
23 መጋቢት 2025, 08:13 EAT
እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ኻን ዩኒስ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ከፍተኛ የሐማስ ፖለቲካዊ አመራር መገደላቸው ተሰማ።
የሐማስ ኃላፊ እሑድ ጥዋት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የፖለቲካ አመራር የነበሩት ሳላህ አል-ባርዳዊል በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።
የአካባቢው ሰዎች የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ አባል የነበሩት ባርዳዊል እና ሚስታቸው በአየር ጥቃቱ መገደላቸውን ተናግረዋል።
የእስራኤል ባለሥልጣን እስካሁን ስለግድያው አስተያየት አልሰጡም።
የእስራኤል ጦር ኃይል ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ በጋዛ ከፍተኛ ጥቃት ማድረስ የጀመረ ሲሆን ለተኩስ አቁሙ መቋረጥ ሐማስን ተጠያቂ ያደርጋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በአውሮፓውያኑ ጥር 19 የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ከሁለት ወራት በኋላ ፈርሷል።
ሐማስ የእስራኤልን ወቀሳ አይቀበለውም። የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን በካታር፣ ግብፅ እና ዩናይትድ ስቴትስ አሸማጋይነት የተፈረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት ያፈረሰችው እስራኤል ናት ይላል።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ጋዛ ሰርጥ በእስራኤል ጥቃት 32 ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።
እስራኤል በጋዛ ጥቃት ማድረስ የጀመረችው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 ሐማስ በእስራኤል ምድር ባደረሰው ጥቃት 1200 ሰዎችን ገድሎ 251 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው።
ከዚህ በኋላ እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው የአየር ድብደባ እና የእግረኛ ጦር ዘመቻ 49 ሺህ 500 ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል። አልፎም በጋዛ ያለው መሠረት ልማት ሙሉ በሙሉ ሲወድም በርካቶች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
- የሱዳን ጦር የፕሬዚደንቱን ቤተ መንግሥት መልሶ መቆጣጠሩ የአገሪቱን ጦርነት አቅጣጫ ይቀይራል?22 መጋቢት 2025
- በህዋ ለዘጠኝ ወራት ያህል መቆየት በሰውነት ላይ ምን ያስከትላል?23 መጋቢት 2025
- ‘ተዓምረኛዋ አምላክ’ ስትል ራሷን የምትጠራው ሕንዳዊት ማን ነች?23 መጋቢት 2025

በተያያዘ ዜና የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ሃማስ የተቀሩትን ታጋቾች በሙሉ እስካልለቀቀ ድረስ ወታደሩ “በጋዛ ተጨማሪ ቦታዎችን እንዲወር” እንዲሁም የተወሰኑ ክፍሎችን በቋሚነት እንደሚይዝ ዝተዋል።
እስራኤል ካትዝ የአገራቸው ወታደሮች በጋዛ የጀመሩትን የእግረኛ ጦር ጥቃት “በሕይወት ያሉ እና የሞቱት” ታጋቾች እስኪመለሱ ድረስ “አጠናቅረው እንደሚቀጥሉ” ተናግረዋል።
በጋዛ ከሚገኙት 59 ታጋቾች መካከል 24ቱ በሕይወት አሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ ሁለተኛው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የተደረገው ድርድር ውጤት ባለማሳየቱ ዕጣ ፈንታቸው አጠራጣሪ ሆኗል።
ከጥር ወር ጀምሮ ሲተገበር የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት በዚህ ሳምንት እስራኤል በጋዛ ላይ የጀመረችውን የምድር ዘመቻ እና የቦምብ ጥቃት ተከትሎ በይፋ አብቅቷል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ በተጨማሪም እስራኤል “የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በጋዛ ነዋሪዎች በፈቃደኝነት የማዘዋወር እቅድ ተግባራዊ ታደርጋለች” ብለዋል።
ትራምፕ አገራቸው የጋዛን ሰርጥ እንደገና እንድትገነባ እና ሁለት ሚሊዮን ፍልስጤማውያንን በዘላቂነት ለማንሳት እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
ባለፈው ማክሰኞ ዕለት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ከፍተኛ የአየር ድብደባ መክፈቷን ተከትሎ በሁለት ቀናት ውስጥ ከ430 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።