*በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*



ኢሕአፓ/eprp
የትግራይ ሕዝብ መከራ በአስቸኳይ ይቁም!!
*በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢአፓሕ) በትግራይ ክልል እየተስተዋለ የሚገኘውን ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የተከፋፈሉት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሁለት ክፍሎች የሕዝቡን መብትና ጥቅም ሊያከብሩ የሕዝቡን የሠላምና የልማት ፍላጎቶች ሊያስቀድሙ ይገባል ይላል።
አሁን የምናስተውለው፣ሁለቱም የህወሓት ክፍሎች፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩና በሊቀመንበሩ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ወገን፤ እንዲዳኛቸው በተደጋጋሚ የሚማጠኑት ሆን ብሎ በተጠና ስልታዊ መንገድ የትግራይ ህዝብን ለአመታት በቀጠለ ስቃይና መከራ ውስጥ የከተተውን፣ እነሱንም እያራኮተ ያለውን፣ ያለጦርነት መፍትሄ የማያውቀውን ብልጽግና መራሹን የፌደራል መንግስት ነው። ችግሩን እያባባሰባቸው ያለው ራሱ መሆኑን እንዴት መገንዘብ ይሳናቸዋል!?
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ለሰላምና ለእርቅ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ይልቅ በትግራይ ውስጥ ውጥረቱን የሚያባብሱ ንግግሮች እያደረገ፣ ከባድ ጉዳት የሚያስከትሉ ወታደራዊ እርምጃዎች ምርጫዎቹ መሆናቸውንና ከዚህ ቀደም በተካሄደው አውዳሚ ጦርነትም አለመጸጸቱን አሳይቷል።
ከአሰቃቂውና ከ 600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ትግራዋይ ዜጎቻችንን ካሳጣንና ሊገለጽ የማይችል ከፍተኛ ውድመት ካደረሰው ጦርነት ማግስት በህዝብ ላይ ሊደረጉ የማይገባቸው ጎጅ ተግባሮችን የፈጸመን አገዛዝ ከፋፍሎ የማጋጨት ዕቅድ ሰለባ በመሆን እሱኑ ደጅ መጥናት፤ የሚመሩትንና የችግሮቹ ሁሉ ገፈት ቀማሽ የሆነውን የትግራይ ክልል ህዝብ ብሶት፣ መከራና ችግር መናቅ ወይም ተገቢ ሥፍራን አለመስጠት እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል።
ብልፅግና ፓርቲ የትግራይ ተወላጆችን መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ያለማቋረጥ ረግጧል። በመንግስት ሀይሎች የተፈጸሙ ያለፍርድ እና የጅምላ ግድያዎች፣ የጅምላ እስራቶች፣ ማሸማቀቆች፣ መደፈሮች እና መጠነ ሰፊ መፈናቀሎች እንዲሁም ሊሎችም ዘግናኝ ወንጀሎች መፈጸማቸው በዐለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጭምር ተጋልጠዋል።
የተቋማቱ ሪፖርቶች ተራ አሀዛዊ መረጃዎች ብቻ ሳይሆኑ የእጅግ ብዙ ንጹሃን ዜጎችን ሕይወት መጎዳት፣ መበላሸትና መመሰቃቀል በምሳሌነት የሚያስዩም ናቸው። እንደዚህ ላሉት በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር ለሚመሳሰሉ ጥሰቶች የፌዴራሉ መንግስት ተጠያቂ መሆን አለበት። ተጠያቂ መሆን ያለበት አካል ራሱ ዛሬ ከሚታዩት ሁኔታዎች አኳያ ደግሞ በምንም አይነት መለኪያ ያንን ሁሉ በደል ላደረሰበት ህዝብ ዛሬ በተቃራኒው ፍትሕን ያስገኝለታል ተብሎ አይታሰብም። እየከፋና እየባሰበትም እየመጣ እንደሆነ እየተስተዋለም ፍትኅ ያመጣል ተብሎ ሊታሰብ በፍጹም አይገባም።
በትግራይ ያለው ሰብአዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ቀጥሏል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ረገድ የፌደራሉ መንግስት ምላሽ በጣም ሃላፊነት የጎደለው፣አስክፊና አሳፋሪም ነው። ሆን ብሎም በጦርነቱ ወቅት እንዲሁም ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ ህዝብ ላይ ስቃይ ርሃብና ሞትም አውጇል። የብልጽግና ፓርቲ የትግራይን ህዝብም ሆነ የሌሎችን ክልሎች የራስ ገዝ አስተዳደርና መብት በመናድ በትግራይ ዛሬ የሚታየውን የፖለቲካ ምስቅልቅልም ፈጥሯል፡፡
በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱት ጥቂት ማሳያዎች መሰረት አሁን ላይ በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ ያሉት በጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ በህወሃት ሊቀመንበሩ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደነበረው ተቀዳሚ ትኩረታቸው ህዝብ ከሆነ መፍትሄውን ራሳቸው ጋር እንጂ ለህዝብ ከጭካኔ ያለፈ ቀናዒነት እንደሌለው በተደጋጋሚ እያሳየ ከሚገኘው የብልጽግና መንግስት ባለመጠበቅ በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
የህወሓት እንዲሁም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሃላፊነት እና ቀጣይ መንገድን በተመለከተ፤
የፌደራል መንግስቱ የትናንትም ሆኑ የዛሬ ርምጃዎች ለቀጣይ ግጭት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ መገንዘብ አቅቶት ሳይሆን ፈልጎት መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል።
ህወሓት በተለይም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር እና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና እርቅ ለመፍጠር ገንቢ በሆነ መንገድ የመሳተፍ ኃላፊነት አለበት። ህወሓት በዚህ ወሳኝ ወቅት ከፓርቲያዊ ጥቅም ይልቅ የትግራይ ህዝብ አንድነትን ሊያስቀድም ይገባል። ጊዜያዊ አስተዳደሩም ቢሆን ከስልጣን ይልቅ የትግራይ ህዝብ ሰላምና ደህንነት የትኩረት ነጥቡ ሊሆኑ ይገባል። ይህ እርምጃም እርስ በእርስ ባለው ግንኙነት ሁሉን አቀፍነትን፣ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ማሳየትን ይጠይቃል።
በተጨማሪም ከትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር መቀራረብ የህዝቡን ፍላጎትና ፍላጎት ለመረዳት ወሳኝ ነው። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህዝቡን ድምጽ የሚያንፀባርቁ ፖሊሲዎችን የማዘጋጀት ሀላፊነትን አለበት።
በመሆኑም ፓርቲያችን አሁን ካለው ችግር አንፃር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከየትኛውም ሁኔታ በላይ ለትግራይ ህዝብ ቅድሚያ እንዲሰጡ አደራ ይላል። የትግራይ ህዝብ ከጥቃት፣ ከጭቆና እና ከመገለል የጸዳ ህይወት ይገባዋል።
በማጠቃለያም ኢሕአፓ የሚከተሉት የሕዝብ መብቶች እንዲከበሩና ጥቅሞቻቸውም እንዲጠበቁ ይጠይቃል።
1. ማንኛውም ዐይነት የሰብአዊ መብት ረገጣ በአስቸኳይ እንዲቆም እና እስካሁን ለተፈጸሙ ወንጀሎችና ጥፋቶችም ተጠያቂ በሆኑት ላይ ህጋዊ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል።
2. የዜጎች በህይወት የመኖር መብት እንዲረጋገጥ እና ሰብአዊ እርዳታ ያለምንም እንቅፋት ለተጎጂዎች እንዲደርስ መደረግ አለበት።
3. ሁሉም የፖለቲካ ችግሩ የሚመለከታቸው ወገኖች ትርጉም ያለው አካታች የፖለቲካ ውይይት በማድረግ የግጭቶቹን መንስኤዎች በማጥናት ችግሮቹን ለመፍታት እና የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር እኩል ባለመብት ሆኖ የሚኖርበት ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩለት ማድረግ ይገባቸዋል።
4. በትግራይ ውስጥ ያለው ችግር ውስብስብ እና ዘርፈ ብዙ ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ እና ፍትሃዊ መፍትሄ ለማግኘት ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን እንዲረዱት ማስፈለጉን በአጽንዖት እንገልፃለን።
5. በመጨረሻም የትግራይ ህዝብን የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም በስጋት እና በፍርሃት ውስጥ እንዲኖር እያደረጉ ያሉት ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ለህዝቡ ሰላሙን እንዲሰጡት አበክረን እንጠይቃለን።
ከፊታችን ያሉትን ፈተናዎች በጋራ በማሸነፍ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ብሩህ ተስፋ መገንባት እንችላለን።
ሕዝብ ሃያል ነውና ሁሌም ህዝብ ያሸንፋል!!
መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ/ም