ትራምፕና ሀሪስ

23 መጋቢት 2025, 08:46 EAT

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ የነበራቸውን ምሥጢራዊ መረጃ የመመልከት ፈቃድ አነሱ።

ባለሥልጣኖች የአገሪቱን ምሥጢራዊ መረጃ መመልከት የሚችሉበትን ፈቃድ የተነጠቁት የትራምፕ ተቀናቃኝ የነበሩት ካማላ ሀሪስ ብቻ ሳይሆን ሂላሪ ክሊንተንም ጭምር ናቸው።

ትራምፕ የቀድሞ ባለሥልጣኖችና ተቺዎቻቸውን ፈቃድ አንስተዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን እንዲሁም የቤተሰቦቻቸውን ፈቃድ እንደሚያነሱም ሲናገሩ ነበር።

“እነዚህ ሰዎች ምሥጢራዊ መረጃ የማግኘት ፈቃዳቸው ለብሔራዊ ጥቅማችን ዋጋ ስለሌለው ፈቃዳቸው እንዲነሳ ወስኛለሁ” ብለዋል ትራምፕ።

ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር የቀድሞ ባለሥልጣኖች ምሥጢራዊ መረጃ የማግኘት ፈቃዳቸው ይጠበቅላቸዋል።

ትራምፕ ፈቃዳቸውን የነጠቋቸው ተቀናቃኞቻቸው ወደ መንግሥት ተቋማት የመግባት ፈቃድ አይኖራቸውም።

“ምሥጢራዊ መረጃ አያገኙም፣ በየቀኑ ለፕሬዝዳንቱ የሚሰጠውን ማብራሪያ አያገኙም እንዲሁም በደኅንነት ተቋማት ሥር ያለ መረጃ አያገኙም” ይላል የተላለፈው ዕግድ።

ትራምፕ በከፍተኛ የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣናት ላይ ያነጣጠረ እርምጃ ነው የወሰዱት። ዋነኛ ተቺዎቻቸውና ትራምፕን ፍርድ ቤት ያቀረቡ ዐቃቤ ሕጎችም በዕግዱ ተካተዋል።

የባይደን የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን፣ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሌቫን እና ምክትል ዐቃቤ ሕግ ሊሳ ሞናኮ ፈቃዳቸው ተነስቷል።

ትራምፕ በቀድሞ የሥልጣን ዘመናቸው አስተዳደር ላይ የነበሩና በፍርድ ቤት ምስክርነታቸውን የሰጡ ሁለት ሰዎችን ፈቃድም ነጥቀዋል።

እነዚህም ፊዮና ሂል እና አሌክሳንደር ቪንድማን ናቸው።

ሪፐብሊካን የሆኑ ተቺዎች ሊዝ ቼኒ እና አዳም ኪንዚንገርም ፈቃዳቸው ተነስቷል።

ከካፒቶል ሂል አመጽ ጋር በተያያዘ በተከፈተው ምርመራ የተሳተፉ ብቸኞቹ ሪፐብሊካኖች ነበሩ።

ትራምፕ እና የንግድ ተቋማቸውን የከሰሱት የኒው ዮርክ ዐቃቤ ሕግ ለቲሻ ጄምስ ፈቃድም ተነስቷል።

በዚህ ክስ ትራምፕ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ክፍያ ቢፈረድባቸውም ትራምፕ ይግባኝ ብለዋል።

ትራምፕ የፌደራል መንግሥቱን ሠራተኞች ከመቀነሳቸው ጋር የተያያዘ ክስ የመሠረቱት ኖርም ኤሪሰን ፈቃድም ተነጥቋል።

“የትራምፕ ዕግድ ተጨማሪ ክስ እንዳቀርብ ነው የሚያደርገኝ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የትራምፕን ትዕዛዝ በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ተችተዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም የቀድሞ የደኅንነት ሠራተኞችን ፈቃድ ማንሳታቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ፈቃዱን ያነሱን ሠራተኞቹ በ2020 ለባይደን አስተዳደር ወግነዋል በሚል ቢሆንም ይህንን የሚያሳይ ማስረጃ አላቀረቡም።

በ2021 ባይደን ሥልጣን ላይ ሳሉ ትራምፕ “ያልተገባ ባህሪ አሳይተዋል” ብለው ትራምፕ ምሥጢራዊ መረጃ የማግኘት ፈቃዳቸውን መገደባቸው ይታወሳል።

በ2024 የፍትሕ ቢሮው ባገኘው መረጃ ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ ባልተገባ መንገድ ምሥጢራዊ መረጃ አግኝተዋል ብሎ ነበር።

በ2023 ደግሞ ትራምፕ ምሥጢራዊ መረጃን ባልተገባ ሁኔታ ይዘዋል ተብሏል።