ኖላንድ አርባግ

23 መጋቢት 2025, 09:35 EAT

ኖላንድ አርባግ አንጎሉ ውስጥ ቺፕ አስቀብሯል። አእምሮው የሚያስተላልፈውን ትዕዛዝ ወደ ኮምፒውተር የሚያሻግርለትም ይህ ቺፕ ነው።

የ30 ዓመቱ ኖላንድ በአደጋ ሰውነቱ አልታዘዝ ካለው በኋላ ነበር ቺፕ ያስቀበረው። ቺፑን ካስቀበረ ስምንት ዓመት ሆኖታል።

የኢላን መስክ ኒውራሊንክ ተቋም አንጎሉ ውስጥ ቺፕ የቀበረለት የመጀመሪያው ሰው ኖላንድ ነው።

ቺፑ ሲቀበር የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠብቆ እንደነበር ይናገራል።

“ጥሩም ነገር ይምጣ መጥፎ ሳይንሱን እያገዝኩ ነው። ስኬታማ ከሆንን ለኒውራሊንክ ትልቅ ድል ነው” ይላል።

መጥፎ ነገር የሚከሰት ከሆነ ደግሞ ተቋሙ ከሱ መማር እንደሚችል ያምናል።

በ2016 የመኪና አደጋ ሲደርስበት ከወገብ በታች መንቀሳቀስ አቁሟል። የሚኖረው አሪዞና ነው።

መማርና መሥራት እንደማይችል በማሰብ በአደጋው በጣም አዝኖ ነበር።

“ሰውነትን አለመቆጣጠር ነጻነትን ማጣት ነው። ከባድ ነው። ሰዎች ሁሉኑም ነገር ሲያደርጉልኝ ማየት በጣም ይከብዳል” ይላል።

ኒውራሊንክ የገጠመለት ቺፕ የተወሰነ ነጻነት ሰጥቶታል።

ኮምፒውተር ከአእምሮው በሚተላለፍ ትዕዛዝ እንዲቆጣጠር ቺፑ አስችሎታል።

brain computer interface ወይም BCI የሚባለው ይህ አሠራር የሰዎች አእምሮ የሚፈጥረውን ትዕዛዝ ማስተላለፊያ መንገድ የሚከተል ነው።

ስንራመድ፣ ስንመገብ ወይም ሌላ ክንውን ስናደርግ አእምሮ የሚያስተላልፈውን መልዕክት ተከትለን ነው።

ቺፑ ይሄንን መልዕክት ተቀብሎ ነው ወደ ኮምፒውተር የሚወስደው።

በዘርፉ ብዙ ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል። የመስክ ተቋምም ምርምር ከሚያደርጉት አንዱ ነው።

ኖላንድ ቺፕ ከተቀበረለት በኋላ ለዘርፉ ትልቅ እመርታ ነው ተብሏል።

ኖላንድ አርባግ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

መስክ በሕዝብ ዘንድ ዕውቅና የሚያስገኝለትን ቺፕ በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲጽፍ ነበር።

“ተስፋ ሰጪ ውጤት በመጀመሪያው ዙር ሙከራ አግኝተናል። በቀጣይ የሚሆነውን በጉጉት እንጠብቃለን” ብሏል።

ብዙዎች ኒውራሊንክን ከመስክ ጋር ቢያይዙትም ኖላንድ ግን ቴክኖሎጂው ላይ ማተኮር ይመርጣል።

ኖላንድ በቀዶ ሕክምና ቺፑ ከተቀበረከት በኋላ አእምሮው በሚያስተላልፈው ትዕዛዝ የኮምፒውተር ቁልፍ ማንቀሳቀስ ችሏል።

ይህንን ለማድረግ ጣቶቹ እንዲንቀሳቀሱ አእምሮው እንዲያዝ አድርጓል። ቺፑም መልዕክቱን ተቀብሎ ወደ ኮምፒውተሩ ወስዶታል።

“የሆነ ሳይንሳዊ ልቦለድ ነገር ነበር የመሰለኝ” ይላል ኖላንድ።

ኮምፒውተሩን በአእምሮው መቆጣጠርና ማዘዝ መቻሉ መጀመሪያ ላይ እንግዳ ስሜት ነበር።

ኖላንድ ጌም እየተጫወተ ስላደረ ከአደጋው በኋላ ጌም መጫወት አለመቻሉ አሳዝኖት ነበር።

አሁን ግን በቺፑ አማካይነት ጌም መጫወት ችሏል።

“አሁን ጓደኞቼን አሸንፋቸዋለሁ። ሊሆን የሚችል ባይመስልም እውነት ነው” ይላል።

አእምሮው የሚያስተላልፈውን መልዕክት ብቻ ሳይሆን የሚያስበውንም ጭምር በቺፑ አማካይነት ለተመራማሪዎች ይፋ ማድረጉ ነጻነቱን የሚጋፋ እንደሆነ ሳይጠቅስ ግን አላለፈም።

የኒውሮሳይንስ ባለሙያ ፕ/ር አኒል ሴት “ዋናው ችግር የደኅንነት ጉዳይ ነው” ይላሉ።

“የምናደርገውንና የምናስበውን ማንም ሊያውቀው ይችላል። እናም ግለኝነታችን ላይ አደጋ ይደቅናል” ሲሉም አክለዋል።

ኖላንድ በቺፑ ታግዞ ዊልቸሩን መቆጣጠር ይፈልጋል።

ቴክኖሎጂው ፍጹም ነው ማለት አይደለም። በአንድ ወቅት ኖላንድ ኮምፒውተሩን መቆጣጠር ተስኖት ነበር። የኒውራሊንክ ባለሙያዎች ማረሚያ ካደረጉ በኋላ ወደቀደመ አገልግሎቱ ተመልሷል።

ሲንቾርን የተባለው ተቋምም ቺፕ ላይ ይመራመራል። አንጎል ላይ ቀዶ ሕክምና ከማድረግ ይልቅ በደም ሥር ቺፕ ማስገባት ላይ ትኩረት አድርጎ ነው የሚሠራው።

የተቋሙ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ሪኪ ባንርጂ “አንድ ሰው መፍጠር የሚፈልገውን በማንበብ ቺፑ ወደ ድርጊት ይወስዳል” ይላሉ።

አሁን ቴክኖሎጂውን 10 ሰዎች እየተጠቀሙበት ነው።

ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች አንዱ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ በዚህ ቺፕ አማካይነት በምናብ ኒው ዚላንድን መጎብኘት ችሏል።

“ቴክኖሎጂው ለወደፊት የት እንደሚደርስ ይታየኛል። ሰውነታቸውን ማዘዝ ለማይችሉ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚለውጥ ቴክኖሎጂ ነው” ይላል።