ሁኔታ ይስተጓጎላል።

“በየወሩ 1 በመቶ የሚሆነው አጥንታችን እና ጡንቻዎቻችን እየተዳከሙ እና እየሳሱ ይሄዳሉ። ይሄም ሁኔታ እርጅናን ያፋጥናል” ሲሉ ፕሮፌሰር ቤይሊ ያስረዳሉ። ይህም መሬት ላይ በሚመጡበት ጊዜ ፍንትው ብሎ የሚታይ ይሆናል።

በህዋ ላይ የቆዩ የጠፈር ተመራማሪዎች በራሳቸው ለመቀመጥ ሲቸግራቸው የታየ ሲሆን ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ታይቷል።

ለዚያም ነው ወደ ህዋ የሚሄዱ የጠፈር ተመራማሪዎች በጥሩ የአካላዊ ሁኔታ መገኘት አለባቸው የሚባለው። በህዋ ባላቸውም ቆይታ በየዕለቱ በተቻለ መጠን የጡንቻ እና የአጥንት ጤንነታቸውን ለመጠበቅ ክብደትና ብስክሌት መንዳትን ጨምሮ ለሁለት ሰዓታት ያህል አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ከዘጠኝ ወራት በኋላ ከህዋ የተመለሱት ሱኒ እና ቡች ሰውነታቸው ያጣውን በራስ ተግባር ማከናወን ለመመለስ ከፍተኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስልጠና ፕሮግራም ይጀምራሉ።

“ምናልባትም የሰውነታቸውን ጡንቻ መልሶ ለመገንባት ጥቂት ወራት ሊፈጅባቸው ይችላል” ይላሉ ወደ ህዋ ሄደው የነበሩት ዶክተር ሄለን ሻርማን

ሆኖም የአጥንት ጥንካሬ መልሶ እስኪያገግም ድረስ የተወሰኑ ዓመታትን ሊፈጅ እንደሚችል የሚናገሩት ዶክተሯ ይህም ቢሆን “ወደ ምድር ከተመለስን በኋላ እንደገና የሚገነባው የአጥንት ዓይነት ላይ ጥቃቅን ለውጦች ስለሚኖሩ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመው ሁኔታ ሊመለሱ አይችሉም” ይላሉ።

በህዋ ላይ መቆየት ጡንቻና እና አጥንትን ብቻ ሳይሆን መላ ሰውነታችንን ይቀይረዋል።

በሰውነታችን ውስጥ የሚኖሩት ማይክሮባዮም የተሰኙት ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ይቀየራሉ።

በሰውነታችን ያሉ ፈሳሾችም ከስበት ኃይል አንጻር ሌላ ባህርያት ይይዛሉ።

ፈሳሾቹ በመሬት ስበት ወደ እግራችን ከመውረድ ይልቅ ወደ ደረታችን እና ፊታችን ወደ ላይ መሄድ ይጀምራሉ።

እብጠት የተሞላበት ፊት በሰውነታችን ውስጥ ከሚታዩ የመጀመሪያ ለውጦች አንዱ ነው።

ይህም የአንጎል እብጠትን እንዲሁም ዓይን ላይ ያሉ ነርቮችን ጨምሮ ቅርጹ ላይም ለውጦችን ሊያስከትል ይችላል።

ይህም በህዋ ላይ የሚደረገው በረራ ዕይታን የሚጋርድ ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል።

የማዞር ስሜት

የስበት ኃይል አለመኖር የሰውነትን ሚዛን የመጠበቅን መንገድ የትኛው ላይ ወይም ታች እንደሆነ የመለየት (ቬስትቡላር) ስርዓትን ያዛባል።

በህዋ ውስጥ ወደ ላይ፣ ወደ ታች ወይም ወደ ጎን የሚባል አቅጣጫ የለም።

መሬት ላይ ከወረዱ በኋላ የሚፈጠረው “የማዞር ስሜት፣ ሚዛን ለመጠበቅ መሞከር እንዲሁም እንደተለመደው ለመራመድ ጥንካሬ ማጣት ሁለት ወይም ሶስት ቀናትን ይወስዳል” ይላሉ ቲም ፒክ

“እነዚያ በምድር ላይ ያሉ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወይም ሶስት ቀናት ቅጣት ሊመስሉ ይችላሉ” ሲሉም ያክላሉ።