
24 መጋቢት 2025
ብሬንት ደሚትራክ ራሱን የርዕደ መሬት ነቢይ ሲል ይጠራል።
ባለፈው ጥቅምት አጋማሽ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ የማኅበራዊ ሚድያ ተከታዮቹ በምዕራባዊ ካሊፎርኒያ የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል ሲል ተናገረ።
ከሁለት ወራት በኋላ 7.3 ሬክተር ስኬል የሆነ ርዕደ መሬት ሰሜናዊ ካሊፎርኒያን ነቀነቃት።
በዚህ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሥፍራው ነዋሪዎች በሱናሚ እንመታለን የሚል ስጋታቸው ጨመረ። የብሬንት ተከታዮችም ቁጥር ያሻቅብ ጀመር። ብዙዎች ቀጣዩ ርዕደ መሬት የት ይከሰታል የሚለውን ማወቅ ይሻሉ።
“እኔ የምሠራውን ሥራ ለሚያቃልሉ ሰዎች የምለው እንዴት ነው ይህ አጋጣሚ ነው የምትሉት ነው። ርዕደ መሬት የት ይከሰታል የሚለውን ማወቅ ትልቅ ክህሎት ይጠይቃል” ሲል በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ ተናግሯል።
ነገር ግን አንድ ችግር አለ። የዘርፉ ሳይንቲስቶ ርዕደ መሬትን መተንበይ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው ይላሉ።
የመሬት መንቀጥቀጥ መገመት አለመቻሉ ነው አስፈሪ የሚያደርገው።
በሰሜን አሜሪካ በምዕራቡ ጠረፍ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች “ከባድ” ርዕደ መሬት ተከስቶ የብዙዎችን ሕይወት ይቀጥፋል የሚል ስጋት አላቸው።

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ሉሲ ጆንስ የርዕደ መሬት ባለሙያ (ሴይስሞሎጂስት) ሲሆን ዩኤስ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ (ዩኤስጂኤስ) ለተባለው የአሜሪካ መንግሥት የርዕደ መሬት ጥናት ተቋም ለሶስት አስርት ዓመታት ሰርተዋል።
ዘ ቢግ ዋን የተሰኘ መፅሐፍ ያሳተሙት ባለሙያዋ የመሬት መንቀጥቀጥ የመከሰት ዕድል እና እንዴት መቋቋም ይቻላል የሚለውን ያጠናሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሰዎች የመሬት መንቀጥቀጥ መች እንደሚከሰት መተንበይ እንችላለን ሲሉ ተደምጠዋል።
“ሰዎች እንዲህ ዓይነት ነገር ለማወቅ ያላቸው ፍላጎት የተለመደ ቢሆንም የመተንበይ አቅም ግን የላቸውም” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ምድራችን በዓመት እስከ 100 ሺህ የመሬት መንቀጥቀጦች ታስተናግዳለች ይላል ዩኤስጂኤስ፤ ሰዎች የመሬት መንቀጥቀጥ መች እንደሚከሰት ማወቅ መፈለጋቸው የሚገርም አለመሆኑን ለማስረዳት።
ከሳን ፍራንሲስኮ ከተማ በስተሰሜን በምትገኘው የባሕር ዳርቻዋ ዩሬካ ከተማ ባለፈው ዓመት ብቻ 700 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶባታል። ባለፈው ሳምንት ብቻ ደግሞ 10 ርዕደ መሬቶች ተመዝግበዋል።
በዚህ ሥፍራ ነው ብሬንት የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል ብሎ ገምቶ የተሰካለት።
ዩኤስጂኤስ ይህ አካባቢ በርካታ የመሬት መንቀጥቀጦች ከሚያስተናግዶ ሥፍራዎች አንዱ ነው ይላል። ይህ የሆነው ሶስት ቴክቶኒክ ድንጋዮች የሚገናኙበት ስለሆነ ነው።
