የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር

23 መጋቢት 2025, 09:21 EAT

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ዓለም አቀፍ ኃይል ተሳታፊ እንዲሆን ማለታቸውን የትራምፕ ልዑክ አወገዙ።

ስቲቭ ዊትኮፍ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ያመነጩት ሐሳብ “ቀላል መንገድ የተከተለ” እና አውሮፓውያን “እንደ ዊንስተን ቸርችል መሆን አለብን” የሚል እሳቤ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ዊትኮፍ የትራምፕ ደጋፊ ከሆነው ጋዜጠኛ ታከር ካርልሰን ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው ይህን ያሉት።

የትራምፕ ልዩ ልዑክ የሆኑት ዊትኮፍ ቭላድሚር ፑቲንን አድንቀዋል።

“እኔ ፑቲንን እንደ ክፉ ሰው አላየውም” ያሉት ዊትኮፍ “በጣም ብልኅ ሰው ነው” የሚል አድናቆት ጣል አድርገዋል።

ከቀናት በፊት ፑቲንን በአካል ያገኟቸው ዊትኮፍ የሩሲያው ፕሬዝደንት “ግርማ ሞገስ” ያላቸው እና የተሰማቸውን “በቀጥታ የሚናገሩ” እንደሆኑም ገልፀዋል።

አክለው ትራምፕ የግድያ ሙከራ በተፈፀመባቸው ወቅት ፑቲን ፀሎት እንዳደረጉላቸው እንደነገሯቸው ተናግረዋል።

ፑቲን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ፎቶ እንደ ስጦታ እንሰጧቸው እና በዚህም ትራምፕ “እጅጉን እንደተነኩ” አሳውቀዋል።

ዊትኮፍ በቃለ-ምልልሳቸው ወቅት የሩሲያን አቋም ሲያንፀባርቁ የተሰሙ ሲሆን ዩክሬን “ሐሰተኛ ሀገር ናት” ብለው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መቼ ነው በሩሲያ ይዞታ ሥር ላሉ የዩክሬን ግዛቶች እውቅና የሚሰጠው ሲሉ ጠይቀዋል።

“በጦርነቱ ትልቅ ጉዳይ የሚሰጣቸው አራት ግዛቶች የሚባሉት ናቸው። ዶንባስ፣ ክሬሚያ እና ያው የተቀሩት ሁለቱ ናቸው” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

አምስቱ ግዛቶች ሉሀንስክ፣ ዶኔትስክ፣ ዛፖሪዥዢያ፣ ኼርሶን እና ክሬሚያ ናቸው። ዶንባስ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ ሉንስክ እና ዶኔትስክን ያጠቃለለ የኢንዱስትሪ ግዛት ነው።

ዊትኮፍ በኩርስክ የሚገኙ የዩክሬን ወታደሮች ተከበዋል ቢሉም የዩክሬን መንግሥትን ይህ ትክክል አይደለም ይላል።

ጨምረው በከፊል በሩሲያ በተያዙ አራት ግዛቶች “ሕዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ አብዛኛው ሰው በሩሲያ አስተዳደር መሆን ይሻል” ሲሉም ተሰምተዋል።

ምንም እንኳ በተወሰኑ በሩሲያ በተያዙ የዩክሬን ግዛቶች ሕዝበ-ውሳኔ ቢደረግም አካሄዱ እና ውጤቱ ላይ ጥያቄ ተነስቷል።

ዊትኮፍ “ዩክሬን ሐሰተኛ ሀገር ናት” ብለው “የጦርነቱ መንስዔ በኔ አመለካከት ይህ ነው። ምክንያቱም ሩሲያ እኒህን ግዛቶች ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀምሮ የራሷ አድርጋ ነው የምትቆጥረው” የሚል ትንታኔ ሰጥተዋል።

ፕሬዝደንት ፑቲን የጦርነቱ መንስዔ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን በመስፋፋት ሩሲያ ላይ የሚያደርሰው ስጋት እና ዩክሬን ነፃ ሀገር ሆና መቆየቷ የሚያመጣው አደጋ እንደሆነ ይናገራሉ።

የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ወታደራዊ ድጋድ ሊደረግ ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።

ዊትኮፍ ይህ የአውሮፓውያን ነገሮችን “ቀለል አድርጎ” የመመልከት አባዜ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

በጥቁር ባሕር የተኩስ አቁም ስምምነት “በሚቀጥለው ሳምንት ይፈፀማል” ያሉት ልዑኩ “የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት” ለማድረግ ተቃርበናል ብለዋል።

በሩሲያ እና ዩናይትድ ስቴትስ መካከል ስላለው ግንኙነት የተጠየቁት ዊትኮፍ “ሩሲያ እና ዩኤስኤ በጋራ መልካም ነገር የሚሠሩበት ዓለም ማየት የማይሻ ማን አለ?” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።