መሬት የተዋቀረችው በሦስት ንብርብሮች ነው። የመሬት ማዕከላዊው ክፍል ‘ኮር’ ይባላል። ቀጥሎ የሚገኘው ‘ማንትል’ ነው። በመቀጠል ‘ክረስት’ ይመጣል። ይህ በዓይናችን የምናየው የመሬት ክፍል ነው።
ክረስት እና የማንትል የላይኛው አካል ቴክቶኒክ ፕሌትስ ከተባለው ድንጋይ የተሠሩ ናቸው።
‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ ዝግ ባለ መልኩ ሁሌም ይጓዛሉ። በዚህ መካከል ግጭት እና መተፋፈግ ይፈጠራል። ይህ ነው የመሬት መንቀጥቀጥ ሆኖ በመሬት ገጽ ላይ ያሉ አካላትን የሚነቀንቀው እና የሚያፈራርሰው።
በቀላል አገላለጽ በዓይናችን ከምናየው መሬት በታች ያሉት ንብርብር አለቶች በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ እርስ በርስ ሲተፋፈጉ አሊያም ሲፋጩ መሬት ትንቀጠቀጣለች ማለት ነው።
በዩሬካ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል ብሎ መገመት ቀላል ነው የሚሉት ሉሲ ጆንስ ነገር ግን መጠኑ ከፍ ያለ እንደሆነ መተንበይ ብዙም ያልተለመደ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ዩኤስጂኤስ በዚህ አካባቢ ከአውሮፓውያኑ 1990 በኋላ 5 ጊዜ ብቻ ነው ከፍተኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው ይላሉ። አንዱ ብሬንት የገመተው ነው።
- በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ምን አይነት ጥንቃቄ ልናድርግ ይገባል?6 ጥር 2025
- የመሬት መንቀጥቀጦች አስከፊ የሚሆኑባቸው 7 ምክንያቶች9 ጥር 2025
- የሞባይል ስልካችን የመሬት መንቀጥቀጥን ለመለየትና ማስጠንቀቂያ ለማግኘት እንደሚያስችል ያውቃሉ?14 መስከረም 2024

ሳይንቲስቶች የመሬት መንቀጥቀጥ ለምን እንደሚከሰት ባያውቁም መተንበይ ግን ፍፁም የማይሆን ነው ይላሉ።
ዩኤስጂኤስ እንደሚለው በአንድ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ በተወሰኑ ዓመት የመከሰት ዕድሉን ማስላት ቢቻልም መጠኑ ምን ያክል ይሆናል የሚለውን መተንበይ ከባድ ነው።
ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው ከሚገመቱ ሥፍራዎች አንዱ ደቡብ ካሊፎርኒያ ነው። ቢሆንም መች ይከሰታል የሚለው አይታወቅም። በሥፍራው ኃይለኛ የሚባል ርዕድ መሬት የሚከሰተው ከ200-300 ዓመታት ባለው ጊዜ ነው።
ሉሲ ጆንስ እንደሚሉት በርካታ ሰዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ትንበያ የማድረግ አቅም እንዳለቸው ነግረዋቸው ያውቃሉ።
ብሬንት ሳይንቲስት አይደለም። በደቡብ ምዕራብ አላስካ፣ ጃፓን እና በኒው ዚላንድ ደሴቶች ከፍተኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል ሲል ገምቶ ያውቃል።
ዩኤስጂኤስ የመሬት መንቀጥቀጥን ለመተንበይ ሶስት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው ይላል። ቀን እና ሰዓት፣ የመሬት መንቀጥቀጡ የሚከሰትበት ሥፍራ እንዲሁም መጠኑ።
የብሬንት ግምት ይወላውላል። በአንድ ወቅት ከትራምፕ በዓለ ሲመት በፊት ወይ በኋላ ሲል ገምቶ ነበር። ቀጥሎ ደግሞ ከ2030 በፊት ሲል ተነበየ።
የርዕደ መሬት ነቢይ ሲል ራሱን የሚጠራው ብሬንት ይህ ታላቁ ርዕደ መሬት በቅርብ ዓመታት እንደሚከሰት ያምናል።
“የዕድል ጉዳይ አይደለም። አሊያም መገጣጠም አይደለም” ሲል ለቢቢሲ ይናጋራል።